ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሐማስ ባለሥልጣን የትራምፕ የሰላም ዕቅድ "የፍልስጤም ሕዝብን ፍላጎት ችላ ያለ ነው" አሉ
አንድ ከፍተኛ የሐማስ ባለሥልጣን የዶናልድ ትራምፕ የጋዛ የሰላም ዕቅድ የእስራኤልን ፍላጎቶች የሚጠቅም እና "የፍልስጤምን ሕዝብ ፍላጎት ችላ ያለ" በመሆኑ ቡድኑ ላይቀበለው እንደሚችል ለቢቢሲ ገለፁ።
ባለሥልጣኑ በትራምፕ የሰላም ዕቅድ ላይ እንደተቀመጠው ሐማስ ትጥቁን ፈትቶ ለማስረከብ የመስማማት ዕድሉ ጠባብ መሆኑን ተናግረዋል።
ሐማስ በጋዛ ዓለም አቀፍ የሚያረጋጋ ኃይል ይሰማራል መባሉን አዲስ ዓይነት ወረራ ነው በማለት ተቃውሟል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የትራምፕን ዕቅድ ሰኞ ዕለት በዋይት ሐውስ በተገኙበት ወቅት ተቀብለዋል።
ሐማስ እስካሁን ድረስ ይፋዊ ምላሽ አልሰጠም።
የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሐማስ በዋይት ሐውስ የቀረበውን ምክረ ሃሳብ "ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ" እየተመለከተው ነው ብለዋል።
ስለ ሐማስ ድርድር እውቀቱ ያላቸው የፍልስጤም ባለሥልጣን ለቢቢሲ ቡድኑ በጋዛ እና በሌላ አካባቢ የሚገኙ አመራሮቹን ማሳተፉን ተናግረዋል።
የቡድኑ ወታደራዊ አዛዥ ኢዝ አል ዲን አል ሃዳድ የቀረበው ዕቅድ ላይ ከመስማማት ይልቅ መዋጋትን እንደሚመርጡ እየተነገረ ነው።
በቅርቡ ከጋዛ ውጭ ያሉ የሐማስ ባለሥልጣናት ታጋቾቹን ላይ ቀጥተኛ ቁጥጥር ስለሌላቸው ከሚደረጉ ውይይቶች ገለል ተደርገው ነበር።
በርካታ ቀናትን ይወስዳል ተብሎ የሚጠበቀው የሐማስ ድርድር ሌሎች የፍልስጤም አንጃዎችንም አካትቷል።
በመስከረም 26ቱ ጥቃት ላይ የተሳተፈው እና የተወሰኑ የእስራኤል ታጋቾችን ይዞ የነበረው የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ (ፒአይጄ) በመባል የሚታወቀው ታጣቂ ቡድን ዕቅዱን ማክሰኞ ዕለት ውድቅ አድርጓል።
ሐማስ ዕቅዱን ለመቀበል ከባድ የሚያደርግበት ብቸኛ መደራደሪያው የሆኑትን ታጋቾች ሁሉንም በአንድ ጊዜ እንዲያስረክብ የሚለው ክፍል ነው።
ምንም እንኳ ዶናልድ ትራምፕ ዕቅዱን ቢደግፉትም እሰራኤል ታጋቾቹን ከተቀበለች በኋላ በቅርቡ ዶሃ ላይ የሐማስ አመራርን ለመግደል የአሜሪካን አለመስማማት ችላ በማለት እንዳደረገችው ወታደራዊ ዘመቻዋን ልትቀጥል ትችላለች የሚል ጥርጣሬ አለ።
ከዚህ በተጨማሪ የትራምፕ አስተዳደር ይፋ ያደረገው የጋዛ ካርታ፣ አካባቢው ከግብጽ ጋር በሚዋሰንበት ደቡባዊ ክፍል ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ ቀጠና እንደሚገነባ ያሳያል።
ይህ እንዴት አንደሚተዳደር ይፋ ያልሆነ ሲሆን እስራኤል የምትሳተፍበት ከሆነ ለአለመግባባት መነሻ መሆኑ አይቀርም።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚነሲትር ምንም እንኳ ሰኞ ዕለት በዕቅዱ ላይ መስማማታቸውን ቢገልፁም ኔታንያሁ የዕቅዱን በርካታ አካላት ወደ ጎን ሲሉ ተስተውለዋል።
በኤክስ ገጻቸው ላይ ባጋሩት የቪዲዮ መልዕክት የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ እንደሚቆዩ እና የፍልስጤምን አገርነት "በኃይልም ቢሆን እንደሚቃወሙ" ተናግረዋል።
ይህ ከትራምፕ ዕቅድ በተቃራኒ የቆመ ሃሳብ ነው።
በትራምፕ ዕቅድ ላይ የእስራኤል ጦር ሙሉ በሙሉ ለቅቆ እንደሚወጣ ያስቀመጠ ሲሆን ዕቀዱ በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ ከሆነ "የፍልስጤማውያን ራስን በራስ ማስተዳደር እና አገርነት ጥርጊያ መንገድ እንደሚከፍት" አስቀምጧል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም ከነበራቸው አቋም በተለየ ሁኔታ የጋዛ ነዋሪዎች ከተማውን ለቀው እንዲወጡ አይገደዱም።
"ነዋሪዎች እዛው እንዲቆዩ እናበረታታለን። የተሻለች ጋዛን እንዲገነቡ እናግዛቸዋለን" በሚል በሰላም ዕቅዱ ላይ ሰፍሯል።
በጋዛ ውስጥ በርካታ ፍልስጤማውያን ጦርነቱን ስለሚያስቆመው የዕቅዱ ደጋፊዎች ናቸው።
የሰላም ዕቅዱ ሐማስ ጋዛን በማስተዳደር ረገድ "ቀጥተኛ ወይም ተዘዋዋሪ" ሚና ሊኖረው እንደማይችል ያትታል።