ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሐማስ ታጋቾችን ለመልቀቅ መስማማቱን ተከትሎ እስራኤል ጋዛን መደብደብ እንድታቆም ትራምፕ አሳሰቡ
ሐማስ የተቀሩትን እስራኤላውያን ታጋቾች ለመልቀቅ መስማማቱን ገልጾ በሰላም ዕቅዱ ላይ ተጨማሪ ድርድር እንደሚያስፈልግ አስታውቋል።
ሐማስ የሰላም ዕቅዱን መቀበሉን ካስታወቀ በኋላ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል በጋዛ የምታደርሰውን ጥቃት እንድታቆም አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ፤ ሐማስ የሰላም ዕቅዱን ካልተቀበለ "ገሀነም ይጠብቀዋል" በማለት ሲዝቱ ቆይተዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሰላም ዕቅዱን የመጀመሪያ ምዕራፍ ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሐማስ "ለዘላቂ ሰላም ዝግጁ ነው" ያሉት ትራምፕ በበኩላቸው እስራኤል ጋዛን መደብደብ ማቆም አለባት ብለዋል።
ትራምፕ የሐማስን ምላሽ በበጎ ቢቀበሉም ቡድኑ ቁልፍ የሆኑ የሰላም ዕቅዱን ክፍሎች አለመቀበሉ ጥያቄ አጭሯል።
20 ነጥቦች ካሉት የአሜሪካ የሰላም ዕቅድ መካከል በተወሰኑት እንደሚስማማ ሐማስ ገልጿል።
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር አሁን ያለው ሁኔታ ተስፋ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ "አሳዛኙ የጋዛ ግጭት እንዲቆም ሁሉም ወገኖች እንዲተባበሩ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል።
የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን "ሐማስ ለጋዛ የሰላም ዕቅድ የሰጠው ምላሽ ገንቢ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የጀርመን መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ በበኩላቸው "ታጋቾች የሚለቀቁበት እና በጋዛ ሰላም የሚሰፍንበት ወቅት ተቃርቧል" ብለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን "ሁሉም ታጋቾች ተለቀው በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚደረስበት ወቅት ተቃርቧል" በማለት መግለጫ አውጥተዋል።
የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በበኩላቸው "ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የተኩስ አቁም ስምምነት ነው" ብለዋል።
ሐማስ የሰላም ዕቅዱ ቁልፍ ነጥቦች ላይ ለመስማማት ባይፈቅድም የሰላም ዕቅዱ እንዲተገበር ከአጋሮቹ ጫና እየተደረገበት ነው።
ሐማስ የተስማማባቸው ነጥቦች ጦርነቱን ማስቆም ይችሉ እንደሆነ አሁንም በግልጽ አልታወቀም።
እስራኤል የወታደሮቿን ቁጥር "እንደምትቀንስ" አስታውቃለች።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት "ጋዛን በቁጥጥሩ ሥር ለማዋል" የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲገታ ትዕዛዝ መተላለፉም ተዘግቧል።
ኔታንያሁ የሰላም ዕቅዱን የመጀመሪያ ምዕራፍ ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ቢገልጹም፣ ትራምፕ ካስቀመጧቸው 20 ነጥቦች መካከል የትኞቹን እንደሚተገብሩ ግልጽ አይደለም።
20 ነጥብ ባለው የሰላም ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱት ሐሳቦች አንዱ ጋዛ "ለጎረቤቶቿ ስጋት የማትሆን እና ከሽብር ነጻ የሆነች ከተማ መሆን አለባት" ይላል።
በጋዛ "መልሶ ግንባታ ተከናውኖ የጋዛ ሕዝቦች ተጠቃሚ ይሆናሉ" የሚል ነጥብም ተካቷል።
ሁለቱ የሰላም ዕቅዱ ነጥቦች ከተሳኩ በኋላ "ጦርነቱ ይቆማል" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።
ከዚያም "የእስራኤል ወታደሮች አካባቢውን ለቀው ይወጣሉ" በማለት አክለዋል።
ሐማስ የተቀሩትን እስራኤላውያን ታጋቾች ከለቀቀ በኋላ 2,000 ፍልስጤማውያን እስረኞችን እስራኤል ትለቃለች።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው "ታጋቾችን በቶሎ እንድናድን እስራኤል ጋዛን መደብደብ ማቆም አለባት" ብለዋል።