የፍልስጤማውያን ወላጆች ሰቆቃ፡ 'ልጄ ምግብ እየጠበቀ ተገደለ'

ዲአ በማዕከላዊ ጋዛ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ ይኖራል። የልጆች አባቱ ዲአ እንግዶቹን በፈገግታ ቢያስተናግድም ሕመሙን መደበቅ አይችልም።

"ይሄ የአብደላ ክፍል ነው።ጎራ በሉ" ሲል እንግዶቹን ይቀበላል። አብደላ የ19 ዓመት ልጁ ነው። በጋዛ የሰብዓዊ እርዳታ ሲከፋፈል በተተኮሰ ጥይት ነሐሴ መባቻ ላይ ተገድሏል።

እርዳታው አሜሪካና እስራኤል በጥምረት መስጠት የጀመሩት ሲሆን በእስራኤልና አሜሪካ ወታደሮች ጥበቃ ይደረግበታል።

ዲአ የልጁን ቦርሳ አቅፎ ተቀምጧል። "የውድ ልጄ ጠረን አሁንም ቦርሳው ላይ አለ። ፈጣሪ ነፍሱን ይቀበላት" ይላል ዲአ።

ዲአ በልጁ ሕልፈት ራሱን ተጠያቂ ያደርጋል። ከመገደሉ ከአንድ ቀን በፊት ወደ እርዳታ መስጫው ልጁ እንዳይሄድ ቢጠይቀውም ልጁ ግን "አታስብ አባዬ፣ ከፈጣሪ ጋር ሁሉም ይሳካል" ሲል መለሰለት።

"አስቀያሚ ስሜት ነው። ልጄን ወደ ሞት ሰደድኩት። ግን እርዳታው ያስፈልገን ነበር። እኔንና እናቱን እንዲሁም ታናናሾቹን ለመመገብ ሲል ሄደ።"

እስራኤል ወደ ጋዛ እርዳታ እንዳይገባ በማገዷ ረሃብ እጅጉን በርትቷል። የተኩስ አቁም በተደረገበገት ጊዜ ብቻ ነበር እርዳታ በአግባቡ መድረስ የቻለው። ሆኖም እስራኤል ሙሉ ዕቀባ ጥላ ጦርነቱ ዳግመኛ ተጀምሯል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የድንገተኛ ጊዜ የምግብ እርዳታ የሚያደርገው ተቋም እንዳለው በጋዛ ከተማ ረሃብ ተስፋፍቷል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ረሃብ የለም ይላሉ። ለተፈጠረው የእርዳታ "እጥረት" እስራኤል ተጠያቂ አይደለችም ሲሉ ያስተባብላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ሐማስ እርዳታ ሲዘርፍ ማስቆም አልቻለም ሲሉም ይከሳሉ። ተመድ ክሱን ያጣጥላል። እስራኤል ለክሷ ማስረጃ እንደሌላትም ያስረግጣል።

ረሃብ በጠናባት ጋዛ እንደ አብደላ ያሉ ወጣቶች ራሳቸውን ለሞት አጋልጠው ወደ ሰብአዊ እርዳታ ማዕክል ያቀናሉ።

እስራኤል በጋዛ የምታደሰው ጥቃት የፍልስጤማውያንን ሕይወት እንዳልነበረ አድርጓል። ቢያንስ 65,000 ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተዘግቧል።

አብደላ ብሩህ ወጣት ነበር። በክፍሉ ውስጥ በለጠፋቸው ማስታወሻዎች በፈተናው ከ95% በላይ ነጥብ ማግኘት እንዳለበት ራሱን ያስታውሳል።

ሁሌም ሽክ ያለ አለባበስ ይመርጣል። ከፊቱ ፈገግታ አይጠፋም። እየፈራረሰች ባለችው ጋዛ ውስጥም ቢሆን ቀጣይ ሕይወቱ እንዲሰምር ይወጥን ነበር።

በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉት መካከል ከ18,000 በላይ የሚሆኑት ልጆች መሆናቸው ተዘግቧል።

ሞአዝ የአብደላ ጎረቤት ነው። ወደ እርዳታ ማዕከሉ የሄዱት አብረው ነበር። ረዥም ሰልፍ ስለሚኖር ብዙዎች ማልደው በቦታው ይገኛሉ።

አብደላ ለመጸዳዳት ዘወር ሲል ሞአዝ በሰልፉ ላይ ነበር። ሞአዝ ሰልፍ ሲሰማ እየሮጠ ወደ ጓደኛው አቀና። አብደላ በሕይወት የቆየው ለ10 ደቂቃ ብቻ ነበር።

ዲአ "የጋዛ ነዋሪዎች ሰላማዊ ነን። አብደላ እንደ ሌሎቹ ወጣቶች ነበር። ሕልሙን ሳይኖር ተቀጠፈ። ነፍሱን ይማረው" ይላል።

የእስራኤል መከላከያ ንጹኃን ላይ "ሆነ ብሎ እንደማይተኩስ" ያስተባብላል።

የእርዳታ ማዕከሉ ጠባቂዎችም ንጹኃን ላይ እንደማይተኩሱ ይገልጻሉ።

የአብደላ ታሪክ ቢቢሲ አይ በሠራው ዘጋቢ ፊልም ተካቷል። ፊልሙ 'Gaza: Dying for Food' ይሰኛል።

ፍልስጤማውያን እርዳታ ሲጠባበቁ እንደሚገደሉ በዝርዝር የሚታይበት ዘጋቢ ፊልም ነው። ፊልሙን መሥራት ቀላል አልነበረም።

እስራኤል ቢቢሲን ጨምሮ መገናኛ ብዙኃን ወደ ጋዛ ገብተው በነጻነት እንዲዘግቡ አትፈቅድም።

በጋዛ ያሉ ጋዜጠኞች ሕይወታቸውን ለሞት አሳልፈው ሰጥተው ነው የሚሠሩት። ተመድ እንደሚለው በእስራኤል ጥቃት ቢያንስ 248 ጋዜጠኞች ተገድለዋል።

በእስራኤልና አሜሪካ ጥምረት በሚተዳደረው የሰብአዊ እርዳታ ማከፋፈያ ፍልስጤማውያን ላይ ወታደሮች እንደሚተኩሱ የዐይን እማኞችን በማነጋገር ቢቢሲ መረዳት ችሏል።

እስራኤል ለተወሰነ ጊዜ ጋዜጠኞች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ስትፈቅድ በወታደሮች ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገባቸው ነው። የቢቢሲ ዘጋቢም አንዴ ጋዛ ገብቶ እንደነበር ይናገራል።

እስራኤል ንጹኃን ዜጎችን የመጠበቅ ዓለም አቀፍ ሕግን ጥሳ ንጹኃንን ዒላማ አድርጋለች ተብላ ብትከሰሰም ለቢቢሲ ማብራሪያ የሰጠው ወታደር ይህንን አስተባብሏል።

ወታደሩ "ሐማስ እስራኤል ላይ ጥቃት በመፈጸሙ ሁሉም ፍልስጤማውያን ጥፋተኛ ናቸው። ለምን ሐማስን ሳያስወግዱ ቀሩ" ይላል።

ቢቢሲ መረጃ ለማግኘት ጋዛ ውስጥ ከሚሠሩ ዘጋቢዎች ጋር ይጣመራል። መረጃዎቹኑም ያጣራል። ሆኖም ጋዛ ከሚኖሩ ሰዎች ጋር በቀላሉ መገናኘት አይቻልም።

የአብደላ ታሪክ ከተቀረፀ በኋላ ለንደን እስከሚደርስ ሳምንታት ወስዷል። የእርዳታ ማዕከሎቹ ውስጥ ቀረጻ እንዲካሄድ እስራኤል ፈቃደኛ አልሆነችም።

እስራኤል በጋዛ የስልክ መገናኛ መስመሮች ላይ ጥቃት ስለፈጸች በቀላሉ ሰዎችን ማግኘት አይቻልም። በጋዛ መንቀሳቀስ በአብዛኛው የሚታሰብ አይደለም።

ሞአዝ ጓደኛው ሲገደል አጠገቡ ነበር።

ሪም የተባለችው እናት ለልጆቿ ምግብ ለማግኘት የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም።

ባለቤቷ የጦርነቱ መባቻ አካባቢ ነው የተገደለው። እሱም ምግብ እየፈለገ ሳለ ነበር የተገደለው።

ሪም ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ካደረገች በኋላ ሁለት ልጆቿን ይዛ ከጋዛ ሳትሸሽ አልቀረችም። ለስድስተኛ ጊዜ መፈናቀሏ ነው።

ቶፊክ ኦማር የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ነው። ወደ ዩኬ ከተመለሰ በኋላ በጋዛ በተመለከተው ነገር መረበሹን ይናገራል። ሆስፒታሎች በሰዎች አስክሬን ተጨናንቀው ተመልክቷል። እነዚህ ሰዎች በእርዳታ ማዕከል አቅራቢያ የተገለዱ ናቸው።

"ከእርዳታ ማዕከሎቹ የሚመጡ ሰዎች እንደሚነግሩን ከሆነ የሚተኩሱት የእስራኤል ወታደሮችና የማዕከሉ ጠባቂዎች ናቸው። ቀጥታ ሕዝቡ ላይ ነው የሚተኩሱት" ይላል።

ቢቢሲ በእርዳታ ማዕከላት ስለሚፈጸሙ ግድያዎች ሁለት ውስጥ አዋቂዎችን አነጋግሯል። መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ቢሆኑም ለደኅንነታቸው በመስጋት ማንነታቸው እንዲገለጽ አልፈቀዱም።

የሥራ ባልደረቦቻቸው መረጃ እንዳይሰጡ ቢያስጠነቅቋቸውም ለመናገር ፈቅደዋል።

የእስራኤልና አሜሪካ ጥምር እርዳታ ማዕከሎች 3 ብቻ ናቸው። ተመድ ግን ወደ 400 የሚጠጉ ማዕከሎች ነበሩት።

ማዕከሎቹ የወታደሮች ማቆያ እንደሚመስሉ ከውስጥ አዋቂዎቹ አንዱ ይናገራል። ሁሌም ጥይት ሲተኮስ ይሰማል። ምግብ ለሚሹ ሰዎች እርዳታ የሚቀርብበት ቦታም አይመስልም።

በሚሥጥር የቀረጻቸው ተንቀሳቃሽ ምሥሎች የእስራኤል ወታደሮች ወደተሰበሰበ ሕዝብ ሲተኩሱ ያሳያል። በአንድ ቀን ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

ተንቀሳቃሽ ምሥሎቹ የእስራኤል ወታደሮች ወደተራቡ ሰዎች አነጣጥረው ሲተኩሱ ያሳያሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በአካባቢው ይሰባሰባሉ።

ቢቢሲ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን ከዐይን እማኞች ምስክርነት በተጨማሪ ዘመኑ በደረሰባቸው መተግበሪያዎችና በሳተላየት ምሥሎች በመታገዝ ጥይቶች ከየት አቅጣጫ እንደሚተኮሱ ለመረዳት ችሏል።

አክሌድ የተባለው ተቋም በእርዳታ መስጫ ማዕከላት የተፈጸሙ ግድያዎችን ቁጥር መዝግቧል። ተቋሙ በተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ ዩኬና ሌሎችም የአውሮፓ አገራት ይደገፋል።

በጦር ቀጠና መረጃ የሚሰበስበው አክሌድ እንደሚለው፣ በአሜሪካና እስራኤል ጥምር እዳታ መስጫ ተቋማት ቢያንስ 1,300 ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

አብዛኞቹ የተገደሉትም ከእስራኤል ወታደሮች በተተኮሰ ጥይት ነው። እነዚህ እርዳታ ማዕከላት ከመከፈታቸው በፊትም በመላው ጋዛ እርዳታ የሚጠባበቁ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

እስራኤል በጋዛ ጥቃት መፈጸም ከጀመረች ወዲህ በየወሩ 30 ፍልስጤማውያን ይገደሉ የነበረ ሲሆን አሁን ወደ 500 ከፍ ብሏል።

የእስራኤል መከላከያ ስለእነዚህ ግድያዎች እንደማያውቅና ቁጥሮቹ "እንደተጋነኑ" በመግለጽ ክሱን ያስተባብላል።

ሌላኛው ለቢቢሲ መረጃ የሰጠው የእስራኤል ወታደር ነው። መረጃ አሾልኮ ለማውጣት የተስማማው ወታደር ማንነቱ እንዳይጠቀስ ጠይቋል።

በጋዛ እንዲያደርግ የሚጠየቀው ነገር ምን ከሞራል አንጻር ምን ያህል ተገቢ እንደሆነ ይጠይቃል። ልክ እንደሱ የሚሰማቸው ሌሎችም እስራኤላውያን ወታደሮች አሉ።

እንደሌሎች ወታደሮች አገሩን ለመከላከል ጦርነቱ ውስጥ እንደገባ ያምን የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ኔታንያሁ በሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ ጦርነቱ እንቀጠለ ይሰማዋል።

በፍልስጤም የቀጠለውን የእስራኤል ወረራ የሚቃወሙ የእስራኤል ወታደሮች የተሰባሰቡበት 'ብሬኪንግ ዘ ሳይለንስ' የተባለ ቡድን አባል ነው።

"ንጹኃን ሰዎችን ምን ያህል እንዳዋረድናቸው ማየት ይከብዳል። ምግብ ለማግኘት ይፍጨረጨራሉ" ይላል ወታደሩ።

ለሕዝብ ማስጠንቀቂያ ለመስጠት በእርዳታ ማዕከል አቅራቢያ እንዲተኩሱ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል። እርዳታ የሚቀበሉ ሰዎች መስመር አልፈዋል ሲባል ተኩስ ይከፈታል። የተሰመረ መስመር እንዳለ ግን ለፍልስጤማውያን አልተነገራቸውም።

"አረንጓዴና ቀይ የሚባል መስመር አለ። አረንጓዴ መስመር ላይ ለማስጠንቀቂያ ይተኮሳል። ቀይ መስመር ላይ የሚተኮሰው ጉዳት ለማድረስ ነው" ይላል ወታደሩ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በተሰበሰቡበት መስመር አልፋችኋል ብሎ መተኮስ ወታደሩ እንደሚረብሸው ይናገራል።

"በጣም ያስጨንቀኛል። ተኩሱን ካልሰሙ ወደ እኛ ይሮጣሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ነው የሚተኮሰው።"

የእስራኤል መከላከያ ለዚህ ጉዳይ ምላሽ ባይሰጥም ንጹኃን ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ አሠራር መለወጡን ይገልጻል።

የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክ "እርዳታ ለመውሰድ ሲጠባበቁ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ማስረጃ አለን። በብዛት በእስራኤል ወታደሮች ነው የተገደሉት። ይህ በዓለም አቀፍ ሕግና በሰብአዊ ሕግ ተቀባይነት የለውም" ይላሉ።

እስራኤልን ሲደግፉ የቆዩ ምዕራባውያን መፍትሔ የሚመጣው ሁለት አገራት ጎን ለጎን ሲመሠረቱ ነው ወደሚለው አቋም አዘንብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ዩኬና ፈረንሳይን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ሰጥተዋል። እስራኤል ዕውቅና መስጠትን ለሐማስ "ሽብርተኛነት ድጋፍ ማሳየት" ስትል ነቅፋለች።

እስራኤል በግዳጅ የያዘቻቸው የፍልስጤም ግዛቶች ዓለም አቀፍ ሕግን ይጥሳሉ። እስራኤል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከጋዛ እንዲወጡ ጥቃት ማድረስ ቀጥላለች።

ኔታንያሁ የጋዛ ሰርጥን ለመቆጣጠር የወጠኑት ዕቅድ አካል ነው። አንድ አክራሪ የእስራኤል እንደራሴ የጋዛ ሰርጥን ወደ "ቅንጡ መኖሪያ መገንቢያ" ለመለወጥ ማቀዳቸውን ገልጸዋል።

እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ከፍታለች ተብላ የተከሰሰችው በጥይትና ፈንጂ ብቻ ሳይሆን ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ በመጠቀምም ጭምር ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በድንገተኛ ጊዜ የምግብ አቅርቦት ላይ የተሰማራው ድርጅት በእስራኤል ከበባ ምክንያት የተፈጠረው ረሃብ እየተስፋፋ ነው ይላል።

እስራኤል ፍልስጤማውያንን እንደ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት በመወጠን ከበባውና ጥቃቱን መፈጸሟን ይገልጻል።

እስራኤል የጦር ወንጀል መፈጸሟን ታስተባብላለች። ሐማስን ድል ለመንሳት የተቃጣ ጦርነት ነው በማለትም እስራኤል ትገልጻለች።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በድንገተኛ ጊዜ የምግብ አቅርቦት ላይ የተሰማራው ድርጅት በጋራ ከተማ ረሃብ መስፋፋቱን የሚገልጽ ሪፖርት ያለፈው ነሐሴ ላይ ሲያወጣ እስራኤል ከፍተኛ ጥቃት ለመፈጸም ዝግጅት ላይ ነበረች።

በቋፍ ላይ ባለችው ጋዛ ተጨማሪ ጥቃት መፈጸም ረሃቡን "አሁን ካለውም በላይ" እንደሚያባብሰው ተቋሙ አስጠንቅቋል።