እስራኤላዊቷ እናት፡ 'ልጄ ይኑር ይሙት አላውቅም'

ልጇ በሐማስ የታገተባት እስራኤላዊ እናት ልጇ በሕይወት ይኑር ወይም ይሙት እንደማታውቅ ትናገራለች።

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሰላም ዕቅድ በሐማስ የታገቱ እስራኤላውያንን ያስመልሳል ተብሏል።

ሔሩት ኒማሮዲ ልጇ ታሚር ከታገተ ጀምሮ "ክፉ ይደርስበታል" ብላ እንደምትሰጋ ለቢቢሲ ገልጻለች።

ከታገተ ሁለት ዓመት አልፎታል። "አሁንም በሕይወት አለ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ" ብላለች።

ታሚር በሕይወት ይኑር አይኑር ለቤተሰቡ መረጃ አልተሰጠም። ሌሎች ታጋቾች ያሉበት ሁኔታ ለቤተሰቦቻቸው ቢገለጸም ስለ ታሚር አለመታወቁን እናቱ ትናገራለች።

ትራምፕ ያቀረቡት የሰላም ዕቅድ በአገራት መሪዎች ድጋፍ አግኝቷል። ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት በሐማስ እና እስራኤል መካከል ቀጥለዋል።

ቀጥተኛ ያልሆነው ውይይት የሰላም ዕቅዱ የመጨረሻ ስምምነት ላይ እንዲደረስበት ያስችላል ተብሏል።

የግብፅ እና ፍልስጤም አመራሮች ለቢቢሲ እንደገለጹት ውይይቱ እየተካሄደ ያለው እስራኤላውያን ታጋቾች እና ፍልስጤማውያን እስረኞች የሚለቀቁበትን "መንገድ ለማመቻቸት" ነው።

ሔሩት "ሰላም ለማውረድ ሲሞክሩ ቆይተዋል። ከዚህ ቀደም ባይሳካም የአሁኑ ተስፋ ያለው ይመስላል" ትላለች።

በሕይወት ያሉት ታጋቾችና የሞቱ ታጋቾችን አስከሬን ማስመለስ የሰላም ዕቅዱ የመጀመሪያ ክፍል ነው።

"ይሄ ትልቅ ዜና ነው። እንደ በረከት ነው የምናየው። ታጋቾች በአፋጣኝ መለቀቅ አለባቸው። በሕይወት ያሉትም የሞቱትም። የሞቱት ታጋቾች አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው ተሰጥቶ እርማቸውን ማውጣት አለባቸው" ስትል ሔሩት ትናገራለች።

ታሚር በሐማስ ከታገቱ 47 እስራኤላውያን አንዱ ነው።

እናቱ ለመጨረሻ ጊዜ ያየችው ታግቶ የሚያሳይ ቪድዮ ሲወጣ ነው።

"የመጨረሻ ልጄ ያኔ 14 ዓመቷ ነበር። ኢንስታግራም ላይ ታላቅ ወንድሟ መታገቱን አይታ እያለቀሰች መጣች። ታሚር የሌሊት ልብሱን እንደለበሰ፤ ባዶ እግሩን ነበር። መነጽር ሳያደርግ ማየት ባይችልም መነጽሩ ወልቆ ነበር። መፍራቱ ያስታውቃል።"

በእስራኤል መከላከያ ውስጥ የትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆነው ልጇ ሲታገት 18 ዓመቱ ነበር።

"ልጄ በጂፕ ተጭኖ ወደ ጋዛ ተወሰደ" ትላለች። ከዚያ በኋላ ይኑር ይሙት አታውቅም።

ኔፓላዊው ታጋች ቢፒን ጆሺም ያለበት ሁኔታ አይታወቅም።

የታጋቾች ቤተሰቦች ሕይወታቸው ባለበት እንደቆመ ይናገራሉ።

"ሰዎች ሁለት ዓመት ሙሉ እንዴት አሳለፍሽ ይሉኛል? ሁለት ዓመት መሙላቱ አይሰማኝም። አንድ አታካች ቀን ሆኖ ነው የሚሰማኝ" ስትል ሔሩት ትናገራለች።

ሐማስ ከሁለት ዓመት በፊት 1,200 ሰዎችን ገድሎ 251 ሰዎችን አግቷል። እስራኤል በጋዛ በከፈተችው ጥቃት ከ67,000 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተገልጿል።

ታሚር መታገቱ ሲገለጽ እናቱ ቴል አቪቭ ያለው ቤታቸው አቅራቢያ ነበረች።

ታሚር በወቅቱ በለቀቀው ቪድዮ "በየቦታው ያለማቋረጥ ሮኬት ይተኮሳል" ሲል ይደመጣል።

ወደ ቤት እንደሚመለስ ለእናቱ ቢነግራትም በዚያው ታግቶ ቀረ።

"ራስህን ጠብቅ አልኩት። መልዕክት እንዲልክልኝ ነገርኩት። ለመጨረሻ ጊዜ ይሄንን ነው የተነጋገርነው። ከ20 ደቂቃ በኋላ መወሰዱን ሰማሁ።"

ከሌሎች ታጋቾች ቤተሰቦች ጋር በመሆን ሰላማዊ ሰልፍ እያደረገች ልጇ እንዲለቀቅ ስትጠይቅ ቆይታለች።

"አንዳንድ ቀን ግን ከአልጋዬም መውጣት አልችልም" ትላለች።

የትራምፕ የሰላም ዕቅድ ለታጋቾች ቤተሰቦች ተስፋ ፈንጥቋል።

በቴል አቪቭ እሷን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች ተሰባስበው ድምጻቸውን አሰምተዋል። ታግተው የተለቀቁ ሰዎችም የንቅናቄው አካል ናቸው።

የልጇ ፎቶ ያለበትን ካናቴራ አድርጋ ነው በሰላማዊ ሰልፍ የምትገኘው።

"ትራምፕ ይሄንን የሰላም ዕድል አያሳልፉም ብዬ አምናለሁ" ትላለች።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርጉ" ስትልም ታጋቾች እንዲመለሱ ትማጸናለች።

"ለመተኛት ስሞክር ልጄ ሲታገት የነበረው የፍርሃት ገጽታ ፊቴ ላይ ድቅን ይላል። ለሁለት ዓመት በተስፋ መኖር ያታክታል።"