ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል ግሬታ ተንበርግን እና ሌሎች 170 የጋዛ ተሟጋቾችን ከአገሯ አባረረች
እስራኤል ባለፈው ሳምንት እርዳታ ለማድረስ የጋዛን የባሕር ክልከላ ለመጣስ ሲሞክሩ ተይዘው በእስር ላይ የነበሩትን ስዊድናዊቷን የአየር ንብረት ተሟጋች ግሬታ ተንበርግን እና ሌሎች 170 የፍልስጤም ደጋፊ የመብት ተሟጋቾችን ከአገሯ አባራለች።
ተንበርግ በአቴንስ አየር ማረፊያ በተሰበሰቡ በደርዘን የሚቆጠሩ ደጋፊዎቿ አበባ ሲበረከቱላት መዳፏን ጨብጣ እጇን ከፍ አድርጋለች።
የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አክቲቪስቶቹ ወደ ግሪክ እና ስሎቫኪያ መላካቸውን ገልጸዋል።ከአክቲቪስቶቹ መካከል የግሪክ፣ የስሎቫኪያ፣ የፈረንሳይ፣ የጣሊያን፣ የእንግሊዛዊ እና የአሜሪካ ዜጎች ይገኙበታል ብለዋል።
አክቲቪስቶቹ በእስር ላይ በነበሩበት ወቅት በደል ደርሶባቸዋል፤ መሰረታዊ መብቶቻቸውን ተነፍገው ነበር የሚለውን "የሐሰት ዜና" ውንጀላ በድጋሚ ውድቅ አድርገዋል።
42 ጀልባዎችን ተጠቅመው በስፍራው ከደረሱት 479 ሰዎች መካከል 341ቱ ከአገሪቱ እንዲወጡ መደረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
138ቱ አክቲቪስቶች እስራኤል ውስጥ በእስር ላይ ይገኛሉ። እሑድ ዕለት ከ40 በላይ የሚሆኑት የረሃብ አድማ ላይ መሆናቸው መረጋገጡን የግሎባል ሱሙድ ፍሎቲላ (ጂኤስኤፍኤፍ) ዘገባ አመልክቷል።
ዓላማው "በጋዛ ባሕር ላይ የተጣለውን ሕገወጥ ከበባ መስበር፣ ሰብአዊ ኮሪደር መክፈት እና በፍልስጤም ሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ማስቆም ነው" ብሏል።
የእስር እርምጃዎቹ ዓለም አቀፍ የባሕር እና የሰብዓዊ ሕጎችን የሚጥሱ ናቸው ብሏል።
የእስራኤል ባለስልጣናት በበኩላቸው ሕጋዊ እገዳ ማስተላለፋቸውን እና ጀልባዎቹ በድምሩ ሁለት ቶን እርዳታ ብቻ ስለሚያጓጉዙ ጉዳዩ "የታይታ" ነው ብለውታል።
የግሪክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ተበርግ በእስራኤል ከተባረሩ በኋላ ሰኞ ወደ አቴንስ ከተወሰዱ የ16 የአውሮፓ አገራት 161 ዜጎች መካከል ናት። ስሎቫኪያ 10 ሰዎችን በተለየ በረራ ተቀብላለች።
ስዊዲናዊቷ አቴንስ ከደረሰች በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገረችው ጂኤስኤፍ "የእስራኤል ሕገ ወጥ እና ኢሰብአዊ የባሕር ከበባ ለመስበር የተደረገ ትልቁ ሙከራ ነው።"
"ዓለም አቀፍ አንድነት"
ግሬታ፤ "እኛን ይወክላሉ የተባሉት መንግሥቶቻችን ይህን ማድረግ ሲሳናቸው እና የዘር ማጥፋት፣ ሞትና ውድመትን የሚያቀጣጥሉ መሪዎች ሲሆኑ እኔን አይወክሉኝም የሚሉ ሰዎች ዓለም አቀፋዊ ትብብር ታሪክ ነበር" ብላለች።
"እመኑኝ፣ በእስር ቤት ስለደረሰብን ግፍ እና በደል ለረጅም ሰዓት ማውራት እችል ነበር። ታሪኩ ግን ያ አይደለም" ስትል አክላለች።
እንዲባረሩ ከተደረጉት መካከል አንዱ የሆነው ስፔናዊው የሕግ ባለሙያ ራፋኤል ቦሬጎ እሑድ ምሽት በማድሪድ አውሮፕላን ማረፊያ ለጋዜጠኞች "በተደጋጋሚ የአካል እና የአዕምሮ ጥቃት" እንደደረሰባቸው ተናግሯል።
"ደበደቡን፣ መሬት ላይ እየጎተቱ፣ ዓይኖቻችንን ሸፍነው፣ እጃችንን እና እግራችንን አስረው፣ እስር ቤት ውስጥ አስገቡን እና ሰደቡን" ሲል ከሷል።
እሑድ ወደ ጄኔቫ የተመለሱ ዘጠኝ የስዊዘርላንድ ዜጎችም "ኢ-ሰብዓዊ የእስር ሁኔታ እና አዋራጅ አያያዝ" ነበር ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ዕለት በሰጠው መግለጫ የአክቲቪስቶቹ ሕጋዊ መብቶች "ሙሉ በሙሉ እንደሚከበሩ እና በዚህ መልክ እንደሚቀጥሉ" አፅንኦት ሰጥቶታል።
"የሚረጩት ውሸት ቀድም ብለው ያቀዱት የሐሰተኛ ዜና ዘመቻ አካል ነው" ብሏል።
ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው ሰኞ ዕለት መደበኛ የህክምና ምርመራ ስታደርግ የነበረች የህክምና ባለሙያ በእስር ላይ በነበረች በአንዲት የስፔን ዜጋ እስር ቤት ተነክሳለች ብሏል።
በኋላም ስፔናዊቷ ከአገር እንድትባረር ተደርጋለች። ባለሙያዋ ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባት አክሏል።
የጂኤስኤፍ ጀልባዎች ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ ከባርሴሎና የተነሱት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፈው የተቀናጀ የምግብ ዋስትና ደረጃ ምደባ (አይፒሲ) ባለሙያዎች በጋዛ ከተማ ረሃብ መኖሩን ካረጋገጡ በኋላ።
ረሃቡ በሳምንታት ውስጥ ወደ መሃል እና ደቡብ ጋዛ ሊዛመት እንደሚችልም አስጠንቅቀዋል።
በጋዛ ሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ቢያንስ 460 ፍልስጤማውያን በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ መሞታቸውን ገልጿል። ከእነዚህም መካከል 182 ያህሉ የረሃብ ማስጠንቀቂያው ከወጣ በኋላ መሞታቸውን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስራኤል በጋዛ ላይ የተጣለችውን እገዳ በአስቸኳይ እንድታነሳ እና ሕይወት አድን ቁሶች እንዲገቡ ጠይቀዋል።
አካባቢውን የተቆጣጠረችው እስራኤል በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት በቂ የምግብ እና የህክምና አቅርቦቶች ለጋዛ ሕዝብ እንዲደርሱ ማድረግ አለባት።
እስራኤል በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት እንደምትንቀሳቀስ እና ዕርዳታ እንዲገባ ሁኔታዎችን እንደምታመቻች ገልጻለች።
የአይፒሲ ግኝቶችን እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሩን መረጃም አስተባብሏል። በቅርቡ በተባበሩት መንግስታት የምርመራ ኮሚሽን የቀረበውን እና ጦሩ በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል የሚለውን ውንጀላ አጥብቆ ውድቅ አድርጓል።
መስከረም 26 ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል በተፈፀመው ጥቃት 1,200 ሰዎች ሲገደሉ 251 ሌሎች ደግሞ ታግተዋል። የእስራኤል ጦር በምላሹ በጋዛ ጦርነት ከፍቷል።
የግዛቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደገለፀው ከሆን ከጦርነቱ መጀመር ጊዜ ጀምሮ እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ጥቃት ቢያንስ 67,160 ሰዎች ተገድለዋል።