ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፍልስጤም ደጋፊዎችን አሳፍራ ወደ ጋዛ የምታቀናው መርከብ በድሮን መመታቷን አዘጋጆቹ ተናገሩ
ታዋቂዋ ግሬታ ተንበርግን ጨምሮ የፍልስጤም ደጋፊዎችን አሳፍራ ወደ ጋዛ የምታቀናው ፍሎቲላ የተሰኘችው መርከብ በድሮን መመታቷን አዘጋጆቿ ተናገሩ።
መሰረታዊ የሚባሉ ዕርዳታዎችን የጫነችው መርከብ እስራኤል "በጋዛ ላይ የጣለችውን ከበባ የመስበር" ተልዕኮን አንግባለች።
የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው በቱኒዝያ ሲዲ ቦው ወደብ እንደሆነም የጉዞው አዘጋጆች ግሎባል ሱሙድ ፍሎቲላ (ጂኤስኤፍ) አስታውቋል።
የፖርቹጋል ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበች የነበረችው ይህች መርከብ ስትመታ የሚያሳይ ቪዲዮ በኢንስታግራም ያጋሩ ሲሆን ስድስቱም ተሳፋሪዎች እንዲሁም የበረራ ሰራተኞች በደህንነት ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል።
የቱኒዝያ ባለስልጣናት በበኩላቸው መርከቧ በድሮን ተመትታለች መባሏን "መሰረት የለውም" ሲሉ ማጣጣላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የመጀመሪያ ምርመራ የሚያሳየው የፍንዳታው መነሻ ከመርከቧ ውስጥ መሆኑን ማመላከታቸውን ዘገባው አክሏል።
የሰብዓዊው እርዳታ የጫነችው ፎሎቲላ ባለፈው ሳምንት ከባርሴሎና ተነስታ ቱኒዝያ የደረሰችው እሁድ ዕለት ነበር።
መርከቧ በቱኒዝያ የውሃ ክልል ውስጥ በድሮን መመታቷን እና በተቀሰቀሰው እሳት ወለሉ ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።
አዘጋጆቹ በተከታታይ በኢንስታግራም ባወጧቸው ቪዲዮዎች በመርከቧ ላይ ተቀጣጣይ መሳሪያ እሳት መነሳቱን ሰራተኞቹ እሳቱን ማጥፋት መቻላቸውን ገልጸዋል።
የቱኒዝያ ብሔራዊ ጥበቃ ቃል አቀባይ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የድሮን ምልክቶች አለመገኘታቸውን ጠቅሰው ምርመራው ቀጥሏል ብለዋል።
የተባበሩትን መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ልዩ መልዕክተኛ እና የቱኒዝያ ነዋሪ የሆኑት ፍራንቼስካ አልባኔዝ የድሮን ጥቃቱ ከተረጋገጠ "በቱኒዝያ እንዲሁም በአገሪቷ ሉዓላዊነትን የጣሰ ጥቃት ነው" ማለታቸው በጂኤስ ኤፍ በተጋራ ቪዲዮ ተናግረዋል።
ልዩ መልዕክተኛዋ ሲዲ ሳይድ ወደብ ላይ እንዳሉ እና ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር በመሆን እውነታውን ለማወቅ እየጣሩ መሆኑን በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
እስራኤል በጋዛ የምታደርገው ጦርነትን በሰላ በመተቸት የሚታወቁት አልባኔዝ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ማይክሮሶፍት እና አማዞንን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከእስራኤል ጋር የሚያደርጉትን የንግድ ግንኙነት እንዲያቆሙ ከዚህ ቀደም መጠየቃቸው ይታወሳል።
ኩባንያዎቹ ከእስራኤል ጋር የንግድ ሽርክና በመቀጠል በጋዛ እና እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ እየተፈጸሙ ባሉ የጦር ወንጀሎች ተባባሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ባለሙያዋ ፍራንቼስካ አልባኔዝ አስጠንቅቀዋል።
ለተባበበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት አልባኔዝ "የዘር ማጥፋት ኢኮኖሚ" ሲሉ ጠርተው የጋዛ ጦርነት ምንም አይነት ተጠያቂነት እና ቁጥጥር ሳይደረግበት ለአዳዲስ መሳሪያዎች እና ቴክኖሎጂዎች መሞከሪያ ሆኗል ብለዋል።
እስራኤል የባለሙያዋን ሪፖርት "መሰረተ ቢስ" በማለት ውድቅ አድርጋ "የታሪክ ቆሻሻን ይቀላቀላል" ብላለች።
በዚህ የጠነከረ አቋማቸው አሜሪካ በባለሙያዋ ላይ ማዕቀብ ጥላባቸዋለች።
አዘጋጆቹ የዚህ ተልኳቸው ዓላማ "እስራኤል በጋዛ ላይ የጣለችውን ህገወጥ ከበባ መስበር" እንደሆነ የገለጹ ሲሆን በርካታ ተግዳሮቶች እያጋጠማቸው ይገኛል።
ከዚህ ቀደም ስዊድናዊቷ ተሟጋች ቱንበርግን ጨምሮ 12 የፍልስጤም ደጋፊዎች ሰብዓዊ እርዳታን ጭነው ወደ ጋዛ እያቀኑ በነበረበት ወቅት እስራኤል በቁጥጥር ስር አውላ ከአገር ማባረሯ ይታወሳል።
እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዳይደርሳቸው ከመጋቢት ጀምሮ ሙሉ እገዳ ጥላለች። ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎ በጋዛ የማያባራ ጥቃት እያካሄደች ነው።
የእስራኤል ጦር ይሄንን ሁሉ የሚያደርገው ሐማስ የቀሩ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ ነው ይላል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ በተደጋጋሚ ማሰማቱን ተከትሎ እገዳው በከፊል ቢላላም አሁንም ፍልስጤማውያኑ በከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት እየተፈተኑ ነው።
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተወሰኑ የእርዳታ መኪኖች በተጨማሪ፤ እስራኤል እና አሜሪካ ለፍልስጤማውያን እርዳታ እናከፋፍላለን በሚል 'የጋዛ ሂውማኒታሪያን ፋውንዴሽን' (ጂኤችኤፍ) የተሰኘ አወዛጋቢ ድርጅት አቋቁመዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እርዳታ ሲጠባበቁ ባሉ ፍልስጤማውያን ላይ በየቀኑ በሚባል ሁኔታ የእስራኤል ጦር በሚከፍተው ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
በባለፉት ሁለት ወራት የእስራኤል ጦር በእርዳታ ጠባቂ ፍልስጤማውያን ላይ በከፈተው ተኩስ ከ1,000 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ አስታውቋል።
ከእነዚህ ውስጥም 766 ግድያዎች የተፈጸሙት በጋዛ የሰብዓዊ ፋውንዴሽን ግቢ ውስጥ ነው።
ቀሪዎቹ 288 ፍልስጤማውያን ደግሞ የተገደሉት የተፈጸሙት በተባበሩት መንግሥታት እና በሌሎች የእርዳታ መኪኖች አቅራቢያ ነው።