የእስራኤል ቀኝ አክራሪ ሚኒስትሩ ታዋቂውን ፍልስጤማዊ ፖለቲከኛ እስረኛ ሲያስፈራሩ ታዩ

የእስራኤል ቀኝ አክራሪ ሚኒስትር ኢታማር ቤን ግቪር ከ20 ዓመት በላይ በእስር ያለውን ታዋቂውን ፍልስጤማዊ ፖለቲከኛ ማርዋን ባርጋሃውቲ በእስር ቤት ሄደው ሲያስፈራሩት የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያ ወጥቷል።

ሚኒስትሩ በእስር ቤት ሄደው ያደረጉትን ማንጓጠጥ እና ማስፈራራት የፍልስጤም አስተዳደር በጽኑ አውግዞታል።

የአስተዳደሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሁሴን አል ሼክ ይህ "የስነ ልቦና፣ የሞራል እና የአካል ሽብርተኝነት መገለጫ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።

ይህ የ13 ሰኮንድ ርዝመት ያለው ቪዲዮ ማርዋን ከዓመታት በኋላ በይፋ የታየበት ነው።

ፖለቲከኛው ሰውነቱ ጠውልጎ፣ ከስቶ እና ከሳስሞ ታይቷል።

የእስራኤል ብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ቤን ጊቪር ለፍልስጤማዊው እስረኛ "አታሸንፍም። ከእስራኤል ህዝብ ጋር የሚጣላ፣ ልጆቻችንን የሚገድል፣ ሴቶቻችን የሚገድል ከምድረ ገጽ እናጠፋዋለን" ሲሉ ነግረውታል።

ማርዋን በለሆሳስ ድምጽ ጣልቃ ለመግባት ሲሞክርም፤ ቤን ጊቪር ጮክ ባለ ድምጽ "ይህ በታሪክ ሁሉ ስለመሆኑ ማወቅ አለብህ" ሲሉ አቋርጠውት ሲናገሩ ታይተዋል።

የ66 አመቱ ፖለቲከኛ ከ20 ዓመታት በላይ በእስር ያሳለፈ ሲሆን እስራኤል አምስት ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት አቀነናብሯል በሚል ነው ለእስር ያበቃችው።

በዚህም አምስት የእድሜ ልክ እና 40 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።

የህዘብ አስተያየት መስጫዎች እንደሚያሳዩት ማርዋን በፍልስጤማውያን ዘንድ በጣም ተወዳጅ መሪ መሆኑን ነው።

ምርጫ ቢደረግ ፍልስጤማውያን በአሁኑ ወቅት ካሉት የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ ሆነ የሐማስ መሪዎች አስቀድመው ማርዋንን በፕሬዚዳንትነት እንደሚመርጡት እነዚህ የህዝብ አስተያየቶች አመላክተዋል።

የፍልስጤምን አስተዳደር የተቆጣጠረው የፋታህ መሪም ተደርጎ ይታያል።

በአውሮፓውያኑ 2000- 2005 በተካሄደው ሁለተኛው የፍልስጤም ኢንቲፋዳ (ህዝባዊ አመጽ) ማርዋን ባሳየው መሪነት እስራኤል ኢላማ አድርጋዋለች።

የፍልስጤም አስተዳደር ወገዛን ተከትሎ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ "ደግሜ ደጋግሜ እለዋለሁ" ብለዋል።

ሐማስ በደቡባዊ እስራኤል የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ማርዋን ለብቻው እንዲታደሰር መደረጉን የፍልስጤም እስረኞች መብት ተሟጋች ድርጅት አስታውቋል።

የእስር ቤት ጠባቂዎች በፖለቲከኛው ላይ "አሰቃቂ ጥቃት" እንደፈጸሙበት የተገለጸ ሲሆን የእስራኤል የእስር ቤት አገልግሎት ይህንን አስተባብሏል።

ሚኒስትሩ ወደ እስር ቤት ሄደው ማርዋንን የሚያስፈራሩበትን ቪዲዮ አስመልክቶ የፍልስጤም ታሳሪዎች ማህበር ኃላፊ አብዱላህ አል ዛጋሪ እስራኤል፤ "ማርዋንን ጨምሮ በእስር ቤቶቿ እየማቀቁ ያሉ መሪዎችን ለመግደል ትፈልጋለች" ብለዋል።

ሐማስ የያዛቸውን ቀሪ ታጋቾች በእስራኤል እስር ቤቶች ባሉ ፍልስጤማውያንን ለመቀያየር የሚፈልግ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ አንዱ ማርዋን ነው።

ሆኖም እስራኤል ይህንን ፖለቲከኛ ትለቀዋለች ተብሎ የሚታሰብ አይደለም።

የማርዋን ባለቤት ፋድዋ ለተከታዮቹ ባስተላለፈችው መልዕክት ከቪዲዮው መውሰድ ያለባቸው ጥንካሬውን የሚያሳየውን ነው ብላለች።

ማርዋን በፍልስጤም ያሉ የተለያዩ ፖለቲከኞችን አንድ ላይ በማምጣት ወደ ድርድር መምጣት የሚችል መሪ እንደሆነ ፍልስጤማውያኑ ያምናሉ።

እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል አልፈጸምኩም ብትልም የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ጨምሮ እስራኤል በጋዛ ጦርነት እየፈጸመችው ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ይላሉ።

እስራኤል በአገርነት፣ በአውሮፖውያኑ 1948 ስትመሠረት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያንን ያፈናቀለች ሲሆን፣ ይህንንም "ናቅባ" (ታላቁ እልቂት) ሲሉ ይጠሩታል።

በአሁኑ ወቅትም ፍልስጤማውያኑ ይኸው ይደገማል በሚል ፍራቻ ላይ ናቸው።

ከቀያቸው የተፈናቀሉት ፍልስጤማውያኑ አብዛኞቹ በጋዛ ሰፍረዋል።

በአሁኑ ወቅት ካሉ የጋዛ ነዋሪዎች መካከል ሦስት አራተኛውን የሚይዙት በዚያን ወቅት የተፈናቀሉ የልጅ ልጆች ናቸው።

ሌሎች 900 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ አሁን እስራኤል በኃይል በያዘቻት ዌስት ባንክ ይኖራሉ።

በተጨማሪም 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ፣ በሶሪያ እና በሊባኖስ እንደሚኖሩ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።

እስራኤል በአውሮፓውያኑ 1967 በተደረገው የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ነው የፍልስጤማውያኑ ግዛት የሆኑትን ዌስት ባንክ እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠረችው።

ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ለ700 ሺህ አይሁዳውያን መኖሪያ የሚሆኑ 160 ሰፈራዎችን ገንብታለች። በዌስት ባንክ 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማውያን ይኖራሉ።

አብዛኛው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል እያደረገችው ያለውን ሰፈራ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሕገወጥ ነው ሲል ይኮንናል።

እስራኤል ይህንን አትቀበልም።

በእስራኤል በተከታታይ የመጡ አስተዳደሮች ሰፈራዎች እንዲስፋፉ አድርገዋል።

ይሁን እንጂ ሰፈራን የሚደግፈው የቅኝ ክንፍ አክራሪ ጥምረት የሆነውን መንግሥት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድጋሚ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ሰፈራዎች እየተስፋፉ ይገኛሉ።

የጋዛ ጦርነትም እንዲሁ ለእነዚህ ሰፈራዎች መጨመር በር መክፈቱም ተነግሯል። ሰፈራዎች መስፈፋት ብቻ ሳይሆን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያኑ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች መባባሱም ተገልጿል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከሆነ የጋዛ ጦርነት ከተነሳ ጀምሮ በዌስት ባንክ ቢያንስ 975 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጸጥታ ኃይሎች እና በእስራኤል ሰፋሪዎች ተገድለዋል።