ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል እና ሐማስ ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ ወደ ሰላም ይመጡ ይሆን?
ከሁለት ዓመት ጦርነት በኋላ በጋዛ ያለውን ግድያ እና ውድመት የሚያስቆም እና በሕይወት ያሉ እና የሞቱ እስራኤላውያን ታጋቾች ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚመልስ የሰላም ስምምነት ዕድል በደጃፍ ነው።
ይህ ዕድል ነው፤ ነገር ግን በሐማስም ሆነ በእስራኤል ተቀባይነት ማግኘት እንደሚችል ማንም እርግጠኛ አይደለም።
ሐማስ በእስራኤላውያን ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰበት ሁለተኛ ዓመት በሚታሰብበት ዕለት ውይይቱ እየተካሄደ መሆኑ አሳዛኝ አጋጣሚ ነው።
የመስከረም 26 2016 ዓ.ም. ጥቃት ወደ 1,200 የሚጠጉ ሰዎች የገደለ ሲሆን 251 ያህሉ ደግሞ ታግተዋል።
እስራኤላውያን 20 ታጋቾች በሕይወት እንዳሉ የሚያምኑ ሲሆን የቀሪዎቹ 28 ሰዎች ደግሞ አስከሬናቸውን ለመረከብ ይፈልጋሉ።
የእስራኤል መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ አብዛኛውን ጋዛ ያወደመ ሲሆን ከ66,000 በላይ ፍልስጤማውያንን ገድሏል።
ከሟቾቹ መካከል አብዛኛው ሰለማዊ ዜጎች እና ከ18,000 በላይ ደግሞ ሕጻናት ናቸው።
ይህ የቁጥር መረጃ የተገኘው የሐማስ አስተዳደር አካል ከሆነው የጤና ሚኒስቴር ነው።
ከሚኒስቴሩ የሚገኘው አሃዝ ብዙውን ጊዜ እንደ አስተማማኝ መረጃ ተደርጎ ይቆጠራል።
መቀመጫው ለንደን የሆነው የሕክምና መጽሔት፣ ዘ ላንሴት ላይ የሰፈረ ጥናት የሟቾቹ ቁጥር ዝቅ ተደርጎ እንደተገመተ አመልክቷል።
እስራኤላውያንም ሆኑ ፍልስጤማውያን ጦርነቱ እንዲያበቃ ይፈልጋሉ።
እስራኤላውያን በጦርነት ደክመዋል እናም አብዛኛው ሰው ታጋቾችን የሚመልስ እና ጦርነቱን የሚያስቆም ስምምነት እንዲደረግ እንደሚፈልጉ የተሰበሰቡ የሕዝብ አስተያየቶች ያሳያሉ።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በእስራኤል ጦር ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ተጠባባቂ ኃይሎች ለረዥም ወራት በጦርነት ውስጥ ሲሳተፉ ከቆዩ በኋላ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ ይፈልጋሉ።
በጋዛ ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጦር ጥይት፣በረሃብ እና ወደ ሰርጡ የሚገባን ማንኛውም እርዳታ ማገዷን ተከትሎ በተፈጠረ ሰው ሰራሽ ድርቅ የተነሳ በሰብዓዊ አደጋ ውስጥ ይገኛሉ።
እስራኤልን በአውዳሚ ኃይል ማጥቃት የቻለው ሐማስ ከሁለት ዓመት የማያባራ ወታደራዊ ዘመቻ በኋላ ተሰብሯል።
በፍርስራሾች መካከል የደፈጣ ውጊያ የሚያካሂድ የከተማ ሽምቅ ተዋጊ ኃይል ሆኗል።
ቡድኑ ለፍልስጤም ምሑራን ሥልጣን ለማስረከብ ቢስማማም፣ ሐማስ እስትንፋሱን የሚያቆይበት መንገድ መፈለጉ አይቀርም።
የተረፉትን ከባድ መሳሪያዎቹን ማስረከብ ወይም ማውደም እንዳለበት ቢቀበልም፣ ለሁለት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በጭካኔ አገዛዙ የደቆሳቸው ፍልስጤማውያን በቀል እንዳይፈጽሙበት ራሱን ለመከላከል የሚያስችል በቂ ጦር መሣሪያ መያዝ ይፈልጋል።
በእርግጥ ይህንን በአደባባይ ባይለውም አሁንም ተከታዮች ያሉት ድርጅት እና እስራኤልን ለማጥፋት የሚጥር ታጣቂ በመሆኑ ስሙን ጠብቆ ለመቆየት የሚያስችለው እና ዳግም ራሱን ማደራጀት አቅም የሚሰጠው መሣሪያ ያስፈልገዋል።
እስራኤል በበኩሏ ሐማስ እጅ የሚሰጥበትን መንገድ መቀመር ትፈልጋለች። ነገር ግን ሐማስ የዛሬ ወር ከነበረው ይልቅ ጠንካራ ድርድር ለማካሄድ እና በርካታ ዕድሎችን ለመክፈት አጋጣሚዎቹ ያሉት ይመስላል።
እስራኤል በዶሃ ትራምፕ ያቀረቡትን የሰላም ሃሳብ ላይ ለመወያየት ተገናኝቶ የነበረውን የሐማስን ዋነኛ ተደራዳሪ ለመግደል ያልተሳካ እርምጃ ከወሰደች በኋላ ሁኔታዎች ተለውጠዋል።
በወቅቱ ዋና ዒላማዋ የነበረው የሐማስ ተደራዳሪዎችን ይመራ የነበረው ከፍተኛ አመራሩን ካህሊል አል-ሀያን መግደል ነበር።
ምንም እንኳን ዋነኛ የሐማስ ተደራዳሪዎች ከእስራኤል ጥቃት ቢያመልጡም የአል-ሀያ ልጅ ግን ከሟቾች መካከል አንዱ ነው።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በአእምሮአቸው የተለየ ራሳቸውን ከዚህ ሁሉ ውስብስብ ውስጥ የሚያወጡበት አማራጭ አላቸው።
ሥልጣናቸውን ማስጠበቅ፣ በሙስና ወንጀል የተከሰሰቡበትን ክስ ለሌላ ጊዜ ማራዘም፣ በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄደውን ምርጫ ማሸነፍ እና ከናዚ ጭፍጨፋ በኋላ በአይሁዶች ላይ እጅግ የከፋ ሞት ያስከተለው የጸጥታ ስህተት መሪ ሆኖ በታሪክ ውስጥ ላለመመዝገብ ይፈልጋሉ።
ይህንንም ለማሳካት ደጋግሞ አስተማማኝ "ጠቅላላ ድል" ለማወጅ ተዓማኒ የሆነ መንገድ ያስፈልጋል።
ኔታንያሁ ይህንን የታጋቾቹ መመለስ፣ የሐማስ መጥፋት እና ጋዛን ከወታደራዊ ቀጠናነት ነጻ ማውጣት ሲሉ ያስቀምጡታል።
ይህን ማድረግ ካልቻሉ እስራኤል ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በሊባኖስ እና በኢራን በጠላቶቿ ላይ ያደረሰችውን ትክክለኛ ጉዳት ለማመልከት በቂ አይሆንም።
የሐማስ እና የእስራኤል ተደራዳሪዎች ፊት ለፊት አይገናኙም።
የግብፅ እና የኳታር ባለሥልጣኖች አሸማጋዮች ይሆናሉ። እናም እዚያ የሚገኙት አሜሪካውያን ትልቅ ተጽእኖ ምናልባትም ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል።
በሐማስ እና እስራኤል መካከል የሚደረገው ንግግር መሠረቱ ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡት ባለ 20 ነጥብ የጋዛ የሰላም ዕቅድ ነው።
ፕሬዚዳንቱ በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ስለ ዘላቂ ሰላም የሚለጥፉ ቢሆንም፣የማያደርጉት ነገር ቢኖር በዮርዳኖስ ወንዝ እና በሜዲትራኒያን ባህር መካከል ያለውን መሬት ለመቆጣጠር በሚል በእስራኤላውያን እና በፍልስጤማውያን መካከል ያለውን የረዥም ጊዜ ግጭት ማስቆም ነው።
የፕሬዚዳንቱ ዕቅድ የዌስት ባንክን የወደፊት ዕጣ ፈንታም አይጠቅስም። ዩናይትድ ኪንግደም እና ሌሎች ግን እንደ ፍልስጤም ግዛት እውቅና ሰጥተዋል።
በሻርም ኤል ሼክ የሚኖረው ድርድር ከፍተኛ ውጥረት የተሞላበት ነው።
በአረቦች እና በአይሁዶች መካከል ከመቶ ዓመት በላይ የዘለቀውን እጅግ አውዳሚ እና ደም አፋሳሽ ጦርነትን ለማስቆም የሚችል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ዕድሉ አለ።
የመጀመርያው ፈተና እስራኤላውያን ታጋቾችን ማስለቀቅ ይሆናል።
በምትኩ ደግሞ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያለፍርድ ተይዘው በእስር ላይ የሚገኙ እና የእድሜ ልክ እስራት የሚቀጡ ፍልስጤማውያንን ማስለቀቁም ቀላል ስራ አይደለም።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በፍጥነት ውጤት ይፈልጋሉ።
በመካከለኛው ምሥራቅ ታላቅ ድርድር ለማድረግ ያላቸውን ፍላጎት ማደስ ይፈልጋሉ።
በዚህ መሃል በእስራኤል እና በሳዑዲ አረቢያ መካከል መቀራረብ ይሆናል።
እስራኤል በጋዛ እጅግ በጣም ብዙ የፍልስጤም ሰላማዊ ዜጎችን እየገደለች እና የሰብዓዊ እርዳታ ላይ እገዳ እየጣለች እንዲሁም ሐማስ እስራኤላውያንን አግቶ ይህ ሊሆን አይችልም።
ሳዑዲዎችም ፍልስጤም ነጻ የሆነች አገርን ለማምጣት ግልፅ እና የማይቀለበስ መንገድ ከሌለ ይህ ሊሆን እንደማይችል በተከታታይ ባወጡት ይፋዊ መግለጫዎች በግልፅ ተናግረዋል።
ትራምፕ ኔታንያሁ የፍልስጤም ነጻ አገርነትን ዕድል የሚያመለክት ግልጽ ያልሆነ እና አሻሚ ሃሳብን የያዘ ሰነድ ላይ እንዲፈርሙ አስገድዷቸዋል።
ኔታንያሁ በኋላ በሰጡት መግለጫ ፍልስጤማውያን መቼም ቢሆን አገር አይሆኑም በማለት የፈረሙትን ሰነድ ላይ የሰፈረውን ሃሳብ ችላ ማለትን መርጠዋል።
በትራምፕ ሰነድ ውስጥ እስራኤል ሐማስ ሙሉ በሙሉ ከመጥፋቱ እና የወደፊቷ የጋዛ አስተዳደር ውስጥ ካለመኖሩ ባሻገር የምትፈልገው ብዙ ነገር አለ።
ኔታንያሁ በኦቫል ኦፊስ ውስጥ የሚፈልጉትን የማግኘት ልምድ ያላቸው ቢሆንም አሁን ግን ትራምፕ የሐማስ አመራርን ለመግደል በዶሃ ለፈጸሙት የአየር ጥቃት ለኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር መደበኛ ይቅርታ የጠየቁበትን ደብዳቤ እንዲያነቡ አድርገዋቸዋል።
ትራምፕ መካከለኛው ምሥራቅን እንደገና ለመፍጠር ያላቸውን ፍላጎት ወደፊት ለማራመድ ኳታርን በዋነኛነት ይፈልጓታል።
አንዱ ጥያቄ ሐማስ እስራኤል ጋዛን ለቅቃ የምትወጣበት እና ጦርነቱን የምታቆምበት የጊዜ ሰሌዳ ሳይመለከት ታጋቾቹን ለመልቀቅ ለምን ተዘጋጀ? የሚል ነው።
አንደኛው አማራጭ ኳታራውያን ትራምፕ ታጋቾቹን፣ በሕይወት ያሉ እና የሞቱትን በሙሉ በማስለቀቅ ድል ማድረጋቸውን እንዲያውጁ ዕድል ካገኙ እስራኤልጋዛን ለቅቃ እንድትወጣ ማድረግ እና ጦርነቱን እንድታቆም ማስገደድ አይሳናቸውም ብለው አሳምነዋቸው ሊሆን ይችላል።
ያም ሆኖ ትራምፕ አሁንም ኔታንያሁ እና እስራኤላውያን እንዲሰሙት የሚፈልጓቸውን ቋንቋዎች እየተጠቀሙ ነው።
ሐማስ ስምምነቱን ውድቅ ካደረገ የሚደርስበትን ጥቃት በመግለጽ ሲያስፈራሩ፣ እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት እርምጃ እንድትወስድ "ሙሉ ድጋፍ" እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ሐማስ ቆራጥ ከሆነ ለመስማማት ጥቂት ቀናት ብቻ እንደሚፈጅ ተናግረዋል።
ውስብስብ ስምምነትን ለመደገፍ የሚያስፈልጉ ጥቃቅን ነገሮችን መስመር ለማስያዝ ብዙ ጊዜ ይወስዳል። እስካሁን ተደራዳሪዎቹ በእጃቸው ያለው ነገር የትራምፕ የሰላም ዕቅድ ብቻ ነው።
ስምምነቶችን የመፈጸም ችሎታን በተመለከተ ከትራምፕ ከራሳቸው በላይ ማንም የላቀ አስተያየት ያለው የለም። በውጭ ፖሊሲ ውስጥ፣ እስካሁን ድረስ የተገኘው ከፉከራዎቻቸው ጋር አይጣጣምም።
ትራምፕ እንደሚናገሩት ብዙ ጦርነቶችን አላስቆሙም።
ትራምፕ እንደተነበዩት የሩስያ እና የዩክሬን ጦርነትን በአንድ ቀን ውስጥ አላስቆሙም ። ነገር ግን ትራምፕ ያላቸው አንድ ክህሎት፣ በሪል እስቴት ውስጥ ረዥም ዓመት እንደማሳለፋቸው፣ የሚፈልጉትን ለማግኘት እንዴት ተጽዕኖ መፍጠር እንዳለባቸው ማወቃቸው ነው።
በግብፅ እየተካሄደ ያለው ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር መሆን የቻለው ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱም ወገኖች ላይ ጫና መፍጠር በመቻላቸው ነው።
ሐማስን በእቅዱ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ካልሆነ የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠበት ማስፈራራት ቀላል ነገር ነበር።
ቡድኑ እአአ በ2006 ምርጫ ካሸነፈ ጊዜ እና ከተቀናቃኙ ፋታህ ጋዛን በ2007 ከነጠቀ በኋላ የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ዓለም አቀፍ ጫናን ሐማስ ላይ ሲያካሄዱ ቆይተዋል።
በዶናልድ ትራምፕ እና ክሊንተን፣ኦባማ እና ባይደን መካከል ያለው ትልቅ ልዩነት ቤንያሚን ኔታንያሁ እርሳቸውን ለመሸወድ ለሚያደርጉት ሙከራ ጠንከር ያለ ምላሽ መስጠታቸው ነው።
ትራምፕ ላቀረቡት የሰላም ዕቅድ ሐማስ የሰጠውን "አዎ፤ግን" ምላሽ እንደ ተቀበለው አድርገው ወስደውታል።
አክሲዮስ የዜና አገልግሎት እንደዘገበው ኔታንያሁ ሐማስ ጊዜ እየገዛበት መሆኑን ለማሳመን ቢሞክሩም የትራምፕ ምላሽ "ለምንድን ነው አሉታዊ የሆንከው" የሚል ነበር።
እስራኤል የዩናይትድ ስቴትስ ጥገኛ ነች። አሜሪካ በጦርነቱ ውስጥ ሙሉ አጋር ነች። ያለ አሜሪካዊ እርዳታ እስራኤል ጋዛን በዚህ መጠን ያለ ርህራሄ እና ረዥም ጊዜ ልታጠቃ አትችልም ነበር።
አብዛኛው የጦር መሳሪያዎቿ በአሜሪካ የሚቀርቡ ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትም እስራኤል ጦርነቱን እንድታቆም ጫና ለመፍጠር የተደረጉ ውይይቶችን እና የተላለፉ በርካታ ውሳኔዎችን በመቃወም የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ከለላን የምትሰጠው አሜሪካ ናት።
ሐማስም ሆነ እስራኤል ጦርነቱ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ጠንካራ ተቺዎች አሏቸው።
የሐማስ ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት አሁንም በጋዛ የሚገኙት ወታደራዊ አዛዦች እስከመጨረሻው ለመውጋት እና በተቻለ መጠን ታጋቾቹን ይዘው ለመቆየት ተዘጋጅተዋል።
የቤንያሚን ኔታንያሁ ጥምረት ፍልስጤማውያን ከጋዛ ማባረር እና በአይሁድ ሰፋሪዎች መተካት ለሚለው ሕልማቸው መሳካት ቅርብ እንደሆኑ በሚያስቡ እጅግ በጣም ብሄራዊ ጽንፈኞች ድጋፍ ላይ የተመሰረተ ነው።
በግብፅ ያለው ውይይት ካልተሳካ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች የመጨረሻ የሚሉትን እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ።