ቢቢሲ እና ሶስት የዜና ወኪሎች እስራኤል የውጭ ጋዜጠኞችን ወደ ጋዛ እንድታስገባ የሚጠይቅ ፊልም ለቀቁ

ቢቢሲ እና ሶስት ዓለም አቀፍ የዜና ወኪሎች እስራኤል የውጭ ጋዜጠኞች ወደ ጋዛ እንዲገቡ እንድትፈቅድ የሚጠይቅ አጭር ፊልም አሰራጩ።

የፈረንሳዩ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ)፣ አሶሼትድ ፕሬስ (ኤፒ) እና ሬውተርስ የዜና የለቀቁት ይህ ፊልም፤ በአንጋፋው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ዴቪድ ዲምብልቢ የተተረከ ነው።

የፊልሙ ተራኪ ዴቪድ፤ በ1977 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የተከሰተውን ርሃብ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ይፋ ያደረገውን ዘገባ ያዘጋጀው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ጆናታን ዲምብልቢ ወንድም ነው።

ጋዜጠኛው፤ "በፍልስጤማውያን ዘጋቢዎች ላይ የተጫነውን ሸክም ተጋርተን እውነታውን ለዓለም ማቅረብ እንድንችል ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች አሁን ወደ ጋዛ እንዲገቡ መፈቀድ አለበት" ብሏል።

ሀማስ በመስከረም 2016 ዓ.ም. የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ዘመቻ ከጀመረች ወዲህ የውጭ አገር ጋዜጠኞች በገለልተኝነት ወደ ጋዛ እንዳይገቡ ከልክላለች። የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞች በእስራኤል ቁጥጥር ስር ወደሚገኝ የጋዛ ሰርጥ አካባቢ ተወስደው ነበር።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ ጋዜጠኞች ወደ ጋዛ በመግባት "ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲዘግቡ ለመፍቀድ" ሲባል ወታደሮች "በጦር ሜዳዎች ላይ እንዲያጅቧቸው" እንደሚደረግ ከዚህ ቀደም ተናግሯል።

የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ከደህንነት ጋር በተያያዘ ጋዜጠኞች ላይ የተጣለው እገዳ ምክንያታዊ እንደሆነ ባሳለፈነው ዓመት ውሳኔ አሳልፏል።

የቢቢሲ ኒውስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዲቦራ ተርነስ፤ "ዓለም በመስከረም 26 የሀማስን ግፍ ከተመለከተ ሁለት ዓመት ገደማ ሆኖታል። ከዚያ ወዲህ በጋዛ ጦርነት ተፋፍሟል፤ ጋዜጠኞች ግን እንዲገቡ አልተፈቀደላቸውም" ብለዋል።

"በዚያ ካሉ ጋዜጠኞች ጋ በጋራ በመስራት እውነታውን ለዓለም እንድናደርስ አሁን ወደ ጋዛ መግባት አለብን" ሲሉም አክለዋል።

በአራቱ መገናኛ ብዙኃን የተዘጋጀው አጭር ፊልም ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) ባዘጋጀው አንድ ሁነት ላይ ይቀርባል። ፊልሙ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በሚካሄድበት ተመሳሳይ ሰዓት እንዲቀርብ እንደሚደረግም ተገልጿል።

ፊልሙ በጋዜጠኞች የተቀረጹ ታሪካዊ ክስተቶችን እና የግፍ ድርጊቶችን ምስሎች ያካተተ ነው። የ1977ቱን የኢትዮጵያ ርሃብ፣ የቪየትናም ጦርነት፣ የቻይና ቲያኒመን አደባባይ ተቃውሞ፣ የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ፣ የሶርያ የስደተኞች ቀውስ እና በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት የሚያሳዩ ምስሎች ተካትተውበታል።

ዲምቢልቢ በፊልሙ ላይ፤ "በዩክሬን፣ በዓለም ዙሪያ ጋዜጠኞች የህዝቡን ስቃይ ለመዘገብ በየቀኑ ህይወታቸውን አደጋ ላይ እየጣሉ ነው" ሲል ይተርካል።

"ወደ ጋዛ ሲመጣ ግን የዘገባ ስራው ከባድ ዋጋ እየከፈሉ ባሉት ፍልስጤማውያን ጋዜጠኞች ላይ ብቻ ወድቋል፤ ይህም [ሁኔታውን ለዓለም የሚያደርሱ] እማኞች ጥቂት እንዲሆኑ አድርጓል" ሲልም ይደመጣል።

የዜና ተቋማት፤ የእስራኤል ባለሥልጣናት ጋዜጠኞች ወደ ግዛቱ መግባታቸውን እንዲፈቅዱ ጥሪ ሲያቀርቡ ይሄ የመጀመሪያው ጊዜ አይደለም።

ሐምሌ ላይ ቢቢሲ ኒውስ፣ ኤኤፍፒ፣ ኤፒ እና ሬውተርስ በጋራ ባወጡት መግለጫ በጋዛ የሚገኙ ጋዜጠኞች ርሃብ እና መፈናቀልን ጨምሮ እያለፉበት ያለውን ሁኔታ በተመለከተ የተሰማቸውን "አሳሳቢ ስጋት" ገልጸዋል።