ኢንስታግራምና ፌስቡክ ለኦፊሴላዊ የሰማያዊ ምልክት ክፍያ ሊጠይቁ ነው

ሜታ የተሰኘው የፌስቡክና ኢንስታግራም አስተዳዳሪ ኩባንያ ተጠቃሚዎች ከፍለው የሰማያዊ ምልክት ማግኘት እንደሚችሉ አስታውቋል።

'ሜታ ቬሪፋይድ' የተሰኘው አዲሱ ሥርዓት በድረ-ገፅ ለሚጠቀሙ 11.99 ዶላር ለአይፎን ተጠቃሚዎች ደግሞ 14.99 ዶላር ወርሃዊ ክፍያ እንደሚጠይቅ ተሰምቷል።

በዚህ ሳምንት በአውስትራሊያና ኒው ዚላንድ ይህን አዲሱን የክፍያ ሥርዓት ጀምሯል።

የሜታ ሥራ አስኪያጅ ማርክ ዛከርበርግ እንዳሉት ክፍያው ማሕበራዊ ድረ-ገፆች ደኅንነታቸው እንዲጠበቅና ማንነታቸው የታወቀ ሰዎች እንዲጠቀሙት ያስችላል ሲል ተደምጧል።

የትዊተር ባለቤት የሆነው ኢላን መስክ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ተጠቃሚዎች የሰማያዊ እርማት ለማግኘት እንዲከፍሉ ማድረጉ ይታወሳል።

ሜታ የዘረጋው ‘የሰብስክሪፕሽን’ ክፍያ ለጊዜው በፌስቡክና ኢንስታግራም ቢዝነስ ለሚሠሩ ክፍት ባይሆንም ማንኛውም ግለሰብ መጠቀም ይችላል።

‘ባጅ’ አሊያም ‘ብሉ ቲክ’ ተብሎ የሚጠራው መንገድ በርካታ ተከታይ ያላቸው ሰዎች ኦፊሴላዊ ገፃቸው መሆኑን ለመጠቆም ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል።

ሜታ እንደገለጠው በክፍያ የሚገኘው ‘ብሉ ቲክ’ ተጠቃሚዎች የሚለጥፉት መልዕክት በብዙዎች እንዲታይና በተመሳሳይ ስም ገፅ ከሚከፍቱ ተጠቃሚዎች እንዲጠበቁ ያደርጋል።

ኩባንያው ለቢቢሲ እንደተናገረው አዲሱ የክፍያ ሥርዓት ከዚህ ቀደም ሰማያዊ እርማት ያገኙ ተጠቃሚዎችን አይመለከትም።

ነገር ግን ብራቸውን አውጥተው ሰማያዊ እርማት ያገኙ ሰዎች የተሻለ መልዕክታቸው ለሌሎች የመድረስ አቅም አለው ይላል ኩባንያው።

ትዊተር፤ ባለፈው ኅዳር አንዳንድ ተጠቃሚዎች ገንዘብ ከፍለው ሰማያዊ እርማት ካገኙ በኋላ የተለያዩ ድርጅቶችንና ታዋቂ ሰዎችን ማስመሰል ከጀመሩ በኋላ በክፍያ 'ብሉ ቲክ' መስጠትን ገታ አድርጎ ነበር።

ቢሆንም ሜታ እንደሚለው ተጠቃሚዎች የክፍያ ሥርዓቱን ለማግኘት መንግሥት ያወጀው መታወቂያና ፊታቸውን የሚያሳይ ፎቶ ማስገባት አለባቸው።

ሜታ ይህ የክፍያ ሥርዓት መቼ ለሌሎች ሃገራት ይፋ እንደሚሆን ባይገልጥም ዛከርበርግ “በቅርቡ” ይሆናል የሚል ጥቆማ ሰጥቷል።

ኩባንያው ባለፈው ኅዳር በኮቪድ-19 ምክንያት በተከሰተው የኢንቨስተመንት ቀውስ 11 ሺህ ሰዎች ሥራቸውን ማጣታቸውን ገልጦ እንደነበር ይታወሳል።

በወቅቱ ዛከርበርግ የሜታ ገቢ እየተመነደገ ይመጣል ብሎ ቢገምትም ይህ ግን ሳይሆን ቀርቷል።

ዛከርበርግ እንደሚለው አዲሱ የክፍያ ሥርዓት የተዘረጋው የኩባንያውን ገቢ ለማሳደግ በሚል ነው።