ቱርክ ከሁለት ግዛቶች በስተቀር በሌሎቹ ሥፍራዎች የነብስ ማዳን ሥራዋን ገታች

ቱርክ፤ በከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ከተመታች ከሁለት ሳምንታት በኋላ የነብስ ማዳን ሥራዋን ማቀዛቀዝ ጀምራለች።

የሃገሪቱ አደጋ መከላከል መሥሪያ ቤት እንዳስታወቀው ከሁለት ግዛቶች በስተቀር በተቀሩት ሥፍራዎች የነብስ ማዳን ሥራው ቆሟል።

የአደጋ መከላከል ኤጀንሲ ኃላፊ እንዳሉት በካህራማንማራስ እና ሃታይ ግዛቶች ብቻ የነብስ ማዳን ሥራው ይቀጥላል።

ነገር ግን ከፍርስራሾች ውስጥ ሰዎችን በነብስ የማግኘት ተስፋው እየተሟጠጠ መጥቷል።

በሌላ በኩል የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ወደ ቱርክ አቅንተው ሃገራቸው ለሰብዓዊ እርዳታ 100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

7.8 ማግኒቲዩድ የተመዘገበው አስከፊው የመሬት መንቀጥቀጥ በዋነኛነት ካህራማንማራስ የተሰኘችውን ግዛት የጎዳ ሲሆን እስካሁን ድረስ 44 ሺህ ሰዎች በደቡብ ምስራቅ ቱርክና በሰሜናዊ ሶሪያ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ቱርክ ውስጥ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት 345 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን ተከትሎ የሟቾች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል ይገመታል። በርካታ ሰዎች አሁንም እየተፈገለጉ ይገኛሉ።

ቱርክም ሆነች ሶሪያ እስካሁን ድረስ ምን ያክል ሰዎች እንደጠፉ በቁጥር ያስቀመጡት ነገር የለም።

“በአብዛኛዎቹ ግዛቶቻችን የነብስ ማዳን ሥራዎች ተጠናቀዋል” ብለዋል የአደጋ መከላከል መሥሪያ ቤት ኃላፊው ዩኑስ ሴዜር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ።

ምንም እንኳ በሁለቱ ግዛቶች የነብስ ማዳን ሥራው አሁንም ተጠናክሮ ቢቀጥልም በሚቀጥሉት ቀናት እየቀነሰ እንደሚመጣ ኃላፊው ተናግረዋል።

ባፈለው አርብ የነብስ አድን ሠራተኞች ከፍርስራሾች ውስጥ ቢያንስ ሶስት ሰዎችን ማውጣት ችለዋል። ይህ የሆነው የመሬት መንቀጥቀጡ ከደረሰ ከ11 ቀናት በኋላ ነው።

ምንም እንኳ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ቱርክ ለማቅናት ከመሬት መንቀጥቀጡ በፊት አቅደው የነበረ ቢሆንም ድጋፋቸውን ለማሳየት እንደመጡ ተነግሯል።

ብሊንከን ወደ ሥልጣን ከመጡ ሁለት ዓመት ቢያልፋቸውም ወደ ቱርክ ሲያቀኑ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

“እርዳታው በቅርቡ መጓጓዝ ይጀምራል። እርዳታ ለነብስ አድን ሥራ ሳይሆን ለዘለቄታው መልሶ ማቋቋሚያ የሚሆን ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ብሊንከን ወደ ሶሪያ እርዳታ ማስገባት “በጣም በጣም ከባድ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የቱርክ ፕሬዝደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋንን ከማግኘታቸው በፊት ወደ ሃታይ ግዛት ተጉዘው የነብስ ማዳን ሥራውን እንደሚመለከቱ ተዘግቧል።

ሁለቱ ባለሥልጣናት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በተለይ ደግሞ ቱርክ፤ ስዊድንና ፊንላንድ ኔቶን እንዳይቀላቀሉ ለምን ፈለገች በሚለው ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።