በጋምቤላ የስደተኞች መጠለያ 80 ሺህ ሕጻናት ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጋልጠዋል - ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Ehab Zawati/MSF
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በጋምቤላ ክልል ከሚገኙ ሰባት የስደተኞች መጠለያዎች መካከል በአራቱ ውስጥ ያለው የተመጣጠነ ምግብ አገልግሎት በመቋረጡ፣ 80,000 የሚደርሱ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ለሕይወት አስጊ በሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጦት አደጋ ላይ ወድቀዋል አለ።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በጋምቤላ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ የሚሰጡ ቁልፍ ለጋሾች ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ የስደተኞች የኑሮ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ እየሽቆለቆ መሆኑን ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 30/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ ገልጿል።
መግለጫው አክሎም 80 ሺህ ደቡብ ሱዳናውያን ሕጻናት ለሕይወት አስጊ የሆነ ረሃብ ተደቅኖባቸዋል ሲል ገልጿል።
ቡድኑ የሕክምና አገልግሎት በሚሰጥባቸው በጋምቤላ ክልል በሚገኙ ሰባት የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ 395,000 ስደተኞች እንደሚኖሩ አስታውቋል።
ከአውሮፓውያኑ 2014 ጀምሮ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ሱዳን ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ጋምቤላ በርካታ ቁጥር ያላቸውን የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ይኖራሉ።
ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ዋነኛው ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋም የሆነው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) የሚያደርገውን ድጋፍ አቋርጠዋል።
ይህ በመላው ዓለም በምግብ፣ በጤና፣ በግብርና እና በሌሎችም ዘርፎች ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ድጋፍ የሚያደርገው የእርዳታ ተቋም መዘጋት በዓለም ዙሪያ በሚካሄዱ የሰብአዊ እርዳታ ፕሮግራሞች ላይ ጥልቅ ተጽእኖ እንደሚኖረው ተነግሯል።
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መንግሥት እንዲሁ የውጭ እርዳታውን 40 በመቶ እንደሚቀንስ የካቲት ወር ላይ አስታውቆ ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ያቀደው የውጭ እርዳታ ቅነሳ በአፍሪካ ለሕጻናት ትምህርት እና ለሴቶችን ጤና የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንሰው ተገልጿል።
ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን በመግለጫው ላይ ቡድኑ ባለፉት አስር ዓመታት በስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል።
የተለያዩ መንግሥታዊ ድርጅቶች በመጠለያ ጣቢያዎቹ የሚያደርጉት የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ የተስተጓጎለው ዩኤስኤአይዲ እንዲሁም ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ በከፍተኛ መጠን በመቀነሳቸው እንደሆነ የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ገልጿል።
የእርዳታው መቋረጥ በምግብ አቅርቦት፣ በጤና ክብካቤ አገልግሎት እንዲሁም የንፁህ መጠጥ ውሃ እና የንጽህና አገልግሎቶችን በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶታል ብሏል።
ለ17 ወር ልጇ ኩሌ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ከሚገኘው የኤምኤስኤፍ የጤና ተቋም የሕክምና ድጋፍ የምታገኘው ኒያኡሂላ ፖች "ካለፈው ዓመት ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ ቅነሳ አለ። ከዚህ በፊት እናገኛቸው የነበሩ ነገሮች አሁን አይሰጡም" ብላለች።
የኒያኢሂላ ልጅ በምግብ እጥረት መጎዳቷን ኤምኤስኤፍ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ከቲየርኪዲ የስደተኞች መጠለያ 8 ኪሎ ሜትር እየተጓዘች እርዳታ የምትቀበለው ኒያዋሂያል "በወር አንድ ጊዜ በቆሎ፣ ስንዴ እና ማሽላ ምግብ እንቀበላለን። ነገር ግን ሁልጊዜ ወሩ ከማብቃቱ በፊት ያልቃል" ስትል ስላለችበት ሁኔታ ተናግራለች።
በክልሉ የሚገኙ ሌሎች የስደተኞች መጠለያዎችም ተመሳሳይ ሁኔታ እያጋጠማቸው መሆኑን የድንበር የለሽ ሐኪሞች ቡድን በመግለጫው አስታውቋል።
በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል እና የገንዘብ አቅርቦት እጥረት ምክንያት የምግብ ሥርጭቱ ለወራት ቆሟል።
ሌላው በለጋሾች ድጋፍ መቋረጥ ምክንያት ከፍተኛ ፈተና ውስጥ የወደቀው እንደ ወባ መከላከል ያሉ ተግባራት የሚሰጡበት በሽታን የመከላከል ሥራው መሆኑን ኤምኤስኤፍ በመግለጫው ላይ አስታውቋል።
በክልሉ የወባ በሽታ እየተስፋፋ በመምጣቱ የኤምኤስኤፍ ቡድን ከግንቦት እስከ ጥቅምት ባለው የዝናብ ወቅት የወባ ሕሙማን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚሄድ ተንብይዋል።
እንደ የአልጋ አጎበር ሥርጭት፣ የቤት ውስጥ እና የውጪ ርጭት እና የጤና አገልግሎትን ወቅታዊ ተደራሽነት የመሳሰሉ ቁልፍ የወባ መከላከል ተግባራት በዚህ ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሱመምጣታቸውን ኤምኤስኤፍ ገልጿል።
በዚህም የተነሳ ክልሉ የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጣጠር ይቸግረዋል የሚል ስጋት መኖሩን የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አስታውቋል።
የኤምኤስኤፍ ምክትል የሕክምና አስተባባሪ ብርሃኑ ሳህሌ "በዚህ ከፍተኛ ሥርጭት ወቅት የሕሙማን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ በተጨናነቀ የኑሮ ሁኔታ እና የንፅህና አጠባበቅ ውስንነት ምክንያት ለወባ ተጋላጭ ለሆኑ ስደተኞች ከባድ ስጋት ይፈጥራል።"
በጋምቤላ በሚገኙ የስደተኛ መጠለያዎች የተለያየ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዓለም አቀፍ እርዳታዎች መቀነሳቸውን ተከትሎ ለቅቀው መውጣታቸው ይነገራል።
"በካምፑ ውስጥ ስትዘዋወር ብዙ ባዶ ሕንፃዎችን ታያለህ። በአንድ ወቅት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይገለገሉባቸው የነበሩ ቦታዎች አሁን ያነሱ ናቸው" የሚለው ደግሞ የኤምኤስኤፍ ፕሮጀክት አስተባባሪ አርማንድ ዲርክስ ነው።
"የእነሱ አለመኖር ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል። በአንድ ወቅት ይህንን ማኅበረሰብ ይደግፉ የነበሩ አገልግሎቶች አሁን የሉም ።"
ኤምኤስኤፍ በመግለጫው ላይ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ ያሉትን የጤና አጠባበቅ ፍላጎቶች ማሟላት ባለመቻላቸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በጋምቤላ የስደተኞችን ውህደት ወደ አካባቢያዊ አገልግሎቶች ለማስፋት ግልጽ እና ወሳኝ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጥሪ አቅርቧል።
ይህም ያለውን የጤና አገልግሎት ለሁሉም አገልግሎት መስጠት በሚችልበት መልኩ እና ወደፊት የሚኖሩ ቅነሳዎችን እንዲቋቋም አድርጎ ማጠናከርን አንደሚጠይቅ ኤምኤስኤፍ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።















