ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በማሊ ጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 49 ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ
በሰሜን ምስራቅ ማሊ ጸንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎች በሕዝብ ማመላለሻ ጀልባ ላይ በፈጸሙት ጥቃት 49 ሰላማዊ ሰዎችን መግደላቸውን የአገሪቱ ግዚያዊ መንግሥት አስታወቀ።
ጽንፈኛ ቡድኑ በወታደራዊ ጦር ሰፍር ላይም ጥቃት ፈጽሞ 15 ወታደሮችን መግደሉን አስታውቋል።
ወታደራዊው መንግሥት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ባስነገረው ዜና 50 የጽንፈኛው ቡድን አባላት መገደላቸውን ገልጿል።
በቅርብ ዓመታት የጽንፈኛ እስላማዊ ቡድን አባላት እንደ ማሊ ባሉ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ያላቸውን ተጽእኖ ፈጣሪነት እያሰፉ ነው።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በዚህ ጥቃት መገደላቸው ይገለጽ እንጂ በሰሜን ማሊ በምትገኘው ቲምቡክቱ ከተማ ባለፉት ሳምንታት በሕዝብ መጓጓዣ የትራንስፖርት አማራጮች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል።
እንደ ማሊ መንግሥት ከሆነ ታጣቂዎቹ ኒጀር ተብሎ በሚጠራው ወንዝ ከጋኦ ወደ ሞፕቲ ከተማ እየተጓዘ በነበረ የሕዝብ ማመላለሻ ጀልባ ላይ ጥቃት ከፍተው ነው 49 ሰላማዊ ሰዎቹን የገለዱት።
መንግሥት ጥቃቱን ተከትሎ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ የሐዘን ቀን አውጇል።
በጀልባ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው ኩባንያ ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ሲናገር የጀልባው የሞተር ክፍል ቢያንስ በሦስት ሮኬቶች ዒላማ ተደርጓል ብሏል።
ከዚያም ታጣቂዎቹ መንቀሳቀስ ወዳቃተው ጀልባ በመግባት ተሳፋሪዎችን ማስወረዳቸውን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የኩባንያውን ምጮች ጠቅሶ ዘግቧል።
ማሊ ከእአአ 2020 ጀምሮ በወታደራዊ ጁንታ ቡድን ስትመራ ቆይታለች።
ወታደራዊ ቡድኑ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ኬይታን ከስልጣን አውርዶ መንበሩን ከያዘ በኋላ ሰፊ ድጋፍ አግኝቶ ነበር።
ወታደራዊ ቡድኑ አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ አነስተኛ በሚባል ደረጃ በአገሪቱ የጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎች እንቅስቃሴን መግታት ችሏል።
ከእአአ 2012 ጀምሮ ከአል-ቃዒዳ እና ከእስላሚክ ስቴት ጋር ግንኙነት ያላቸው ጽንፈኛ እስላማዊ ቡድኑ በሰሜናዊ ማሊ ይንቀሳቀሳሉ።