ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፀሐይ ለመጠጋት እየሞከረች ያለችው የናሳ መንኩራኩር

የአሜሪካው የሕዋ ምርምር ተቋም መንኩራኩር በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፀሐይ የመጠጋት ሙከራ እያደረገች ነው።

ፓርከር ሶላር ፕሮብ የተባለችው መንኩራኩር እጅግ ከፍተኛ ሙቀት እና ላቅ ያለ ጨረር ተቋቁማ ወደ ፀሐይ የመጠጋት ሙከራ ታደርጋለች።

መንኩራኩሯ ለበርካታ ቀናት ከግንኙት ውጭ ስትሆን ሳይንቲስቶች የፀሐይን ቃጠሎ ተቋቁማ ይሆን ወይ የሚለውን በጉጉት እየተጠባበቁ ነው።

መንኩራኩሯ መትረፍ አለመትረፏ በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 27 ይታወቃል ተብሏል።

ፓርከር ሶላር ይህን ሙከራ የምታደርገው ፀሐይ እንዴት ነው የምትሠራው የሚለውን ለመረዳት ነው።

የናሳ የሳይንስ ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ኒኮላ ፎክስ "ላለፉት መቶ ዓመታት ሰዎች ፀሐይን ሲመረምሯት ቆይተዋል። ነገር ግን የአንድ ሥፍራ ከባቢያዊ ሁኔታ ለማወቅ ተጠግቶ ማየት ያስፈልጋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ስለዚህ የኮከባችንን ከባቢያዊ ሁኔታ ለማወቅ በአቅራቢያዋ መብረር አለብን ማለት ነው"

ፓርከር ሶላር ፕሮብ በአውሮፓውያኑ 2018 ነው ወደ ሶላር ሲስተም ማዕከላዊ ክፍል ያቀናችው።

መንኩራኩሯ እስካሁን 21 ጊዜ ፀሐይን የዞረች ሲሆን በየወቅቱ ወደ ፀሐይ እየተጠጋች ትገኛለች። በአውሮፓውያኑ ገና ዋዜማ ግን ከምን ጊዜውም በላይ ወደ ፀሐይ ተጠግታለች።

ፓርከር ሶላር ወደ ፀሐይ የተጠጋችው 6.2 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር (3.8 ሚሊዮን ማይል) ርቀት ላይ ነው።

ኒኮላ ፎክስ እንደሚሉት ይህ ርቀት በጣም የበዛ ቢመስልም በንፅፅር እጅግ ቅርብ ነው።

"እኛ ከፀሐይ 93 ሚሊዮን ማይል ርቀት ላይ ነው የምንገኘው።ለምሳሌ ፀሐይ እና መሬት አንድ ሜትር ርቀት ላይ ቢሆኑ ፓርከር ሶላር ከፀሐይ 4 ሴንቲ ሜትር ርቀት ላይ ነው ማለት ነው። ይህን ያህል ቅርብ ነው" ይላሉ።

መንኩራኩሯ ወደ ፀሐይ ስትጠጋ 1400 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት ተቋቁማ ነው። የፀሐይ ሙቀት የመንኩራኩሯን ክፍሎች የማቅለጥ ኃይል አለው።

ፓርከር ሶላር 11.5 ሴንቲሜትር ስፋት ባለው ካርበን-ኮምፖሲት የተሸፈነች ቢሆንም ዓላማዋ ቶሎ ገብቶ መውጣት ነው።

መንኩራኩሯ የሰው ልጆች ከሠሯቸው ቁሶች እጅግ ፈጣን ስትሆን በሰዓት 430 ሺህ ማይል ትጓዛለች። ይህ ማለት ከለንደን ኒው ዮርክ በ30 ሰከንድ እንደመጓዝ ነው።

ፀሐይን ለመንካት ይህን ያህል መጓዝ ለምን አስፈለገ?

ሳይንቲስቶች፣ መንኩራኩሯ ኮሮና በተባለው በትልቋ ኮከብ የውጭኛው ክፍል አልፋ ለዘመናት ያልተፈታ ጥያቄ ምላሽ ታስገኛለች የሚል ተስፋ አላቸው።

"ኮሮና በጣም በጣም ሞቃት ነው። ለምን እንዲህ ሞቃት እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም" ይላሉ የፊፍዝ ሰታር ላብስ የጠፈር ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ጄኒፈር ሚላርድ።

"የፀሐይ ሙቀት 6 ሺህ ሴልሺየስ አካባቢ ነው። ነገር ግን ኮሮና የተባለው የውጭኛው ክፍል በፀሐይ ግርዶሽ ጊዜ የምናየው ሲሆን ሚሊዮን ዲግሪዎች ሊደርስ ይችላል። የሚገኘው ከፀሐይ ራቅ ብሎ ነው። እንዴት ነው ይህ ከባቢ ሞቃት የሚሆነው?"

ከዚህ በተጨማሪ ሳይንቲስቶች 'ሶላር ዊንድን' ለመረዳት ሙከራ ያደርጋሉ። ሶላር ዊንድ ከኮሮና የሚመነጭ ነው።

ይህ ሶላር ዊንድ ከመሬት 'ማግኔቲክ ፊልድ' ጋር ሲዋሀድ አውሮራ የተባለውን ሰማይ ላይ የሚያበራ ብርሃን ይሰጣል።

ይህ የሕዋ የአየር ሁኔታ የተባለ ሒደት ኤሌክትሪክ ማመንጫዎችን፣ ኤሌክትሮኒክስ እና የኮሚዩኒኬሽን ሥርዓቶችን ሊያውክ ይችላል።

"ሐይን መረዳት፣ ሒደቱን ማወቅ፣ የሕዋ የአየር ሁኔታ እና ሶላር ዊንድን መገንዘብ መሬት ላይ ለምንኖር ሰዎች እጅግ አስፈላጊ ነው" ይላሉ ዶ/ር ሚላርድ።

የናሳ ሳይንቲስቶች በገና በዓል ወቅት በጉጉት የሚጠብቁት ከመሬት ጋር ግንኙነቷ የተቋረጠው መንኩራኩር ጉዳይ ነው።

ኒኮላ ፎክስ እንደሚሉት መንኩራኩሯ ደኅና መሆኗን የሚያሳይ ምልክት ሲታይ የፅሑፍ መልዕክት ይደርሳቸዋል።

ተመራማሪው ሁኔታው በፍርሀት ተውጠው እንደሚጠባበቁ ቢያምኑም በመንኩራኩሯ እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ።

"የመንኩራኩሯ ጉዳይ ያስጨንቀኛል። ነገር ግን ብዙ ነገሮች እንድትቋቋም አድርገን ነው የሠራናት። በጣም ጠንከራ አነስተኛ መንኩራኩር ናት።"