ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግብፅ ወታደሮቿ በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር እንደሚሰማሩ አስታወቀች
የግብፅ ወታደሮች በሶማሊያ በሚሰማራው የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ሚሽን ልዑካን ውስጥ እንደሚካተቱ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
"ከሶማሊያ መንግሥት በቀረበ ጥያቄ መሠረት ግብፅ በሰላም አስከባሪ ሚሽን ውስጥ ለመካተት ወስናለች" ሲሉ የውጭ ገዳይ ሚኒስትሩ ባድር አብድላቲ በጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል ይላል የሮይተርስ ዘገባ።
የሶማሊያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በግብፅ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው ይህ የተጠቀሰው።
የአፍሪካ ሕብረት ስታቢላይዜሽን ኤንድ ሰፖርት ሚሽን (አውሶም) የተባለው የሰላም አስከባሪ ኃይል በሚመጣው የአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት በሶማሊያ ይሰማራል ተብሎ ይጠበቃል።
"በሶማሊያ ስላለው ጉዳይ ውይይት አድርገናል። ሶማሊያ የግዛት አንድነቷን እና ሉዓላዊነቷን ለማስከበር የምታደርገውን ጥረት ግብፅ ትደግፋለች" ሲሉ የግብፁ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የራስ ገዟ ሶማሊላንድ የቀድሞ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ የመግባቢያ ሰነድ መፈረማቸው አይዘነጋም። ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና እንደምትሰጥ በምትኩ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር በር እንደምትከፍት ያትታል።
ይህን ሰነድ ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ውጥረት የከረረ ሆኖ ቆይቷል። የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ ከግብፁ አቻቸው አል ሲሲ እና ከኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረዋል።
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ውጥረት አሳስቦኛል ያለችው ቱርክ ሁለቱን ሀገራት ስታደራድር ቆይታ ታኅሣሥ 2/2017 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና እና የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ በተገኙበት የአንካራ ስምምነት ተፈርሟል።
ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን ስምምነቱን "ታሪካዊ" በማለት በሁለቱ አገራት መካከል "ሰላም እና ትብብር ለማምጣት የመጀመሪያ እርምጃ" እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች አውሶም በተሰኘው በአዲሱ የአውሮፓውያኑ ዓመት በሶማሊያ ይሰማራል ተብሎ በሚጠበቀው ሰላሚ አስከባሪ ሚሽን ውስጥ ስለመካተታቸው የተባለ ነገር የለም።
በተያያዘ ዜና በሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዓሊ ኦማር የሚመራ የልዑካን ቡድን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሰኞ ታኅሣሥ 14/ 2017 ዓ. ም. ወደ አዲስ አበባ ማቅናቱ ተገልጿል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ ልዑካኑ ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት "በአንካራ ስምምነት የተገባውን ቃል ለማጠናከር" ነው ብሏል።
"በአንካራ በሁለቱም አገራት መሪዎች አማካይነት የተደረሰውን ስምምነት መሠረት በማድረግ ጉብኝቱ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኛነት ያጠናክራል" ይላል መግለጫው።
አክሎ "የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት፣ በመከባበርና በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ትብብር የሚጎለብትባቸውን ዕድሎች" ትኩረቱ ያደርጋል ብሏል።
"የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት በሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ላይ ተመርኩዞ ከአጎራባች አገራት ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር ቁርጠኛ ነው።"
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ አንካራ ላይ ተገኝተው ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው ከስምምነት የደረሱት።
የአገራቱ መሪዎች ከስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ስምምነቱ ለወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የባሕር መተላላፊ በር እንድታገኝ የሚያደርግ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ከሁለት ቀናት በፊት የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማክሮን በኢትዮጵያ የአንድ ቀን ይፋዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅትም፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በውይይት እና ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ መናገራቸው አይዘነጋም።