የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከዓለም አቀፉ የእንስሳት መብት ተቆርቋሪ ድርጅት የሚደርስበት ወቀሳ ምንድነው?

ፒታ የተባለው ዓለም አቀፍ የእንስሳት መብት ተቆርቋሪ ድርጅት በቅርቡ አሜሪካ በሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮ የተቃውሞ ሰልፍ አድርጓል።

'ፒፕል ፎር ዘ ኤቲካል ትሪትመንት ኦፍ አኒማልስ' (ፒታ) የተባለው ድርጅት ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮ አካባቢ ነው ሰልፍ የጠራው።

ድርጅቱ እንደሚለው ሕገ-ወጥ የዝንጀሮ አዘዋዋሪዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተጠቅመው የተሸጡ የዝንጀሮ ዝርያዎችን አዘዋውረዋል።

ፒታ በተለይ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመቃወም የተለያዩ ዘመቻዎች እያካሄደ ነው።

የእንስሳት መብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ ዋሺንግተን በሚገኘው የኢቲ ቢሮ ከሰል በመድፋት ተቃውሞውን ማሰማቱ ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእንስሳት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ከፈቱ ያለውን የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻ ጠቅሶ በመግለጫ ምላሽ ሰጥቷል።

በአሜሪካው ቢሮ የተፈጠረው ምንድነው?

በአውሮፓውያኑ ሐሙስ ታኅሣሥ ዲሲ አካባቢ በሚገኘው የአየር መንገዱ ቢሮ ዙሪያ የሳንታ ክላውስ (የፈረንጆቹ የገና አባት) ልብስ የለበሱ የፒታ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮ ዘልቀው ገብተው ከሰል የበተኑት።

ፒታ ታኅሣሥ 18/2024 በድረ-ገፁ ባወጣው መግለጫ በዋሺንግተን ቢሮ ተቃውሞ ያሰማው "አየር መንገዱ [ማኩዌስ የተባሉ] ሊጠፉ የተቃረቡ የዝንጀሮ ዝርያዎችን ለቤተ-ሙከራ ጥቅም ላይ እንዲውሉ አጓጉዟል" በሚል መሆኑን አስታውቋል።

ሕገ-ወጥ ነው የተባለ ዓለም አቀፍ የእንስሳት አዘዋዋሪ ድርጅት የዝንጀሮ ዝርያዎችን በአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ አዘዋውሯል ተብሎ የቀረበበት ክስ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስም መጠቀሱን መግለጫው አመላክቷል።

የፒታ ነባር ምክትል ፕሬዝደንት ካቲ ጊየርሞ "የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፍርሀት የተርበደበዱ ዝንጀሮዎችን አዘዋውሯል።እነዚህ ጦጣዎቹ ስቃይ ደርሶባቸዋል፤ አካላቸው ተበላልቶ፣ ተገድለዋል። የሕዝብን ጤናም አደጋ ሊጥሉ ይችላሉ" ብለዋል።

ኤኤልኤክስናው የተባለው ድረ-ገፅ እንደዘገበው ተቃዋሚዎቹ በቢሮው ውስጥ እና ከቢሮው ውጭ ከሰል መድፋታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጉዳዩን ለፖሊስ ሪፖርት አድርጓል።

ድረ-ገፁ አክሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢሮ ለተወሰኑ ሰዓታት ተዘግቶ እንደነበር አስነብቧል።

ኤኤልኤክስናው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ የደረሰኝ ነው ብሎ በድረ-ገፁ የለጠፈው ተንቀሳቃሽ ምስል ቢሮው ውስጥ የተደፋ ከሰል ያሳያል።

ፒታ በመግለጫው ከሰል የተደፋው በቢሮው መግቢያ በር ላይ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምን አለ?

አየር መንገድ በአውሮፓውያኑ 15 ታኅሣሥ 2024 በኦፊሴላዊ ፌስቡክ ገፁ ባወጣው መግለጫ በማኅበራዊ ሚድያ የተከፈቱ ዘመቻዎችን መመልከቱን አስታውቋል።

መግለጫው ምንም እንኳ ዘመቻውን እያካሄዱ ያሉት ለዱር እንስሳት የሚቆረቆሩ ድርጅቶች ቢሆኑም "እውነተኛ መረጃ ላይ የተመሠረቱ ቢሆኑ እና ሐሰተኛ አሊያም አሳሳች የሆኑ ወቀሳዎችን ከማቅረብ የተቆጠቡ" ሊሆኑ ይገባል ብሏል።

አክሎ "የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሕይወት ያሉ እንስሳት በማጓጓዝ ረገድ የተቀመጠውን ዓለም አቀፍ ሕግ ተከትሎ እንደሚንቀሳቀስ" ገልጿል።

መግለጫው እንደሚለው አየር መንገዱ በቅርቡ ገለልተኛ ባለሙያ ቀጥሮ ባደረገው ማጣራት መሠረት የዓለም አቀፉ አየር ትራንስፖርት ማኅበርን (አያታ) እንዲሁም በሕይወት ያሉ እንስሳት ቁጥጥር (ኤልኤአር) ሕግጋትን ተከትሎ ነው የሚንቀሳቀሰው።

"የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሕግጋትን እየጣሰ ነው የሚያበረው ተብሎ የቀረበው ውንጀላ ሀሰት ነው" ይላል መግለጫው።

"አየር መንገዱ እኒህ የእንስሳት መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች የሚያነሱትን ስጋት ቢረዳም ሕዝቡ እና ድርጅቶቹ ሊያውቁት የሚገባው በሥራችን ከፍተኛውን ሥነ-ምግባራዊ መርሆ እንደምንከተል ነው።"

አየር መንገዱ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በዲሲ አካባቢ በሚገኘው ቢሮው አካባቢ ተነስቶ ነበር ስለተባለው ተቃውሞ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

ቢቢሲ፤ ፒታ የተባለው ድርጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ስለሚያቀርበው ቅሬታ እና በዲሲ ቢሮ ስለተከሰተው ጉዳይ ከአየር መንገዱ ማብራሪያ ጠይቆ ምላሽ አላገኘም።

ፒታ የተባለው የእንስሳት ተቆርቋሪ ድርጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ቅሬታውን ሲያቀርብ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ባለፈው ጥቅምት በኤክስ ገፁ ባጋራው ቪድዮ ቶኪዮ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተቃውሞ ማሰማቱን አሳውቋል። አልፎም ኒው ዮርክ እና ብራሰልስ ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ተቃውሞ ማሰማቱ ይታወሳል።

በአውሮፓውያኑ 2021 'ዎርልድ አኒማል ፕሮቴክሽን' የተሰኘ ድርጅት ይፋ ባደረገው ጥናት ለንግድ የሚውሉ የዱር እንስሳትን አስከፊ በሆነ አያያዝ ከምዕራብ አፍሪካ ወደተለያዩ መዳረሻዎች ያጓጉዛል ሲል መወቀሱ ይታወሳል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሕይወት ያሉ የዱር "እንስሳትን የማጓጉዘው በከፍተኛ ጥንቃቄ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ፣ ብሔራዊ ሕጎችን እና የውስጥ አሰራርን በመከተል ነው" ሲል ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።

ባለፈው ሐምሌ የፒታ ዩኬ የዘመቻ ኃላፊ ሩበን ስኪት፤ የፒታ እስያ ምክትል ፕሬዝደንት ጄሰን ቤከር እና የ11 ዓመት ልጃቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ከሀገሩ መባረራቸው ተዘግቦ ነበር።

ሁለት አሜሪካውያን እና አንድ ብሪታኒያዊ አየር መንገዱ ዝንጀሮዎችን ኢሰብዓዊ በሆነ አያያዝ ሞት ወደሚጠብቃቸው ቤተ-ሙከራዎች ያጓጉዛል በማት ሲቃወሙ ነበር በፖሊስ የተያዙት።

ፒፕል ፎር ዘ ኢቲካል ትሪትመንት ኦፍ አኒማልስ (ፒታ) የተሰኘው ድርጅት በየክፍለ ዓለማቱ የእንስሳትን መብትን በተለመከተ ዘመቻ በማድረግ እና ተቃውሞ በማሰማት የሚታወቅ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።