ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰውን ልጅ በመግደል አደገኛ የሆኑት 10 እንስሳቶች የትኞቹ ናቸው?
የዓለማችን እጅግ አደገኛ እንስሳ የትኛው ነው ብለው ያስባሉ? ጥቂት የማይባሉ እንስሳት በአደገኝነታቸው ዝና ቢጤ አትርፈዋል።የአደገኝነት መንበሩን መቆናጠጥ የሚችለው ግን አንድ እንስሳ ነው። ጥያቄውን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ያህል፤ ብዙ ሰዎችን የሚገድለው እንስሳ የትኛው ይመስሎታል?
የሆሊውድ ፊልሞች ይህንን ስያሜ የተቆናጠጠው ከእንስሶች መካከል ጠንካራው እንደሆነ እንዲያስቡ አድርገዎት ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት እንደ አንበሳ እና አዞ ያሉ እንስሳትን ይበልጥ ሊፈሯቸው ይችላሉ።
ይሁን እንጂ ሰውን ለሞት ከመዳረግ አንጻር ብዙዎቹ እንስሳት ገዳይነታቸው ከሚታሰበው በታች ነው። ለምሳሌ ሻርኮች በየዓመቱ ለሞት የሚዳርጉት አማካይ የሰው ብዛት 70 ብቻ ነው።
በሚያስደንቅ ሁኔታ፤ ብዙዎቹ የምድራችን ገዳይ እንስሳት ብዙውን ጊዜ ትናንሽ ናቸው።ሰዎችን የሚገድሉትም ስለታማ በሆኑት ጥርሶቻቸው ሳይሆን በበሽታ፣ በመርዝ እና በሌሎች መንገዶች ነው።
በጥቅሉ ግን ብዙዎቹ የዓለማችን አደገኛ እንስሳት 'የትኛዎቹ ናቸው?' ለሚለው ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ አስገራሚ ሊሆን ይችላል። ከአስረኛው እንጀምር፦
10ኛ አንበሳ - በዓመት 200 ሰዎችን ይገድላል
ምንም እንኳ ጫካ ውስጥ ባይኖርም 'የጫካው ንጉስ' ተብሎ የሚታወቀው አንበሳ፤ በአደገኝነት ደረጃ ዝርዝር ላይ በቀዳሚነት እንደሚቀመጥ ገምተው ከነበረ ተሳስተዋል። እንዲያም ባይሆን ግን አንበሳ ሊዳፈሩት የማይገባ ጨካኝ አዳኝ እንስሳ ነው። በ114 ዴሲብል የሚለካው አስፈሪ የማጓራት ድምፁ ብቻውን ይህንን ገላጭ ነው።
አንበሳ፤ ብዙውን ጊዜ በምሽት የሚያጠቃ፣ ሰርገው የሚገቡ ቁስለቶችን ለመፍጠር ስለታማ ጥፍሮቹን የሚጠቀም እንዲሁም በንክሻ አጥንት እና የራስ ቅልን የሚሰብር አስፈሪ አውሬ ነው።
ትልቅ ድመት የሆኑት አንበሶች፤እድለ ቢስ ሆኖ ከእጃቸው የገባን ግለሰብ ከብበው በድንገት ዘለው ከማጥቃታቸው በፊት በቡድን ሆነው ያደባሉ።
ወደ አንበሶች መቅረብ ዋጋ ያስከፍላል፤ በተለይ በስሪያ እና ከደቦሎቻቸው ጋር በሚሆኑበት ጊዜ። እነዚህ ግርማ ሞገሳም ትልቅ ድመቶች ርሃብ ሲጠናባቸው እና ልጆቻቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ሊያጠቁ ይችላሉ።
9ኛ ጉማሬ - በዓመት 500 ሰዎችን ይገድላል
እጽዋት ተመጋቢ የሆኑት ጉማሬዎች እዚህ ዝርዝር ውስጥ መግባታቸው አስገራሚ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን አስገራሚ አቀማመጥ ላለው ጥርሳቸው እና ለጠበኛ ባህሪያቸው ምስጋና ይግባና፤ ከፕላኔታችን እጅግ አደገኛ እንስሳት መካከል አንዱ ናቸው።
ጉማሬዎች በጥል ወቅት ግማሽ ሜትር ርዝመት ያለውን ክራንቻ ጥርሳቸውን የሚጠቀሙ ሲሆን የእነዚህ ፍጥረቶች አንድ ንክሻ ብቻውን የሰውን ልጅ ለሁለት ሊከፍል ይችላል። የጉማሬ ንክሻ፤ አንድ ነገርን የክብደት ጫና ለመለካት በሚውለው PSI (pounds per square inch) ሲለካ 1,800 ነው። ይህም ማለት የንክሻው ኃይል ከአንበሳ ጋር ሲጻጸር በሦስት እጥፍ ገደማ ይበልጣል።
በግዛታቸው ሲመጡባቸው አስፈሪ የሆኑት ጉማሬዎች፤ ወደ መኖሪያቸው የሚቀርቡ ሰዎችን ሊያጠቁ ይችላሉ። ጀልባዎችን ሲያዩ ሊያጠቋቸው የመጡ አካላት ስለሚመስሏቸውም ራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ በማጥቃት እና ጀልባን በመገልበጥ ይታወቃሉ። ከፍርሃት የተነሳም ሌሎች ጉማሬዎችን በመብላት ይበልጥ ይታወቃሉ።
8ተኛ ዝሆን - በዓመት 600 ሰዎችን ይገድላል
ነገሮችን በጭራሽ የማይረሱት ዝሆኖች፤ ሌላኛው መገለጫቸው ሰዎችን መግደላቸው ነው። ኃያሎቹ ዝሆኖች፤ ዕድሜ ለግዝፈታቸው ከዓለማችን እጅግ አደገኛ እንስሳት መካከል ናቸው። ሰዎችን በተለያዩ መንገዶች ሊያጠቁ ይችላሉ።
ዝሆኖች ብዙውን ጊዜ ሰዎችን የሚገድሉት በመርገጥ ነው። የአፍሪካ ዝሆን እስከ ስምንት ቶን ድረስ የሚከብድ ሲሆን የእስያ ዝሆኖች እስከ አምስት ከግማሽ ቶን ይመዝናሉ። ይህንን ያህል ክብደት ካለው ዝሆን የሚመጣ ምት እና ረገጣ የሚፈጥረው ኃይል አንድን ሰው ለመግደል በቂ ነው።
በተጨማሪም ዝሆኖች ኩንቢያቸውን ተጠቅመው ሰዎችን ማንሳት እና አሽቀንጥሮ መጣል ወይም ከመሬት ጋር ማላተም ይችላሉ። ጥርሳቸውን በመጠቀም ሰዎችን እንደሚወጉም ይታወቃል።
7ተኛ አዞ - በዓመት 1,000 ሰዎችን ይገድላል
አዞ፤ በዓመት እስከ አንድ ሺህ ለሚደርሱ ሰዎችን ሞት ምክንያት የሚሆን እና በጨካኝነቱ የሚታወቅ እንስሳ ነው። የአዞን ጥርስ አንድ ጊዜ መመልከት ብቻውን እነዚህ ተሳቢ እንስሳት ለምን አደገኛ እንደሆኑ ያስረዳል።
የናይል አዞ ንክሻ እስከ አምስት ሺህ PSI የሚደርስ ኃይል አለው፤ ይህም የዓለም ጠንካራ እንስሳ ያደርገዋል። በንጽጽር ዝቅተኛ የንክሻ ኃይል ያለው በጨዋማ የውሃ ክፍሎች የሚኖረው Saltwater crocodile የተባለው የአዞ ዝርያ ነው። የንክሻ ኃይሉ 3,700 PSI የሚለካው ይህ ዝርያም ቢሆን የንክሻ ኃይሉ ከሌሎች እንስሳት ጋር ሲነጻጸር ሁለተኛ ነው።
እነዚህ የአዞ ዝርያዎች፤ አዳኛቸውን ነክሰው የሚይዙ ሲሆን የበለጠ ህመም ለመጨመር ሲሉም እንደያዙት ሊንከባለሉ ይችላሉ። የናይል አዞዎች በአንጻሩ፤ አዳኛቸውን ሙሉ በሙሉ ከመዋጣቸው በፊት በቀላሉ አካሉን ለመስበር እጅግ ኃይለኛ የሆነውን ንክሻቸውን ይጠቀማሉ።
አዞዎች ጠበኛ እና እጅግ ግዛታቸውን የማያስደፍሩ እንስሳት ናቸው። ብዙውን ጊዜም ወደ መኖሪያቸውን የተጠጋን አካል ውሃ ውስጥ አድብቶ በመጠበቅ ያጠቃሉ።
6ተኛ ጊንጥ - በዓመት 3,300 ሰዎችን ይገድላል
እነዚህ ጥንታዊ፣ ጠበኛ እና ሰውነትን የሚሸክኩ እንስሳት፤ አዳኛቸውን በጭራቸው በመውጋት ወደ ሰውነቱ መርዝ ያስገባሉ። ከ2,600 በላይ ዝርያ የጊንጥ ዝርያዎች ያሉ ሲሆን ሰዎችን መግደል የሚያስችል በቂ መርዝ ያላቸው 25ቱ ዝርያዎች ብቻ ናቸው።
በጣም አደገኛ ከሆኑት ዝርያዎች መካከል አንዱ ስያሜውም ላይ ሞት የሚል ቃል የያዘው ዴዝስቶከር (deathstalker) ነው። ይህ ቢጫ የጊንጥ ዝርያ በደረቅ እና በረሃማ መልክዐ ምድሮች የሚገኙ ሲሆን በሰሜን አፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ በረሃዎችም ይገኛሉ።
እነዚህ ገዳይ ዝርያዎች የሚይዙት መርዝ፤ ወጣቶችን፣ አረጋውያንን እንዲሁም እንደ ልብ ህመም ያሉ ህመሞች ያሉባቸው ሰዎችን ለመግደል የሚበቃ ነው። የመሆን እድሉ ዝቅተኛ ቢሆንም ጤነኛ አዋቂ ሰዎችን በዚህ ጊንጥ ሊገደሉ ይችላሉ።
5ተኛ ገዳይ ትኋን (ቻጋስ በሽታ) - በዓመት 10,000 ሰዎችን ይገድላል
ገዳይ ትኋኖች የቻጋስ በሽታ ዋነኛ አስተላለፊዎች ናቸው። እነዚህ ደም መጣጭ ነፍሳት በመካከለኛው እና ደቡብ አሜሪካ ትልቅ ስጋት ናቸው።
ቻጋስ እስከ ሞት የሚያደርስ በሽታ ሲሆን የሚተላለፈውም በገዳይ ትኋን ንክሻ ወይም በነፍሳቱ የተበከለን ቀዝቃዛ ውሃ እና ምግብ በመጠቀም ነው። በዚህ ነፍሳት ዓይነ ምድር የተበከለ ቀዝቃዛ ውሃ እና ምግብን መጠቀምም ለበሽታው ይዳርጋል።
የፓን አሜሪካ የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ቻጋስ ልብ እንዲሁም የምግብ መፍጫ እና የነርቨስ ስርዓቶችን የሚያጠቃ አስከፊ በሽታ ነው። በእርግዝና ወቅትም ከእናት ወደ ልጅ ሊተላለፍ ይችላል።
4ተኛ ውሻ (የእብድ ውሻ በሽታ) - በዓመት 59,000 ሰዎችን ይገድላል
የሰው ልጅ ጓደኛ የሆነው ውሻ፤ የእብድ ውሻ በሽታ በመባል የሚጠራው ራቢስ በሚይዘው ጊዜ የሰው ልጅ ጠላት ይሆናል። የውሻን ጥቃት ለማስረዳት የውሃ እና መብራት ቆጣሪዎች ጥሩ ምስክር ናቸው።
ውሾች ባለቤቶቻቸውን ከሰርጎ ገቦች የሚጠብቁ ሲሆን ይህንን ለማድረግም ይናከሳሉ።
በውሻ ንክሻ ምክንያት የሚፈጠር ሞት ያልተለመደ ቢሆንም በውሻ ንክሻ ምክንያት በሚተላለፍ የራቢስ በሽታ የሚፈጠር ሞት ግን አዲስ አይደለም። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በተለይ እንደ አፍሪካ እና እስያ ባሉ አህጉራት የሚታይ ነው።
የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በሰው ልጅ ላይ ለሚከሰት የእብድ ውሻ በሽታ ሞት ዋነኛዎቹ ምንጮች ውሾች ናቸው። 99 በመቶው ይህ በሽታ ወደ ሰዎች የሚተላለፈው በውሾች ነው። በሽታው፤ በንክሻ ጊዜ በሚፈጠር የምራቅ ንክኪ፣ መቧጨር እንዲሁም ከውሻው የቆሰለ አካል ጋር በሚኖር ቀጥተኛ ንክኪ ይተላለፋል።
3ተኛ እባብ - በዓመት 138,000 ሰዎችን ይገድላል
የሰው ልጅ እነዚህን መርዛማ ተሳቢ እንስሳት ለመፍራት በቂ ምክንያት አለው። አደገኛ እባቦች በመላው ዓለም የሚገኙ ሲሆን በተለያዩ እና አሰቃቂ መንገዶች ሰዎችን ሊገድሉ ይችላሉ።
ለምሳሌ፤ ብላክ ማምባ የተሰኘው የእባብ ዝርያ በንክሻ ወቅት በሚያስተላልፈው ሁለት ጠብታ መርዝ ሰውን ሊገድ ይችላል። ዘንዶዎች ደግሞ አዋቂ ሰውን በሙሉ ሊውጡ ይችላሉ።
ዘንዶዎች፤ ረጅም አካላቸውን በታዳኛቸው ላይ በመጠምጠም እና ሰውነቱን በመጭመቅ ጥቃታቸውን ይፈጽማሉ። በዚህ ድርጊታቸውም ታዳኙን ያፍናሉ እንዲሁም አጥንቱን ይሰባብራሉ። ከዚያም እንዳሻው በሚለጠጠው መንጋጋቸው የግዳያቸውን ሰውነት በሙሉ ይውጣሉ። እስከ አስር ሜትር ርዝመት ድረስ የሚያድጉት ዘንዶዎች፤ አንድ ሰውን ሙሉ በሙሉ ሊውጡ ይችላሉ።
በእባብ ምክንያት የሚፈጠር የሰው ሞት ብዙውን ጊዜ የሚከሰተው በመርዛማ ንክሻዎች ነው። እድለኛ የሆኑ ሰዎች ግን የሰውነት አካላቸው ተቆርጦ ወይም ሌሎች "ቋሚ አካል ጉዳቶችን" አስተናግደው በሕይወት እንደሚተርፉ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።
2ተኛ የሰው ልጅ (የነፍስ ግድያ) - በዓመት 400,000 ሰዎች ይገደላሉ
አዎ፤ ይህ የደረጃ አሰጣጥ ማጭበርበር ሊመስል ይችላል። ነገር ግን የሰዎችን ግድያ ምክንያትን ካሰብን የሰው ልጆች የዓለማችን ሁለተኛዎቹ አደገኛ እንስሳት ናቸው። ለዚህም ነው የሰው ግድያ እየተቆጠረ የሚመዘገበው።
"Our World in Data" የተሰኘው ድረ ገጽ መረጃ እንደሚያሳየው "እ.አ.አ በ2019 ከተከሰቱ ሞቶች ውስጥ 0.7 በመቶው የነፍስ ግድያ ውጤት" ናቸው። ከሌሎች የዓለም ክፍሎች አንጻር በላቲን አሜሪካ የነፍስ ግድያ መጠን ከፍተኛ ነው። "በኤል ሳቫዶር ከሚከሰቱ ሞቶች ውስጥ ከሰባት በመቶ በላዩ" የነፍስ ግድያ ድርጊቶች ናቸው።
ከእንስሳት መካከል የራሳቸውን ዝርያ የሚገድሉት ሰዎች ብቻ አይደሉም። በመላው እንስሳት መስተጋብር ውስጥ ይህ ድርጊት አለ።
1ኛ ወባ - በዓመት 725,000 ሰዎችን ይገድላል
እንደ ወባ በሽታ ያሉ የጤና እክሎችን የሚያስተላልፉት እና በየዓመቱ ለ725 ሺህ ሰዎችን ሞት ምክንያት የሆኑት የወባ ትንኞች የዓለማችን አደገኛዎቹ እንስሳት ናቸው። የሰውን ልጅ የሚነክሱት ሴት ወባዎች ብቻ ሲሆኑ ይህን እጅግ አደገኛ ያደርጋቸዋል።
የመግደል አቅማቸው ከፍተኛ የሆነው እኚህ ትንሽ በራሪ ነፍሳት ከአሜሪካ ነጻነት እስከ የሮም መነሳት እና መውደቅ ድረስ በተለያዩ ጊዜያት የሰውን ልጅ ታሪክ መርተዋል።
የወባ በሽታ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ አስከፊ ነው። የዓለም 95 በመቶው የወባ በሽታ እና በዚሁ በሽታ የሚከሰት 96 በመቶው ሞት የሚፈጠረው አፍሪካ ውስጥ ነው።
የወባ በሽታ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ጉዞ ሲደረግ በተቻለ መጠን አጎበር በመግዛት የወባ ትንኝን መከላከል እጅግ ጠቃሚ ነው።