የሰውን በሽታ የመለየት አስገራሚ ችሎታ ያላቸው በቤታችን የሚገኙ እንስሳት

ያለብንን በሽታ በትክክል ለማወቅ በጣም ውድ እና ወደ ሰውነታችን ዘልቆ በመግባት ምን እየተካሄደ እንዳለ ለማወቅ የሚያስችሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች እንደሚያስፈልጉ እናስባለን።

በእርግጥ እነዚህ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተራቀቁ የህክምና መሣሪያዎች የሚሰጡት ጠቀሜታ አስገራሚ ነው።

ሆኖም ያለንበትን የጤና ሁኔታ ለማወቅ የሚያስችሉ ብቸኛ ዘዴዎች አለመሆናቸውን ብንነግራችሁስ?

ሌሎቹ በሰውነታችን ውስጥ ያለን በሽታ ለማወቅ የሚረዱን ቤታችንን የሚጋሩ እንስሳት ናቸው።

በበሽታ እንደተያዙ ያላወቁ የቤት እንስሳት አሳዳሪዎች የጤና ችግር እንደነበረባቸው ኋላ ላይ ከእንስሳቶቻቸው መረዳት እንደቻሉ በርካታ የሕክምና ክስተቶች አስረድተዋል።

ለምሳሌ ውሻዎች የአሳዳሪዎቻቸውን ቆዳ [በኋላ ላይ የቆዳ ካንሰር ሆኖ የተገኘ] በመላስ፣ በማሽተት እና በአሳዳሪዎቻቸው ቆዳ ላይ ያለን ምልክት ለመንከስ በመሞከር ምልክት ሲሰጡ ነበር።

ይህንን የሚያደርጉ በርካታ የእንስሳት ዝርያዎች ቢኖሩም ጉንዳኖች፣ አይጦች እና ውሾች በሰው ልጅ ውስጥ ያለን በሽታ እና በምርምር ላይ ያሉ ናሙናዎችን የመለየት አቅማቸውን አሳይተዋል።

በእነዚህ እንስሳት የተለዩ በሽታዎች የተለያዩ ሲሆኑ ካንሰር፣ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን፣ ኮቪድ 19 እና የሆድ ኢንፌክሽን ይገኙበታል።

አብዛኞቹ እነዚህ በሽታዎች በተለይ በሽታ የመከላከል አቅማቸው በተዳከመ ሰዎች ዘንድ ወደ ከፋ ደረጃ ሊሸጋገሩ ስለሚችሉ በጊዜ በሽታዎችን ማወቅ አስፈላጊ ነው።

በመሆኑም መሰል የሰው ልጆችን የሚያጠቁ በሽታዎችን የሚለዩ ጥቂት አስገራሚ እንስሳትን እንመልከት።

ውሾች

ውሾች ፓርኪንሰን የተባለውን የነርቭ ህመም፣ የሽንት ፊኛ ካንሰር እና የወባ በሽታን ጨምሮ የተለያዩ በሽታዎችን ለመለየት ባላቸው ችሎታ ይታወቃሉ።

ለሕክምና አገልግሎት በልዩ ሁኔታ የሰለጠኑ ውሾች የሚጥል በሽታን እንዲሁም የስኳር በሽታ ታማሚዎች በደማቸው ውስጥ የስኳር መጠን ዝቅተኛ መሆኑን መለየት ይችላሉ።

ውሾች በተፈጥሮ የተቸራቸው አስደናቂ የማሽተቻ የስሜት ህዋሳቸው ለመለየት የሚያዳግቱ የጠረን ውህዶችንም ቢሆን የተወሰኑትን ይለያሉ።

የውሾች የማሽተት ችሎታ ሰዎች ካላቸው የማሽተት ችሎታ ከ10 ሺህ ጊዜ በላይ የተሻለ ነው። የአፍንጫ ቀዳዳዎቻቸውን በመጠቀምም ያለምንም ተጨማሪ እርዳታ አዲስ ጠረኖችን የመመርመር ብቃት ተፈጥሮ ችራቸዋለች።

በሕክምናው ዘርፍ ባዮዲቴክሽን (በየቀኑ በሰውነታችን ውስጥ የሚካሄዱ የኬሚካል ለውጦች) እና ለጤና ማስጠንቀቂያ የሚውሉ ውሾች አሉ።

እነዚህ ውሾች ቀደም ብለው ሽልማት እየተሰጣቸው ከተወሰኑ ጠረኖች ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎች የተሰጣቸው ናቸው። ከዚያም የጠረኖችን ወይም የአካል እና የባህርይ ለውጦችን እንዲለዩ ተደርገው ይሠለጥናሉ።

በዚህም ሥነ ሕይወታዊ ለውጥን የሚለዩ - ባዮዲቴክሽን ውሾች የሆነ ጠረን በሚለዩበት ወቅት ሽልማት እንዲሰጣቸው ለመጠበቅ ባሉበት ይቆማሉ።

ለጤና ማስጠንቀቂያ የሚውሉ ውሾች ደግሞ ብዙውን ጊዜ ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ የሆነ እርምጃ እንዲወስዱ ምልክት ለመስጠት ከባለቤታቸው ጋር ይተሻሻሉ፣ ይላፋሉ።

አይጦች

አይጦችም ልዩ ጠረኖችን የመለየት ብቃታቸው ከፍተኛ ነው።

ትልቅ የአፍሪካ ዝርያ ያላቸው አይጦች በሞዛምቢክ በመሬት ውስጥ የተቀበሩ እና የተተው ፈንጂዎችን በጠረን ለመለየት ሲሠለጥኑ ቆይተዋል።

በሕክምናው ዘርፍም ወሳኝ አጋር መሆናቸውን እያረጋገጡ ነው። እያገገሙ ካሉ ህሙማን ከተወሰደ የምራቅ ናሙና ውስጥ የሳንባ በሽታን (ቲቢ) ለመለየት ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ነው።

አይጦች በጣም ፈጣን ሲሆኑ የ100 ህሙማንን ናሙናዎች ለማሽተት የሚወስድባቸው ጊዜ 20 ደቂቃ ብቻ ነው። ቲቢን ከናሙና ውስጥ ለመለየትም የሚያሸቱበትን የስሜት ህዋሳቸውን ይጠቀማሉ።

ለዚህ ለሠሩት ጥሩ ሥራም አቮካዶ እና ሙዝ እንደ ሽልማት ይቀርብላቸዋል። ይህም እነዚህን የሠለጠኑ አይጦች ጊዜ እና ገንዘብ ውስን በሆነባቸው የሕክምና እና የምርምር ተቋማት ጥሩ አማራጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

81 በመቶ ለሚሆን ጊዜ በቲቢ በሽታ የተያዙ ሰዎችን በትክክል በመለየት አስገራሚ ውጤትም አስመዝግበዋል።

ንቦች

እነዚህ ነፍሳት የሳንባ ካንሰርን፣ ቲቢን እና ኮቪድ-19ን ጨምሮ የተወሰኑ በሽታዎችን ምልክቶች መለየት ይችላሉ።

ንቦች ዝቅተኛ መጠን ያላቸው ጠረኖችን ጭምር የማሽተት አቅማቸው ከፍተኛ ነው። ይህም ልክ እንደ ውሾች እና አይጦች የኬሚካል ለውጦችን መለየት ያስችላቸዋል።

ተመራማሪዎችም ለንቦች እንደ ሽልማት ስኳር በመስጠት የተወሰኑ ጠረኖችን እንዲለዩ ማሠልጠን ችለዋል። በሥልጠናው ይህ ምላሻቸው ጤናማ ያልሆነ አናቶሚ (የሰውነት ቅርጽ) እና ፓቶሎጂ (በሽታ) ጋር ለተያያዙ ጠረኖች 'ሴንሲቲቭ' ሲሆኑ የሚሰጡትም ምላሽ ቋሚ ሆኗል።

ይህ ችሎታቸውም ንቦች በተመሳሳይ መልኩ እንደ ሌሎች እንስሳት በሽታዎችን ለመለየት ጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

በተለይም በአካል መጠናቸው አነስተኛ መሆናቸው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ እና በፍጥነት ለሚሠሩ የናሙና ትንተናዎች ብዙም ገንዘብ የማያስወጡ አማራጮች ሊያደርጋችው ይችላል።

ከፍተኛ የማሽተት ችሎታ

እንስሳት በሽታዎች መከሰታቸውን መለየት የሚችሉት እንዴት ነው?

ይህ የሚሆነው በአንድ ሰው ውስጥ ያለውን ጥቃቅን ኬሚካላዊ ለውጦች የመለየት ባላቸው ተፈጥሯዊ ችሎታ ምክንያት ነው።

ውሾችን፣ አይጦችን እና ንቦችን ጨምሮ በርካታ የእንስሳት ዝርያዎች ቮላታይል ኦርጋኒክ ኮምፓውንድስ የሚባሉትን ወደ አየር የሚለቀቁ ጋዞችን እንዲሁም ውህዶችን ጠረኖች መለየት ይችላሉ።

እነዚህ ጠረኖች ጤነኛ የሆነ ሰውም ከሰውነቱ በአነስተኛ መጠን የሚለቃቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

ከሰው ልጅ በትንፋሽ መልክ የሚወጣው አየር ወደ 3500 የሚጠጉ ቮላታይል ኦርጋኒክ ኮምፓውንዶችን የያዘ ነው።

ከሰውነት የሚለቀቁት እነዚህ ጋዞች እንደ አንድ ሰው የጤና ሁኔታ የሚለዋወጡ ሲሆን፣ ጤነኛ ባልሆነ ሰው ዘንድ አሊያም ከበሽታ ጋር እየታገለ ያለ ሰው የእነዚህ ውህዶች ጠረን የተለየ ይሆናል።

በነገራችን ላይ የእነዚህ እንስሳት በሽታዎችን የመለየት ችሎታ የሚጠቅመው ለሰው ልጆች ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ሲ ኢሌጋንስ ትል (ሲ ዎርም) ከሰው ከተወሰዱ ናሙናዎች የካንሰርን በሽታ ብቻ አይደለም የሚለየው።

ሲ ዎርም ባለው የአካላዊ እና የአካል ክፍል ለውጦችን የማወቅ ችሎታው ከውሾች እና ከድመቶች የተወሰዱ ናሙናዎች ውስጥ በሽታዎችን መለየት ይችላል።

የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎች በተለይም የሠለጠኑ በሽታ አነፍናፊ እንስሳት፣ በሽታዎችን በትክክል በመለየት ችሎታቸው ውጤታማ፣ ጎጂ ያልሆኑ፣ ብዙ ገንዘብ የማይፈጁ እና ፈጣን በሽታ የመለያ መንገድ ሆነዋል።

በሰዎች እና በእንስሳት መካከል አዎንታዊ የሆነው ይህ ግንኙነት ከዚህ በላይም ሊያድግ ይችላል።

አሁን ላይ ባሉ ሕጎች ምክንያት እንስሳት በሽታዎችን የመለያ መንገድ ተደርገው ጥቅም ላይ የሚውሉት ከሕክምና ዘዴዎች ጋር በማቀናጀት ነው። ሆኖም የሕጉ ማዕቀፍ የሚፈቅድ ከሆነ አነፍናፊ እንስሳት አንድ ቀን ወሳኝ የሕክምና አካል ሊሆኑ ይችላሉ።

አነፍናፊ ውሾች ኮቪድ-19ን ለመለየት ከተለመደው ‘ፒሲአር ምርመራ በበለጠ ፈጣን እና ርካሽ ነበሩ። እንስሳት ያላቸውን በሽታዎች የመለየት ችሎታ በመረዳት እና አስገራሚ ችሎታቸውን ተግባር ላይ በማዋል በቤተ ሙከራ የሚሠሩ ምርመራዎችን በተሻለ መልኩ ማሻሻልም ይቻላል።

ሆኖም እነዚህን እንስሳት ለዚህ ዓላማ ጥቅም ላይ ስናውል ጤናቸው እና ደኅንነታቸው ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም መዘንጋት የለበትም። የሠለጠኑ እንስሳት ሥነ ምግባር ጉዳይም ሁልጊዜም ቢሆን ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል።