ከአህያ ወተት የሚገኘው እና አንድ ኪሎ 170 ሺህ ብር የሚሸጠው አይብ

ሰርቢያ ውስጥ ከአህያ ወተት የሚገኝ አንድ ኪሎ ግራም አይብ 1200 ዩሮ ይሸጣል። ይህ ዋጋ ከአማካይ ሰርቢያዊያን ወርሀዊ ደመወዝ ላቅ ያለ ነው።

አይቡ የሚሸጠው ዛሳቪቻ በተባለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ግቢ ውስጥ ነው።

ይህ ግቢ ከዋና ከተማዋ ቤልግሬድ በስተምዕራብ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

"አንድ ኪሎ ግራም አይብ ለማግኘት 25 ሊትር ወተት ያስፈልጋል። አንዲት አህያ ይህን ያክል ወተት የምታመርተው በአንድ ዓመት ተኩል ነው" ሲሉ የግቢው ኃላፊ ቩክ ሲሚች ለቢቢሲ ይናገራሉ።

እርግጥ ነው ስፔን ውስጥ የሚመረተው ካብራሌስ ተባለው ሰማያዊ አይብ (ብሉ ቺዝ) እጅግ ውዱ ነው።

በ2024 2.5 ኪሎ ግራሙ 36 ሺህ ዩሮ መሸጡ ይታወሳል። በዚህም በዓለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ሊሰፍር በቅቷል።

በሰርቢያ ከአህያ ወተት የሚገኘውን አይብ መግዛት የሚችሉት ኪሳቸው ደለብ ያለ ሰዎች ብቻ ናቸው።

ሰርቢያዊው የቴኒስ ኮከብ ኖቫክ ጆኮቪች ለሬስቶራንቶቹ እንዲሆን በሚል ለአንድ ዓመት የሚበቃ የአህያ አይብ መግዛቱ ይነገራል።

የቀድሞው የዛሳቪቻ ተፈጥሮ ጥበቃ ኃላፊ ስሎቦዳን ሲሚች እንደሚሉት ጆኮቪች ግማሹን ኪሎ 480 ዩሮ ነው የሸመተው።

የአህያዎች ገነት

36 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ ያረፈው ዛሳቪቻ ሌሎች ቦታዎች የማይገኙ ዕፅዋት እና የእንስሳት ዝርያዎችን እንዲሁም አእዋፍን ያቀፈ ግቢ ነው።

ነገር ግን ግቢው የሚታወቀው በአህያዎቹ ነው። 300 አህያዎቹ ያሉት ሲሆኑ በደቡብ ምስራቅ አውሮፓ ትልቁ የአህያ ማዕከል ነው።

ራሳቸውን ያልቻሉ ውርንጭላዎች እናታቸውን ታከው ቆመዋል። ሥራ የማይጠበቅባቸው አህያዎች ደግሞ፣ ጭነት የማያውቀው ጀርባቸውን ምግባቸው ላይ አሳርፈዋል።

ምንም እንኳ አህያ በባህሪው ግትር ነው ቢባልም በጣም ሩህሩህ እና መግባባት የሚችል እንስሳ ነው።

"እያንዳንዱ አህያ የራሱ የሆነ ባሕሪ አለው" ይላሉ የአህያዎች ማሳደጊያ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ኒኮላ ኒሊች።

"አንዳንዶች ጨዋታ ወዳድ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ ቁጥብ ናቸው። ነገር ግን ሁሉም መታቀፍ ይወዳሉ። አይብዛ እንጂ" ይላሉ።

ከ300 አህያዎቹ አንድ ደርዘን የሚሆኑት ብቻ ናቸው ወንዶች።

ሴት አህያዎች ከወለዱ ከ9 ቀናት በኋላ ለስርያ ዝግጁ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ወተት ለመስጠት ዝግጁ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

ነገር ግን አህያዎች ወተት የሚሰጡት ውርንጭላ ሲኖራቸው ብቻ ነው። እንደዛም ሆኖ የሚሰጡት የወተት መጠን እጅግ አናሳ ነው።

"አንዲት ሴት አህያ በቀን የምታመርተው 300 ሚሊሌትር ወተት ብቻ ነው። የአንድ የውሀ ብርጭቆ መጠን ያክል ማለት ነው።"

ከዚህ ላይ ግማሹን የሚጠጡት ውርንጭላዎች ናቸው። ይህ ማለት በቀን የሚገኘው የወተት መጠን እጅግ አናሳ ነው ማለት ነው።

ከአህያ ወተት የሚገኘውን አይብ ምን ልዩ ያደርገዋል?

የአህያ አይቡን ልዩ የሚያደርገው ምንድነው? ውስጡስ ምን አዝሏል? ተብሎ የተጠየቁት ኒኮላ ኒሊች በፈገግታ ይመልሳሉ።

"እሱን እንኳ ይፋ አላደርግም።"

ከአህያ ወተት አይብ ማምረት የሚለው ሐሳብ የመነጨው በቩክ ሲሚች አባት ስሎባዳን ሲሚች አማካይነት ነው።

የአህያ ወተት ልክ እንደ ሰው ልጅ ወተት ያለ ሲሆን በቀላሉ የሚወፍር አይደለም። ይህ ማለት አይብ ማምረት ቀላል አይሆንም ማለት ነው።

ነገር ግን ከብዙ ሙከራ በኋላ የዛሳቪቻ የምግብ ኢንጀነሮች አይብ የማምረቱን ጥበብ ተካኑት።

"የአይቡ ጣዕም የሚገኝ አይደለም" ይላሉ ሲሚች። "ማለት የምችለው ጣዕሙ ውድ ነው ብቻ ነው።"

ምንም እንኳ ይህ ከአህያ ወተት የሚገኝ አይብ እጅግ ተፈላጊ ቢሆንም ለሕዝቡ የሚሸጥ አሊያም ወደ ውጭ የሚላክ አይደለም።

መግዛት የሚቻለው ከዛሳቪቻ ብቻ ነው። ግቢው ውስጥ የሚገኘው ሬስቶራንት ውስጥም አይሸጥም። መግዛት የሚሹ አንድ አነስተኛ ሱቅ መሔድ አለባቸው።

"በዓመት ከ25 እስከ 30 ኪሎ ግራም ብቻ ነው የምናመርተው። ለዚህ ነው በቀላሉ የማይገኝ ምርት የሆነው" ሲሉ ሲሚች ያብራራሉ።

አዝጋሚ ምርት

ሰርቢያ የተለያዩ የአህያ ማሳደጊያ እርሻዎች አሏት። ነገር ግን አብዛኛዎቹ አይብ ሳይሆን ወተት ነው የሚሸጡት ይላል ከሰርቢያ የአርብቶ አደሮች ማኅበር የተገኘው መረጃ።

የአህያ ወተት ምርቱ ለአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ይህ ነው የሚባል አስተዋፅዖ የለውም ሲል የሰርቢያ ንግድ ምክር ቤት ለቢቢሲ ተናግሯል።

ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከአህያ የሚገኝን ወተት በሰፊው ማምረት ትርፋማ ስላልሆነ ነው።

ይህን አይብ ወደ ውጭ ሀገር መላክ የማይቻለው ደግሞ እንዴት እንደሚመረት ምስጢራዊ ቀመሩ ያለው ዛሳቪቻ ግቢ ውስጥ ብቻ በመሆኑ ነው።

"ለጊዜው ለማንም ላለማጋራት ቆርጠናል" ሲሉ ሲሚች ያስረግጣሉ።

ምንም እንኳ ከዓለም አቀፉ ገበያ ፍላጎት ቢኖርም ሲሚች ወደ ውጭ መላክ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

"በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች ስለኛ እየሰሙ ነው። እኛ የምናመርተውን አይብ ሁሉ ለገበያ ነው የምናቀ ርበው" ይላሉ።

ነገር ግን ሲሚች እንደሚያምኑት አብዛኛዎቹ ደንበኞቻቸው ብር ያላቸው የውጭ አገራት ዜጎች ናቸው።