አሜሪካ በየመን የሁቲ አማፂያን የሚገኙበትን በርካታ ስፍራዎች ደበደበች

የፎቶው ባለመብት, DVIDS
የአሜሪካ ጦር በኢራን የሚደገፉ እና በየመን የሚንቀሳቀሱ የሁቲ ታጣቂዎች የሚጠቀሙባቸውን 15 ቦታዎች መደብደቡን አስታወቀ።
ፔንታጎን የአየር ኃይሉን እና የጦር መርከቡን በመጠቀም “የውቅያኖስ ላይ እንቅስቃሴን ለመከላከል” በሚል ጥቃቱን መክፈቱን አስታውቋል።
ሰንዓን ጨምሮ በተወሰኑ የየመን ከተሞች በርካታ ፍንዳታዎች ተሰምተዋል።
ከባለፈው ዓመት ሕዳር ወር ጀምሮ የሁቲ ታጣቂዎች በቀይ ባሕር ላይ በሚቀዝፉ ከ100 በላይ መርከቦች ሲያጠቁ ሁለቱን ደግሞ ማስመጣቸው ይታወሳል።
የአማፂ ቡድኑ ጥቃቱን የከፈቱት እስራኤል በጋዛ የምታካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ በመቃወም ነው።
በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካን ወታዳራዊ እንቅስቃሴ የሚከታተለው ማዕከላዊ ዐዕዝ እንዳለው ከሆነ የአየር ድብደባው ዒላማ ያደረገው የጦር መሳርያ የሚገኝባቸውን፣ የጦር ካምፖች እና የሁቲዎች ንብረት የሆኑ መሳርያዎች ያሉባቸውን ስፍራዎች ነው።
ለሁቲ ቅርበት ያለው አንድ መገናኛ ብዙኀን በአሜሪካ የአየር ጥቃት ከተመቱት ከተሞች መካከል የየመን ዋና ከተማ ሰንዓ ትገኝበታለች።
ሰኞ ዕለት ሁቲዎች አሜሪካ ሰራሽ የሆነ ሰው አልባ አውሮፕላን መትተው መጣላቸውን ተናግረው ነበር።
አሜሪካም ሰው አልባ አውሮፕላኑ ተመትቶ እንደወደቀባት አረጋግጣለች።
ባለፈው ሳምንት ፔንታጎን እንዳለው ከሆነ የሁቲ አማፂያን በቀጠናው በሚገኘው የአሜሪካ የጦር መርከብ ላይ “የተቀናጀ ጥቃት” ቢከፍቱም የተኮሷቸው መሳርያዎች ሁሉ ዒላማቸውን ከመምታታቸው በፊት ከሽፈዋል።
ሁቲዎች በቀይባሕር ላይ የሚንገሳቀሱ መርከቦቸን ከማጥቃታቸው ባሻገር በቀጥታ ወደ እስራኤል ሚሳዔሎችን በማስወንጨፍ እነዲሁም የድሮን ጥቃትም ይፈጽማሉ።
በሐምሌ ወር ከየመን የተነሳ ድሮን በቴልአቪቭ አንድ ሰው ሲገድል 10 አቁስሏል።
ባለፈው ወር ቡድኑ በቴልአቪቭ የሚገኝ ዋና አየር ማረፍያን ዒላማ ያደረገ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ሚሳዔሎችን ወደ እስራኤል አስወንጭፏል።
እስራኤል ከሁቲ አማፅያን ለሚደርስባት ጥቃት በሙሉ አጸፋዊ ምላሽ ስትሰጥ ቆይታለች።
ባለፈው ዓመት መጀመርያ ላይ አሜሪካ፣ ዩኬ እና 12 ሌሎች አገራት በቀይ ባሕር ላይ ያለውን የመርከቦች ዝውውር ከሁቲ አማፂያን ጥቃት ለመጠበቅ በሚል በጋራ ጥቃት ከፍተው ነበር።
ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ ከምትደግፋቸው አማፂያን መካከል ሄዝቦላ በሊባኖስ፣ ሐማስ በጋዛ፣ ሁቲዎች ደግሞ በየመን ይገኛሉ።












