በኢትዮጵያ በየትኞቹ አካባቢዎች ድርቅ ተከስቷል?

በምሥራቅ አፍሪካ ለተከታታይ አምስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ በመጥፋቱ በአርባ ዓመታት ውስጥ ያልታየ ድርቅ ተከስቷል።

በዚህም ከ36 ሚልዮን በላይ ሰዎች በድርቁ ምክንያት እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል። ከሁለት ሚልዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን ለማትረፍ ከቀያቸው መሰደዳቸውን የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይኦኤም) ሪፖርት ያመለክታል።

ከእነዚህ አስቸኳይ እርዳታ ፈላጊ ሰዎች 24 ሚልዮኑ በኢትዮጵያ የሚገኙ ናቸው። በድርቅ ምክንያት ከተፈናቀሉት መካከል ደግሞ ከ500 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ድርጅቱ ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) በበኩሉ ግጭት፣ ድርቅ፣ የኑሮ ውድነት እና የምግብ ዋጋ መጨመር ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው መፈናቀል ጀርባ ያሉ ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ያስረዳል።

ዓለም አቀፉ የምግብ ድርጅት በበኩሉ 11.8 ሚልዮን ኢትዮጵያውያን በድርቅ ምክንያት አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ጥር ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት ጠቁሟል። ቁጥሩ በ2022 ከነበረው ጋር በ59 በመቶ ከፍ ብሏል።

የዝናብ እጥረቱ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በሶማሌ ክልሎች ለአስርት ዓመታት ያልታየ ከባድ ድርቅን አስከትሏል።

ከሰሞኑም የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) በግጭት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እርዳታ ጠባቂ ለሆኑ ኢትዮጵያውን ድጋፍ ለማድረግ ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ መግለጹ ይታወቃል።

ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በየትኞቹ አካባቢዎች ድርቅ ተከስቷል?

ቦረና

በኦሮሚያ ክልል ቦረና በዞኑ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች በተመሳሳይ መጠን በድርቁ መጎዳታቸው ተገልጿል።

በዚህም ሳቢያ ለሰዎች ሕይወት ለአደጋ መዳረጉን እንዲሁም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የነዋሪው የኑሮ መሠረት የሆኑ ከብቶች እና ሌሎች የቤት እንስሳት ሜዳ ላይ ወድቀው ቀርተዋል። በርካታ ነዋሪዎችም መቶዎች የሚቆጠሩ ከብቶቻቸውን በድርቁ ምክንያት አጥተው ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል።

ለምሳሌም የተልተሌ ወረዳ ነዋሪው ቱራ ሮባ ከ150 ከብቶቻቸው ሁሉም ከብቶች አልቀው አራት ብቻ እንደቀሯቸው ተናግረዋል።

በዞኑ 867 ሺህ 140 የሚሆኑ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ተለይቷል።

“ከ200 ሺህ በላዩ እስካሁን ምንም እርዳታ አልደረሳቸውም። ይህ ደግሞ በቂ የምግብ እርዳታ አቅርቦት ስለሌለ ነው” ሲሉ የቦረና ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኃላፊ አቶ ሊበን ሳራን አስታውቀዋል።

ሶማሌ ክልል

በሶማሌ ክልል በተለይም በዳዋ፣ አፍዴራ እና ሊበን ዞኖች በተመሳሳይ ድርቅ ተከስቷል።

በዳዋ ዞን በ92 መጠለያ ጣቢያዎች ከ52 ሺህ በላይ ተፈናቃይ የቤተሰብ አባላት ተጠልለው እንደሚገኙ የክልሉ ሕዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲቃድር ረሺድ ገልጸዋል።

በአፍዴራ እና ሊበን ዞኖች ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀል ባለመጀመራቸው ባሉበት ቦታ ድጋፍ እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል።

“በዳዋ ዞን ብቻ ግመል፣ ከብት እና ፍየልን ጨምሮ ወደ 334 ሺህ እንስሳት ሞተዋል። ከ420 ሺህ በላይ እንስሳት ደግሞ ወደ ሞት እየተቃረቡ ነው” ያሉ ሲሆን ከዳዋ ውጪ ባሉት ዞኖች የእንስሳት ሞት አልጀመረም ብለዋል።

ከሶማሌ ክልል አቀማመጥ እና የአየር ፀባይ ጋር በተያያዘ የውሃ እጥረት በመኖሩ፣ የውሃ እጥረት ሲከሰት ቀድመው የሚጎዱት እንስሳቶች ናቸው የሚሉት አቶ አብዲቃድር፤ በክልሉ ድርቅ በተከሰተባቸው ሦስቱ ዞኖች የእንስሳት መኖ አዳርሰናል ብለዋል።

ምሥራቅ ሐረርጌ

በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የተከሰተው ድርቅ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በቅርቡ አንድ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግቦ ነበር፡፡

የውሃ ፤ የጤና እና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ እንደሚያስፈልጉም የኢትዮጵያ ህጻናት አድን ድርጅት አሳውቋል።

“የተከተሰው ድርቅ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ በመሆኑ በ35 ወረዳዎች ላይ ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው” ሲሉ የድርጅቱ የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሚዲያ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ አብዱራዛቅ አህመድ ገልጸዋል።

በድርቁ ምክንያት ከሁለት ሚሊዮን በላይ እንስሳት መሞታቸውም ተዘግቧል፡፡

ድርቁ በሰዎች እና በእንስሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልጸው በዚህ ምክንያት ግን እስካሁን የሞተ ሰው ስለመኖሩ ያገኙት መረጃ እንደሌለ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ደቡብ ኦሞ

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በድርቅ ምክንያት 14 ሺህ ከብቶች ሲሞቱ፣ እንዲሁም ከ337 ሺህ በላይ ሕዝብ ለምግብ እጥረት ተጋልጧል።

በዞኑ በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች በተከሰተ ከባድ ድርቅ ከሞቱት የቤት እንስሳት በተጨማሪ 2.3 ሚሊዮን ከብቶች ክፉኛ ተዳክመዋል። መንቀሳቀስ ባለመቻላቸውም ባሉበት ቦታ ሆነው መኖ እየቀረበላቸው ይገኛል ሲሉ የዞኑ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዱባ የራ አስታውቀዋል።

“ከ337 ሺህ ሰዎች በላይ የምግብ ችግር አጋጥሟቸዋል” ብለዋል አቶ ዱባ።

በደቡብ ኦሞ ከሚገኙ 13 ወረዳዎች መካከል በማሌ፣ በና ጸማይ፣ ሐመር፣ ዳሰነች፣ ኛንጋቶም እና ስላማጎ ወረዳዎች “ከፍተኛ ችግር ተከስቷል።”

የበና ጸማይ፣ የአሌ እና የሐመር ወረዳዎች የውሃ ምንጭ የነበረው የወይጦ ወንዝ በመድረቁም በወረዳዎቹ የውሃ እጥረት ተከስቷል።

አቶ ዱባ በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ እስካሁን በሰው ሕይወት ላይ ያደረሰው ጉዳት ስለመኖሩ ሪፖርት አለመደረጉን ገልጸዋል።

“ዝናብ እየዘነበ አይደለም። ከብቶቻቸው እየሞቱ ነው። ሰው ወደ እርሻ ሥራው እየገባ አይደለም” ያሉት ኃላፊው ለተቸገሩት ሰዎች እርዳታ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የጎፋ ዞን ወረዳዎች

በምርታማነታቸው በሚታወቁት የጎፋ ዞን ዛላ፣ ኡባ ደብረ ፀሐይ፣ ደንባ ጎፋ ማምረት ቀርቶ ለዕለት ጉርሳቸው ያጡ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።

በዛላ ወረዳ ከሚገኙ 15 ቀበሌ ነዋሪዎች ከግማሽ የሚበልጡት የሚላስ የሚቀመስ አጥተዋል።

የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም ዞራን ጠቅሶ ሪፖርተር እንደዘገበው በወረዳዎቹ ባሉ ቆላማ ቀበሌዎች ባለፈው የበልግ ወቅት 233 ሺህ ቤተሰብ የአስቸኳይ ዕርዳታ ያስፈልገዋል።

ከየካቲት እስከ ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ከዞኑ ለከፋ ጉዳት የተጋለጡትን በመለየት 169 ሺህ ቤተሰብ ዕርዳታ እንዲያገኙ መደረጉን አቶ አብርሃም ጠቁመዋል።

ከሰኔ 2014 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም. ድረስ በወረዳዎቹ ከፍተኛ የሆነ የዝናብ እጥረት ማጋጠሙንም ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት በተለይ በዛላ ወረዳ የሚገኙ 15 ቀበሌዎች እና በኡባ ደብረ ፀሐይ ወረዳ በሚገኙ አምስት ቀበሌዎች ሰብሉ ሙሉ ለሙሉ መጥፋቱን አመልክተዋል።

በደንባ ጎፋ ወረዳ የሚገኙ ቆላማ ቀበሌዎች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የምርት መቀነስ ቢያጋጥምም ችግሩ የጎላው በዛላ ወረዳ ነው።

በመኸር ወቅት በዞኑ 74,000 ሔክታር በሰብል ቢሸፈንም 54 በመቶ የሚሆነው ምርት እንደመከነ አስረድተዋል።

በዚህም በዞኑ 155 ሺህ 247 ሰዎች የዕለት ጉርስ ፈላጊ ሆነዋል።

የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማኖቴ በዛላ ወረዳ 4,288 ሕፃናት በተመላላሽ የምግብ እጥረት ሕክምና እየተሰጣቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከሦስት ሺሕ በላይ የሚያጠቡ እናቶችና ነፍሰ ጡሮች ደግሞ በሕክምና ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ኃላፊው ጠቁመዋል።

የመንግሥት ምላሽ

መንግሥት ድርቅን ጨምሮ በተፈጥሯዊ እና በሰው ሠራሽ ችግሮች ለተጎዱ 21 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እያቀረበኩ ነው ብሏል።

እስካሁን በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ አደጋ ለተጎዱ 21 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እየቀረበ ነው ሲሉ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴን መግለጻቸውን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።

ቁጥሩ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ድጋፍ እየተደረገላቸው የሚገኙ 8 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎችን እንደሚያካትት ተጠቅሷል።

በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ መንግሥት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውም ተገልጿል።

ባለፉት ሁለት ወራት በቦረና 204 ሺህ 756 ኩንታል ምግብ ማቅረብ መቻሉን አቶ ደበበ ገልጸዋል።

በክልሉ የሚመራና ሁሉንም ሴክተር ያካተተ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ያቤሎ ላይ መቋቋሙንም ተናግረዋል።

ተጋላጭ ለሆኑ ሕጻናት፣ ነፍሰጡሮች፣ አጥቢ እናቶች እንዲሁም አቅመ ደካሞች መንግሥት አስር ኩንታል አልሚ ምግብ በአስራ ሦስት ወረዳዎች ተሰራጭቷል።

መንግሥት ሰብዓዊ ድጋፍ ከሚያደርጉ አካላት ጋር ግንኙነት በማድረግ ላይ መሆኑም ተገልጿል።

በዚህም በትግራይ፣ በአፋር እና በአማራ ክልሎች ድጋፍ ለማድረግ 29 አጋር አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ድርቅን ጨምሮ በሰው ሠራሽ ችግሮች የተጎዱ ዜጎችን ለመርዳት ኅብረተሰቡ ድጋፍ በማሰባሰብ እንዲረባረብም ጥሪ አቅርበዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ቢቢሲ ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።