ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአፍሪካ ቀንድ ድርቅ ከ20 ሚሊዮን በላይ ህጻናትን ለከፋ ችግር መዳረጉን ተመድ አስታወቀ
በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለከፍ ችግር የተጋለጡ ህጻናት ቁጥር በአምስት ወራት ውስጥ ከእጥፍ በላይ መጨመሩ የተባበሩት መንግሥት የህጻናት አደን ድርጅት ዩኒሴፍ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በአየር ንብረት ለውጥ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የዋጋ ግሽበት፣ በግጭትና በእህል ምርት እጥረት ምክንያት ለከፋ ርሃብና ውሃ ጥም እንዲሁም ለበሽታ የመጋለጥ ስጋት ያለባቸው ህጻት ባለፈው ሃምሌ ወር ከነበረበት 10 ሚሊዮን ወደ 20.2 ሚሊዮን አሻቅቧል።
የዩኒሴፍ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ኃላፊ ሊኬ ቫን ዴዊሊ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት ድርቁ ያስከተለውን ችግር ለመቅርፍ የሚደረገው ጥረት ዝቅተኛ በመሆኑ በምስራቅ አፍሪካ አስከፊ ድርቅ ከሁለት ትውልዶች በላይ ዘልቋል ብለዋል።
“በርሃብ እና በሽታ ምክንያት ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው እና ወደ ሞት ጠርዝ እየተገፉ፤ ምግብ፣ ውሃ እና የግጦሽ ሳር ፍለጋ እየተሰደዱ ያሉ ሕጻናትንና ቤተሰቦቻቸውን ህይወት ለመታደግ እና ችግሮችን የመቋቋም አቅማቸወን ለማጠናከር የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት ሊቀጥል ይገባዋል” ሲሉም አክለዋል።
በሶስቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሕጻናት በከፍ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ስላጋጠማቸው አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ይታመናልም ብሏል - ዩኒሴፍ።
በተጨማሪም ቤተሰቦች ድርቁ እየፈጠረባቸው ባለው ጫና ምክንያት የሚደርግላቸው ጥበቃ አደጋ ላይ ወድቋል። ይህም የጉልበት ብዝበዛ፣ የህጻናት ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ከፍ እንዲል አድርጓል።
በሌላ በኩል ጾታዊ ጥቃትና ብዝበዛ ጨምሮ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ እና መፈናቀሉ እንዳባባሰው ዩኒሴፍ ጠቁሟል።
ዩኒሴፍ አጋሮቹና ለጋሾች በሚያደርጉለት ድጋፍ በአፍሪካ ቀንድ ሕይወት አድን የሆኑ አገልግሎቶችን እያቀረበ እንደሆነም አመላክቷል።
በኢትዮጵያ፥ በኬንያና በሶማሊያ የዝናብ እጥረት ለ5 ተከታታይ ጊዜያት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተከሰተው ድርቅ እና ለቀጣዩወ ውቅት የተሰጠው ትኩረት ማነስ የገንዘብ እጥረት ሊያጋጥም እንሚችለም አሳስቧል።
እየተገባደደ ባለው የፈረንጆቹ ዓመት ድርጅቱ ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናትና ሴቶችን በህይወት አድን ህክምና ተደራሽ አድርጌያለሁ ያለ ሲሆን ከ6 ወር እስከ 15 ዓመት ያሉ 2 ሚሊዮን ህጻናት የኩፍኝ ክትባት ወስደዋል ብሏል።
2.7 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ለመጠጥ፣ ምግብ ለማብሰል እና ለንጽህና የሚውል ንጹህ ውሃ እንዳከፋፈልም ጠቁሟል።
ደርጅቱ ለቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት ለህይወት አድን ስራዎች እና ለሌሎች ተግባራት 759 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ያለ ሲሆን ተጨማሪ 690 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘና ሌሎች ዘላቂ ተግባራትን ለመከወን እንደሚያስፈልግ አመላክቷል።
ኃላፊዋ በምስራቅ አፍሪካ ያለውን ድርቅ እና ያስከተለውን ችግር ለመፍታት መንግስታት ድጋፍ እንዲያደርጉ የጠየቁ ሲሆን “በአፍሪካ ቀንድ ህጻናት ላይ ሌላ አስከፊ እና የማይቀለበስ ጥፋትን ለመቀነስ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ድጋፍ እንፈልጋለን። የህጻናትን ህይወት ለመታደግ፣ ክብራቸውን ለመጠበቅ እና መጻኢ እድላቸውን ለመጠበቅ አሁኑኑ እርምጃ ልንወስድ ይገባል” ብለዋል።
በኢትዮጵያ፣ኬኒያና ሶማሊያ ስለተከሰተው ድርቅ አህዞች ምን ይላሉ?
- በድርቁ ምክንያት ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ሆነዋል
- ወደ 24 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የውሃ እጥረት ገጥሟቸዋል፤ የውሃ ዋስትናቸውን ያለረጋገጡ ሰዎች ከእጥፍ በላይ ጨምሯል
- ወደ 2.7 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጸናት በድርቁ ምክንያት ትምህርት አቋርጠዋል
- 4 ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ትምህርት የማቋረጥ ስጋት ተደቅኖባቸዋል