ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቭላድሚር ፑቲን ላይ አመጽ ቀስቅሶ የነበረው የቫግነር ቡድን ትጥቅ ሊፈታ ነው ተባለ
ባለፈው ቅዳሜ በቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ላይ አመጽ ቀስቅሶ ሩሲያን ለ24 ሰዓታት ትርምስ ውስጥ ከቷት የነበረው ቫግነር ቅጠረኛ ተዋጊ ቡድን የከባድ መሳሪያ ትጥቅ ሊፈታ ነው ተባለ።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ቫግነር የከባድ ጦር መሳሪያዎችን እንዲያስረክብ ቅድመ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው ብሏል።
ይህ የተባለው በወታደራዊ አመጻ ተግባር ላይ ተሳታፊ የነበሩት የቫግነር አባላት ክስ እንደማይመሰርትባቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዛሬ ከሰዓት ባደረጉት ንግግር የቫግነር አባላትን ወደ ወንጀል ተግባር ተሳስተው እንዲገቡ የተደረጉ “እውነተኛ አገር ወዳድ ተዋጊዎች ናቸው” ብለዋል።
አክለውም የቡድኑ አባላት ካሻቸው ወደ መደበኛ ጦር ሠራዊት መቀላቀል፣ ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ አልያም ወደ ቤላሩስ ማቅናት ይችላሉ ብለዋል።
ፑቲን 2500 የሚሆኑ ወታደሮችን፣ የፖሊስ አባላትን፣ የሩሲያ ብሔራዊ ዘብ እና የደኅንነት ኃላፊዎችን ሰብስበው ስለታማኝነታቸው እና አመጹን ስለማስቆማቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ፑቲን ንግግራቸውን ሲያደምጡ ለነበሩት፤ “የሩሲያን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት አስከብራችኋል፣ የሩሲያውያን ሕይወት እና ነጻነት አስጠብቃችኋል” ካሏቸው በኋላ “የእርስ በርስ ጦርነት አስቁማችኋል” ሲሉ አሞግሰዋቸዋል።
ቫግነር የተባለው ቅጠረኛ ተዋጊ ቡድን የቀስቀሰውን አመጽ ለማስቆም ስለተደረሰው ስምምነት ግን ፑቲን በንግግራቸው ያሉት ነገር የለም።
በየቭጌኒ ፕሪጎዢን የሚመራው ቫግነር ባሳለፈው ቅዳሜ በሩሲያ የጦር አመራሮች ላይ በይፋ ካመጸ በኋላ፣ ሁለት የሩሲያ ከተሞችን ተቆጣጥሮ ወደ ሞስኮ ሲገሰግስ ነበር።
የቡድኑ መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በዩክሬኑ ጦርነት “ስህተት” የፈጸሙ የጦር አመራሮች ለመቅጣት ወደ ሞስኮ “ለፍትሕ” ሲል እንደሚያመራ ገልጾ ነበር።
ይሁን እንጂ የቡድኑ መሪ በቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሸማጋይነት ከፑቲን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ወደ ሞስኮ የሚያደርጉትን ዘመቻ አቁመው ወደ ቤላሩስ ማቅናታቸው ተገልጿል።
ዛሬ ከሩሲያ የወጡ ይፋዊ ሪፖርቶች በአመጹ ላይ ተሳታፊ በነበሩ የቫግነር አባላት ላይ ክስ እንደማይመሠረት አረጋግጠዋል።
የሩሲያ የአገር ውስጥ የደኅንነት ቢሮ (ኤፍኤስቢ) በአመጽ ተግባሩ ላይ የተሳተፉ ሰዎች ላይ ተመስርቶ የነበረው ክስ ሙሉ በሙሉ ውድቅ ተደርጎ መዝገቡ ተዘግቷል ብሏል።
የደኅንነት ቢሮው ዛሬ ይህን ይበል እንጂ ፕሬዝዳንት ቭላድርሚር ፑቲን ትናንት ምሽት በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው አመፅ ያነሱትን የቫግነር ቡድን አባላት አገራቸውን ለከባድ ጉዳት በማጋለጥ ተጠያቂ ይሆናሉ ብለው ነበር።
ፑቲን በትናንቱ ንግግራቸው “ሩሲያ በደም ጎርፍ ስትታጠብ ማየት የጓጉ” ናቸው ያሏቸውን የአመጹ መሪዎችን “ለፍትሕ” ይቀርባሉ ይበሉ እንጂ፣ በዛሬው ንግግራቸው የቫግነር አባላት ወደ ፈለጉት እንዲሄዱ አማራጮችን አቅርበዋል።
ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ሩሲያን በጠንካራ ክንድ የመሩት ቭላድሚር ፑቲን፣ አስተዳደራቸውን በመዳፈር አመጽ የቀሰቀሱባቸው ተዋጊዎችን በምህረት መልቀቃቸው ለብዙዎች ግርምንትን ፈጥሯል።
በየቭጌኒ ፕሪጎዢን የሚመራው ቡድን በሩሲያ የጦር አመራሮች ላይ በይፋ ካመጸ በኋላ፣ ሁለት የሩሲያ ከተሞችን ተቆጣጥሮ ወደ ሞስኮ ሲገሰግስ ነበር።
የቫግነር ቡድን አባላት በግስጋሴያቸው ወቅት ከሰባት ያላነሱ ወታደራዊ ሄሊኮፕተሮች እና አውሮፕላኖችን መትተው ጥለዋል።
በፑቲን አስተዳደር ላይ ወታደራዊ አመጽ ማስነሳት ቀርቶ፤ ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደችው ስላለው ወታደራዊ ዘመቻ ትችት የሰነዘሩ አክቲቪስቶች እና ፖለቲከኞች ረዥም ዓመታት በእስር እንዲያሳልፉ ወደ እስር ቤት ተወርውረዋል።
አሜሪካ ግን በሩሲያ የተከሰተው አመጽ በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ውስጥ ያለውን ትልቅ ክፍተት ያሳየ ነው ብላለች።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን፣ የቫግነር ቡድን በፈጸመው የአመጽ ድርጊት ፑቲንን “በቀጥታ በመገዳደር” ፕሬዝዳንቱ ለቡድኑ መሪ እና አባላት ይቅርታ አድርገው ከስምምነት እንዲደርስ ያስገደደ ነው ብለው ነበር።