ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፕሬዝደንት ፑቲን የቫግነር ወታደራዊ አመፅ አነሳሾች “ለፍትሕ መቅረባቸው አይቀሬ ነው” አሉ
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ አመፅ ያነሱትን የቫግነር ቡድን አባላት አገራቸውን ለከባድ ጉዳት በማጋለጥ ተጠያቂ ይሆናሉ አሉ።
ለአገራቸው ሕዝብ ንግግር ያሰሙት ፑቲን “ሩሲያ በደም ጎርፍ ስትታጠብ ማየት የጓጉ” ናቸው ያሏቸውን የአመጹ መሪዎችን “ለፍትሕ” ለማቅረብ ቃል ገብተዋል።
ነገር ግን ተራ የቫግነር ቡድን አባላትን “አገር ወዳድ” ናቸው፤ ጦር ኃይሉን መቀላቀል አሊያም ወደ ቤላሩስ ማቅናት፣ ከፈለጉም ወደቤታቸው መመለስ እንደሚፈቅድላቸው አሳውቀዋል።
ፑቲን የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን አለቃ የቭጌኒ ፕሪጎዢንን በስም ሳይጠቅሱ አልፈዋል።
ግለሰቡ እኔ በፍፁም ፑቲንን ከሥልጣን ልፈነቅል አላሰበኩም ሲል ከፕሬዝደንቱ ንግግር ቀደም ብሎ ድምፁን አሰምቶ ነበር።
ቫግነር ሩሲያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ የግል ወታደራዊ ኩባንያ ነው።
ቅጥረኛ ቡድኑ ከሩሲያ ወታደራዊ ኃይል ጋር ተጣምሮ ዩክሬን ውስጥ ባለው ጦርነት ሲሳተፍ ቆይቷል።
ቡድኑ ባለፈው አርብ ወደ ሞስኮ እየገሰገሰ መሆኑን አሳውቆ ሁለት ትላልቅ የሩሲያ ከተሞችን ተቆጣጥሮ ነበር።
ቫግነር ይህን ያደረገው የሩሲያ መንግሥት የቡድኑ ቅጥረኛ ወታደሮች በመከላከያ ሚኒስቴሩ ሥር መሆን አለባቸው ማለቱን ተከትሎ ነው።
ይህ እርምጃ ለፕሪጎዢን አስጊ ሆኖ እንደታየው ብዙዎች ይስማማሉ።
የቅጥረኛ ወታደሮች ቡድን መሪው ከዚህ አልፎ የዩክሬን ጦርነትን የሚመሩት ባለሥልጣናት ስህተት እየፈፀሙ ነው ብሎ ያምናል።
ቢሆንም ቫግነር ሁሌም ቢሆን የሩሲያን ፍላጎት ጠብቆ እንደሚንቀሳቀስ ደጋግሞ ሲናገር ይሰማል።
ፕሪጎዢን አመፁን አቋርጦ ወደ ቤላሩስ ለማቅናት ሲስማማ ምንም ዓይነት ክስ እንደማይመሰርትበት ቃል ተገብቶለታል።
ነገር ግን የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ግለሰቡ ምርመራ እየተደረገበት ነው የሚል ወሬ እያሰሙ ነው።
ሰውየው አመፁን ገትቶ ለማፈግፈግ የወሰነው የሩሲያ ወታደሮችን “ደም ላለማፍሰስ” እንደሆነ ገልጺ፣ አንዳንድ ሩሲያውያን ዘመቻው መቋረጡ እንዳሳዘናቸው መስማቱን ይናገራል።
እሱ እንደሚለው በፍፁም በምርጫ ሥልጣን የጨበጡ ባለሥልጣናትን የመፈንገል ሐሳብ የለውም።
ፕሪጎዢን ሐሳቡን በቴሌግራም የማኅበራዊ ገጽ ላይ በድምፅ ስለሚልክ የት እንዳለ እና ምን እያደረገ እንደሆነ ማወቅ የማይታሰብ ነው።
በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው ለሕዝባቸው አጠር ያለች ንግግር ያድረጉት ፑቲን፣ የዘመቻው አስተባባሪዎች “ለፍትሕ መቅረባቸው አይቀሬ ነው” ብለዋል።
ምንም እንኳ በስም ባይጠሩትም፤ ፑቲን አክለውም የቀድሞ ወዳጃቸው ፕሪጎዢንን “ሩሲያን ከጀርባ የወጋ” ሲሉ ገስፀውታል።
ፑቲን አደባባይ ወጥተው ንግግር ማሰማት የመረጡት ለወታደራዊው አመፅ የሰጡት ምላሽ ደካማ ነው መባሉን ለማስተባበል ይመስላል።
ተቀድቶ ወደቴሌቪዥን ጣቢያው የተላከው የፑቲን ንግግር አጠር ያለ እና ፈርጣማ ነው።
የፕሬዝደንቱ ዋነኛ መልዕክት የነበረው አመፅ ያነሳሱት አገራቸውን እና ሕዝባቸውን የካዱ ናቸው የሚል ነው።
የሩሲያ ጠላቶች ሊያደርጉ የሚያስቡትን ደም መቃባትን እና ክፍፍልን እንዴት አንድ ሩሲያዊ ሊያደርገው ይነሳሳል የሚል መልዕክት አለው።
የምዕራቡ ዓለም ሩሲያውያን “እርስ በርሳቸው እንዲጋደሉ” ይሻል ሲሉም ወቅሰዋል።
ነገር ግን የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አሜሪካም ሆነች አጋሮቿ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት የላቸውም ብለዋል።
ፑቲን በንግግራቸው ሩሲያውያንን እና የቤላሩሱን ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮን አመሰግነዋል።
ሉካሼንኮ በመንግሥት እና በቫግነር ቡድን መካከል ያለው ውጥረት እንዲረግብ እንዲሁም ፕሪጎዢን አመፁን እንዲተው እንዳስማሙ ይነገራል።