ፑቲን ላይ ያመጹት የቫግነር መሪ እንቅስቃሴያቸውን ለማቆም ተስማምተው ከአገር ወጡ

በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስተዳደር ላይ አመጽ አስነስተው ወደ ሞስኮ ሲገሰግሱ የነበሩት የቅጥረኛው ቫግነር ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን የጦር እንቅስቃሴያቸውን ለማቆም ተስማምተው ከአገር ወጡ።

የቫግነር መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ወደ ጎረቤት አገር ቤላሩስ ማቅናታቸው ነው የተገለጸው።

የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የቫግነር መሪን እና ፑቲንን ካነጋገሩ በኋላ የቅጠረኛ ቡድን መሪው እና ወታደሮቻቸው ላይ ክስ እንደማይመሰረት ከስምምነት ከተደረሰ በኋላ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ወደ ቤላሩስ አቀንተዋል።

የቅጠረኛ ቡድኑ መሪ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከትናንት በስቲያ አርብ ጀምሮ የሩሲያን መከላከያ ጦር ከፍተኛ አመራሮችን “ልክ አስገባለሁ” በማለት ሲዝቱ ቆይተዋል።

ይህ ቡድን ሩሲያ በዩክሬን እያደረገች ባለችው የጦር ዘመቻ ቁልፍ የሞስኮ አጋር የነበረ ቢሆንም ከቀናት በፊት ቡድኑ ከዩክሬን ድንበር ወጥቶ ወደ ሩሲያ ተመልሶ ሮስቶቮ ኦን ዶን የተባለች የሩሲያ ከተማን ተቆጣጥሮ ነበር።

ይህን ተከትሎ የክሬምሊን አስተዳደር ግለሰቡን ‘የወታደር አመጽ በማነሳሳት’ ከሶታል። ፕሬዝዳንት ፑቲን በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር ቫግነርን አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጡት ዝተው ነበር።

ፑቲን በዚህ አጭር ደቂቃዎችን በቆየ ንግግራቸው “ተክደናል- ከጀርባችን በጩቤ ተወግተናል’ ብለው ነበር።

የቫግነሩ መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በተደጋጋሚ እየተካሄደ ባለው ጦርነት በሩሲያ ወታደሮችና በርሱ ቅጥረኞች ላይ ለሚደርሰው ሰብዓዊ ኪሳራ የሩሲያ መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖችን ተጠያቂ ሲያደርጉ ቆይቷል።

ግለሰቡ በተለይ ከሩሲያ መከላከያ ሚንስትር ጋር ከፍተኛ የሆነ ቅራኔ አላቸው።

በዚህም የቭጌኒ ፕሪጎዢን ሮስቶቭ ከተማን መቆጣጠራቸው እና ወደ ሞስኮ ‘ለፍትሕ’ ሲባል ዘመቻ እንደሚያደርጉ ዝተው ነበር።

ይህን ተከትሎ ባለፉት 24 ሰዓታት በሞስኮ ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ ቆይቷል። ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት እንቅስቃሴ ትናንት ቅዳሜ በመዲናዋ ይታይ ነበር።

ግለሰቡ በወታደሮቻቸው ላይ ክስ እንደማይመሰረት ከተስማሙ በኋላ ወታደሮቻቸው ወደ ሞስኮ የሚያደርጉትን ግስጋሴ አቁመው ወደ ካምፓቸው እንዲመለሱ ካዘዙ በኋላ ወደ ቤላሩስ ማቅናታቸው ነገሮች በሩሲያ ወደ መረጋጋት የተመለሱ ይመስላል።

በሩሲያ የሆነው ምን ነበር?

ዓርብ

የቫግነር አለቃ በሩሲያ መከላከያ ሚንስትር ሰርጌይ ሾይጉ ላይ ክስ መመስረት ይጀምራሉ። የቭጌኒ ፕሪጎዢን መከላከያ ሚንስትሩ የዩክሬን ጦርነትን ያስጀምሩት እራሳቸውን በታሪክ መዝገቦች ላይ ጀግና ለማስባል ነው ሲሉ አጥብቀው ተቹ።

ከዛም ‘ለፍትሕ ሲባል’ ወደ ሞስኮ እንደሚዘምቱ ገለጹ። ቀጠል አድርገው ክሬምሊን ወታደሮቼን በሚሳኤል መታ አሉ። ከዛም በሩሲያ የጦር አመራሮች ላይ አመጽ ጠሩ።

የቫግነር እንቅስቃሴን ተከትሎ በሞስኮ ውጥረት ሆነ።

ቅዳሜ

የቫግነር አለቃ 25ሺህ ወታደሮቻቸው ከዩክሬን ወደ ሩሲያ መመለሳቸውን ገለጹ። የሞስኮ ከንቲባ በመዲናዋ የጸረ-ሽብር እርምጃዎች እንዲወሰዱ አሳሰቡ። የቫግነር ቡድን የተቆጣጠራት የሩሲያዋ የድንበር ከተማ ነዋሪዎች ደግሞ በቤት ውስጥ እንዲቆዩ ታዘዙ።

ትንሽ ቆየት ብሎ የቫግነር ወታደሮች በደቡብ ሩሲያ የሚገኘው ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ውስጥ ታዩ።

ከዛ ቀጥሎ የተከሰተው የቭላድሚር ፑቲን ጠንከራ ያለ ዛቻ አዘል ንግግር ነበር። ፑቲን በዚህ ንግግራቸው "ተክደናል-ተደፍረናል-ከጀርባ ተወግተናል" አሉ።

ትናንት ቅዳሜ የዋግነር ወታደሮች ወደ ሞስኮ በሚወስደው ኤም4 በተባለው አውራ ጎዳና ላይ ወደ መዲናዋ ሲገሰግሱ ታዩ።

ድንገት ሳይጠበቅ የቅጥረኛው ቫግነር ቡድን መሥራችና መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ወታደራዊ እንቀስቃሴያቸው ለማቆም መስማማታቸውን በቴሌግራም ገጻቸው አስታወቁ።

የቭጌኒ ፕሪጎዢን ወታደሮቻቸው ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ እና ወደ ካምፕ እንዲመለሱ አዘዙ።

በዚህ መሃል ቤላሩስ ፕሬዝዳንቷ አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ከፕሬዝዳንት ፑቲን እና ከ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ሲነጋገሩ መቆየታቸውን እና መሪዎቹ መስማማታቸውን አስታወቀች።

በሩሲያ ሰዓት አቆጣጠር ምሽት 3 ሰዓት አካባቢ የሩሲያ ቴሌቪዥን ጣቢያ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ከአገር ይወጣሉ ሲል ዘገበ። ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው የቫግነር መሪ ወደ ሩሲያ እንደሚያቀኑ እና በቡድኑ አባላት ላይ ክስ እንደማይመሰረት ይፋ አደረገ።