ፑቲን "ተክደናል-ተደፍረናል-ከጀርባ ተወግተናል" አሉ

በሞስኮ ውጥረት ነግሷል። ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት እንቅስቃሴ ከዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ እየታየ ነው።

በአንጻሩ የቫግነር ቅጥር ገዳይ ቡድን በደቡብ ሮስቶቭ የመከላከያ ዋና መሥሪያ ቤትን ተቆጣጥሯል።

ፍጹም ያልተጠበቀ ነው የተባለው ይህ የቫግነር ከሩሲያ መከላከያ እዝ አፈንግጦ ማመጽ ብዙ እያነጋገረ ነው።

የቫግነር መሪ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትርና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ሩሲያን ክደዋል ሲል ይከሳል።

ይህን ውጥረት ተከትሎ ቪላድሚር ፑቲን በብሔራዊ ቴሌቪዥን ለሕዝባቸው ንግግር አድርገዋል።

አምስት ደቂቃ ብቻ በቆየው ንግግራቸው ቫግነርን አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጡት ዝተዋል።

ወሳኝ ወታደራዊ እርምጃ ይወሰዳል ያሉት ፑቲን የቫግነርን መሪ በስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

የቅጥረኛው ቫግነር ቡድን መሥራችና መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን የፑቲን ቀኝ እጅና ታማኝ፤ ምግብ አብሳያቸው በኋላም ምሥጢረኛ ነበር።

ፑቲን በዚህ አጭር ደቂቃዎችን በቆየ ንግግራቸው ግን “ተክደናል- ከጀርባችን በጩቤ ተወግተናል’ ብለዋል።

መከላከያ እርምጃ እንዲወስድ መመሪያ እንደተላለፈለትም አስታውቀዋል።

በምዕራብ ሩሲያ የአካባቢ አስተዳዳሪዎች ነዋሪዎች ወደ ጎዳና እንዳይወጡና እንቅስቃሴያቸውን እንዲገድቡ አሳስበዋል።

የቫግነሩ መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በበኩሉ ሮስቶቭ ከተማን መዝጋቱን እና ወደ ሞስኮ እንደሚያመራም ዝቷል።

የቭጌኒ ፕሪጎዢን አመጹን የሚያቆመው መከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ መጥተው ካነጋገሩት ብቻ መሆኑን ጠቅሷል።

የሩሲያ ባለሥልጣናት በበኩላቸው የቭጌኒ ፕሪጎዢን ላይ ክስ ማዘዣ ቆርጠውበታል።

የቭጌኒ ፕሪጎዢን በተደጋጋሚ የሩሲያ መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች በዩክሬን በሩሲያ ወታደሮችና በርሱ ቅጥረኞች ላይ ለሚደርሰው ሰብአዊ ኪሳራ ተጠያቂ ሲያደርጋቸው ቆይቷል።

እርሱ እንደሚለው ከሆነ ከሰሞኑ በርሱ ታጣቂዎች ላይ በተወሰደ የሚሳኤል ጥቃት በርካታ ወታደሮቹ ተገድለውበታል።

ይህን ትእዛዝ የሰጡት ደግሞ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ናቸው ሲል ከባድ ክስ ያቀርባል።

የዩክሬን ጦርነት የተጀመረው ‘የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል ሾይጉ ‘ማርሻል ሾይጉ’ እንዲባሉና በታሪክ ስማቸውን ለማኖር ፈልገው ነው’ የሚል ጠንካራ ክስ አቅርቧል፤ ትናንት በቴሌግራም በተለቀቀ መልእክቱ።

በጄኔራል ሾይጉና በፕሪጎዢን መካከል ያለውን ጥላቻ ክሬምሊን በዋዛ ሲመለከተው ቆይቶ ነው አሁን ወደ አመጽ ያመራው።

ፕሪጎዢን በቴሌግራም ትናንት በለቀቀው መግለጫ "እኔና 25 ሺህ ወታደሮቼ ለመሞት ቆርጠናል" ብሏል።

ቫግነር በአሁኑ ሰዓት ደቡባዊቷን ከተማ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን እየገለጸ ነው።

የዩኬ መከላከያ ሚኒስትር የደኅንነት ክፍል ቫግነር የተወሰኑ ወታደሮቹ ወደ ሞስኮ እያመሩ እንደሆነ ደርሰንበታል ብሏል።

በሞስኮና በሮስቶቭ መካከል በምትገኘው ቮሬኔዝ ከተማ የቫግነር ተዋጊዎች ታይተዋል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው።

ፑቲን ዛሬ ጠዋት ባደረጉት ንግግር የዛሬውን እየሆነ ያለውን ክስተት በ1917 ከሆነው ጋር አመሳስለውታል። “ሩሲያዊ ሩሲያዊን ሊገድል ተነሳ” ብለዋል።

አሁን እየሆነ ያለውን ነገር ለማስታገስ ‘ልክ የሆነ እርምጃ እንወስዳለን’ ብለዋል ፑቲን በጠዋቱ ንግግራቸው።

ፑቲን አያይዘውም በዩክሬን እየተዋደቁ ያሉትን የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን አባላትን ‘ጀግኖች’ ሲሉ አሞግሰዋል።

ይህ በእንዲህ ሳለ በሩሲያ 2ተኛ ከተማ ሴንት ፒትስበርግ የቫግነር ዋና ቢሮ በሩሲያ የደኅንነትና ጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ሆኖ እየተበረበረ እንደሆነ ከዚያ የደረሱ መረጃዎች ያሳያሉ።

ፑቲን በዛሬው አጭር ንግግራቸው ሩሲያን ሊከፋፍሉ የሚሹ ሁሉ አይቀጡ ቅጣት ይቀጣሉ ብለዋል።

የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን አመጽ እንዴት ይቋጫል የሚለውን በተለይ ምዕራቡ ዓለም በታላቅ ተመስጦ እየተከታተለው ይገኛል።

ዩክሬን ለጊዜው በሩሲያ እየሆነ ስላለው ነገር ያለችው የለም።