የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን መሪ የሩሲያ መከላከያ ከፍተኛ አመራሮችን ለመደምሰስ ዛተ

የቅጥረኛው ቫግነር ቡድን መሥራችና መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን የሩሲያን መከላከያ ከፍተኛ አመራሮች “ልክ አስገባለሁ” ሲል ዛተ።

የቡድኑ መሪ ይህን ለማድረግ ‘የትኛውንም ርቀት እንሄዳለን’ ብሏል።

የክሬምሊን አስተዳደር በበኩሉ ግለሰቡን ‘የወታደር አመጽ በማነሳሳት’ ከሶታል።

የቭጌኒ ፕሪጎዢን ከሰዓታት በፊት ወታደሮቹ የዩክሬንን ድንበር አልፈው ወደ ሩሲያ መግባታቸውንና ሮስቶቮ ኦን ዶን ከተማ እንደሚገኙ ተናግሯል።

የቭጌኒ ፕሪጎዢን ማንኛውም አካል መንገዳችን ላይ ጋሬጣ ከሆነብን እንደመስሰዋለን ሲል ዝቷል።

የአካባቢው ባለሥልጣን ዜጎች ተረጋግተው ቤት እንዲቀመጡ መክረዋል። የቭጌኒ ፕሪጎዢን ወታደሮቹ አንድ የሩሲያን ሄሊኮፕተር መ’ተው መጣላቸውን ተናግሯል።

ነገር ግን ይህን ያደረጉት የት እንደሆነ አልባራራም። “ሄሊኮፕተሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ሲተኩስ” ተኩሰን ጥለነዋል ብሏል።

ቫግነር ቅጥረኛ የገዳዮች ቡድን የግል ኩባንያ ሲሆን በቅጥር ይዋጋል፤ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችም ሃብት ንብረት አፍርቷል።

በሩሲያ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በዩክሬን ላይ ዘመቻ የከፈተና በርካታ ድል ያስመዘገበ ቡድን ቢሆንም መሪው የቭጌኒ ፕሪጎዢን ከከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ጋር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቅራኔ ውስጥ መግባቱ ሲዘገብ ነበር።

ትናንት ዐርብ የ62 ዓመቱ የቫግነር ቅጥረኛ ተዋጊዎች ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን ወታደሮቹ በሚሳኤል መገደላቸውንና ይህን ያደረጉትም የሩሲያ ከፍተኛ የመከላከያ ጄኔራሎች ናቸው ሲል ያልተጠበቀና የዓለም ሚዲያን ያነጋገረ ክስ አቅርቧል።

የቭጌኒ ፕሪጎዢን ይህን ይበል እንጂ ወታደሮቹ በሩሲያ ከፍተኛ ጄኔራሎች ትእዛዝ በሚሳኤል ዒላማ ስለመደረጋቸውና በብዙ ቁጥር ስለመሞታቸው ያቀረበው መረጃ የለም።

የሩሲያ ባለሥልጣናት ክሱን አስተባብለው ይህን ሕገ ወጥ ያሉትን የአመጽ ተግባሩን እንዲገታ አሳስበውታል።

የቭጌኒ ፕሪጎዢን በበኩሉ ‘ሰይጣን’ ሲል የጠራቸው የሩሲያ መከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች በርሱ ወታደሮች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያቆሙ ለማስገደድ ኃይል እንደሚጠቀም ዝቷል። ‘እርምጃችን ፍትሕን ለማስፈን ነው” ብሏል።

“እነዚህ ወገኖቻችን የገደሉና ያስገደሉ፣ በዐሥር ሺዎች የሩሲያን ወታደሮችን በዩክሬን አስገብተው ያስጨረሱ ስግብግቦችን እንቀጣቸዋለን፤ ልክ እናስገባቸዋለን” ሲል በቴሌግራም በተላለፈ መልእክት ቁጣውን ገልጧል።

ለዚህም ዘመቻ ከፍተናል ያለው የቫግነር መሪ የሩሲያ ፖሊስ፥ መንግሥት፣ የሩሲያ ወታደር፣ የድንበር መኮንኖች ማናቸውም በጉዟቸው ላይ ደንቃራ ቢሆኑ ይቀጣሉ ሲል ዝቷል።

የኛን ዘመቻ ለማደናቀፍ የሞከረ ጠላት ነው፤ እናጠፋዋለንም ብሏል።

ጨምሮም “ይህ መፈንቅለ መንግሥት አይደለም።ይህ የፍትሕ እርምጃ ነው።የኛ እርምጃ በሩሲያ ወታደሮች ጣልቃ የሚገባ አይደለም ብሏል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ፑቲን ስለ ጉዳዩ መረጃዎች በየደቂቃው እየደረሷቸው ነው ብሏል።

በሞስኮ የጸጥታ ጥበቃው የተጠናከረ ሲሆን ዛሬ ማለዳ ከፍተኛ የወታደሮች እንቅስቃሴ ታይቷል።

አሁን የቫግነር ገዳይ ተዋጊ ቡድን አባላት በሮስቶቭ ከተማ የሚገኙ ሲሆን፣ የሊፔስክ ክልል አስተዳዳሪ ነዋሪዎች ወደ ደቡባዊ አቅጣጫ እንዳይጓዙ መክሯል።

ሊፔስክ ከሮስቶቭ 500 ኪሎ ሜትር ከሮስቶቭ ከተማ ትርቃለች። ከዩክሬን ድንበር ደግሞ 280 ኪሎ ሜትር ርቃ ትገኛለች።

በጉዳዩ ዙርያ የሩሲያ መከላከያ በትዊተር ሰሌዳው “ነገሩን እየተከታተልን ነው’ ከሚል ጽሑፍ በስተቀር የተባለ ነገር የለም።

በዩክሬን የሩሲያ እዝ ምክትል አዛዥ የሆኑት ጄኔራል ሰርጌይ ሱሩቪክን ከዚህ ቀደም የቭጌኒ ፕሪጎዢን የተሞገሱ ሰው ቢሆኑም አሁን ግን “ወደ ዩክሬን እየሰደድክ ያለኸውን ሠራዊት ወደ እዝ ማዕከሉ መልሰህ አስገባ” ሲል መክሯቸዋል።

“ደማችን አንድ ነው” ሲልም በቪዲዮ መልእክት ማስጠንቀቂያ ልኮላቸዋል። በዚህ መልእክቱ ምናልባት ደም መፋሰስ ሊያስከትል የሚችል ውጊያ ሊደረግ ይችል ይሆን የሚል ስጋትን አጭሯል።

አንድ ከፍተኛ የሩሲያ መኮንን የቫግነርን አመጽ “ፑቲንን ከጀርባ በጩቤ የመውጋት ያህል ነው’ ሲሉ ገልጸውታል።

የሩሲያ ብሔራዊ ሚዲያ የሩሲያ የደኅንነት አገልግሎት የቭጌኒ ፕሪጎዢን ላይ የወታደር አመጽ በማነሳሳት የክስ ፋይል እንዲከፈት ማዘዙ ተሰምቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ወታደሮቹ ሰውዬን እንዳይታዘዙትና ከቻሉም በቁጥጥር ሥር እንዲያውሉት መሥሪያ ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እየወጡ መሆኑ ምልክት የታየው ባለፈው ግንቦት የቭጌኒ ፕሪጎዢን በተገደሉ ወታደሮች አስክሬን ዙርያ ሆኖ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል ሰርጌይ ሾጉን “በቂ መሣሪያ እያቀረቡልን አይደለም፤ አስጨረሱን” እያለ ፍጹም ያልተጠበቀ የቪዲዮ መልእክት ከላከ በኋላ ነው።

ትናንት ዐርብ በለቀቀው የቪዲዮ መልእክት ደግሞ ይህ ጦርነት የተጀመረው ‘ለጄኔራል ሾጉ ክብር ነው። እሱን ማርሻል ለማስባልና በታሪክ ስሙን ለማጻፍ ነው’ ሲል የመከላከያ ሚኒስትሩን አብጠልጥሏል።

‘መከላከያ ሚኒስትሩ ሕዝቡን ዋሽተዋል፣ ፑቲንን አታለዋል፣ በዩክሬን በኩል ወረራ እንደተፈጸመብን፣ ኔቶ በኛ ላይ እንደዘመተ፣ ዩክሬን ልታጠቃን እንደሆነ አስመስለው ዉሸት ተናግረዋል” ብሏል።

ይህ ዘገባ በሚጠናቀርበት ወቅት በሩሲያ የመከላከያ ሠራዊት በተጠንቀቅ እንዳለ የተነገረ ሲሆን፣የቫግነር ቅጥረኛ የገዳኞች ቡድንም ሮስቶቭ ከተማ በመግባት የደቡባዊ ሩሲያ የወታደራዊ ዋና መሥሪያ ቤትን መክበቡ ተሰምቷል። የሞስኮ ባለሥልጣናት በበኩላቸው በቡድኑ መሪ ላይ የእስር ማዘዣ ቆርጠውበታል።

የቅጥረኛ ቡድኑ መጨረሻ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ብዙዎችን ሰቅዞ የያዘ ጥያቄም ሆኗል።

የቡድኑ መሪ በሮስቶቭ የደቡባዊ ሩሲያ ወታደራዊ ዋና መሥሪያ ቤትን የምንለቀው መከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሾይጉ እና የእግረኛ ሠራዊት አዛዡ ጄኔራል ቫልሪ ጌራሲሞቭ እዚህ ድረስ መጥተው ካነጋገሩን ብቻ ነው ብሏል ዛሬ ጠዋት።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በቅጥረኛ ቡድኑ ላይ ጥቃት ይከፍታል ወይስ መሪውን ለማግባባት ይሞክራል የሚለው በጉጉት እየተጠበቀ ነው።