ዶ/ር ዕሌኒ ገብረ መድኅን የ‘ግሎባል ኢኮኖሚ’ ሽልማት አሸናፊ ሆኑ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሥስራቿ ዶ/ር ዕሌኒ ገብረ መድኅን ጀርመን ኪል ከተማ የሚገኘው ኪል ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተቋም የሚያዘጋጀውን 18ኛውን ግሎባል ኢኮኖሚ ሽልማትን አሸናፊ ሆኑ።

ሰኞ ሰኔ 12/2014 ዓ.ም. ምሽት ላይ በኪል ከተማ በተከናወነ ሥነ ሥርዓት ላይ ሽልማታቸውን የተቀበሉት ዶ/ር ዕሌኒ፣ ሽልማቱ ኢትዮጵያ ወስጥ ላከናወኗቸው ተግባራት እውቅና የሚሰጥ በመሆኑ እንደተደሰቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ላለፉት 18 ዓመታት በኪል ሲካሄደ የቆየው የግሎባል ኢኮኖሚ ሽልማት የዘንድሮውን ዶ/ር ዕሌኒ በቢዝነስ ዘርፍ ሲያሸንፉ፣ የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ንጎዝ ኦኮንጆ በፖለቲካ ዘርፍ እንዲሁም የአፍሪካ ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሌዎናርድ ዋንታቼኮ በምጣኔ ሃብት ዘርፍ አሸንፈዋል።

ዶ/ር ዕሌኒ ገብረ መድኅን አሁን ላይ በተባባሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ውስጥ የተቋቋመውን የግል እና የመንግሥት ሴክተሮችን በማጣመር ወጣት ሥራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ የተቋቋመውን “ቲምቡክቱ” የተሰኘውን መርሃ ግብር ከኒው ዮርክ በኃላፊነት እየመሩ ይገኛሉ።

ኪል ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተቋም ዶ/ር ዕሌኒ ለሽልማቱ ብቁ እንዲሆኑ በዳኞች የተቀመጡ ምክንያቶችን ሲገልጽ በኢትዮጵያ ያላቸውን አስተዋጽኦ ዘርዝሯል።

ኢኮኖሚስቷ በአበርክቷቸው የበርካታ አርሶ አደሮችን እና ወጣቶችን ሕይወት ማሻሻላቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ በተለይ በአፍሪካ ጭምር ቀዳሚ ነው ባለው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አማካኝነት ለ15 ሚሊዮን አርሶ አደሮች መተዳደሪያን እንዳስገኙ አመልክቷል።

ከዚያም በኋላ “ብሉሙን” የተሰኘ ተቋም በማቋቋም ከግብርና ጋር ለተያያዙ የሥራ ፈጠራ እና የሃሳብ ማፍለቂያ የሚሆን ማዕከል ለወጣቶች እንደፈጠሩም ጠቅሷል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ በመንግሥታቱ ድርጅት አማካኝነት ለሥራ ፈጣሪ አፍሪካውያን በሚሆን ተግባር ላይ መሰማራታቸውን ገልጿል።

ተቋሙ በድረ ገጹ ላይ ባወጣው ጽሁፉ ዶ/ር ዕሌኒ ገብረ መድኅን “ቁርጠኛ፣ ደፋር፣ አርቆ አሳቢ እና ማኅበራዊ ኃላፊነት የሚሰማት” ሲልም አሞካሽቷቸዋል።

ዶ/ር ዕሌኒ ስለሽልማቱ ምን አሉ?

ሽልማቱን አስመልክቶ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ የነበራቸው ዶ/ር ዕሌኒ ገብረ መድኅን የተበረከተላቸው ሽልማት የፈጠረባቸውን ስሜት ሲናገሩ “በጣም ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ። በኢትዮጵያ የተሰራው ሥራ ለሌሎች አገራት ሊጠቅም እንደሚችል የሚያሳይ ነው” ብለዋል።

በተለይ በምርት ገበያ የተሰራው ሥራ ለአፍሪካ ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል የተበረከተላቸው እውቅና ማሳያ እንደሆነም ተናግረዋል።

“ኢኮኖሚስት ለመሆን ያቀድኩት በ15 ዓመት ዕድሜዬ ነው” የሚሉት ዶ/ር ዕሌኒ፣ ከልጅነት ህልማቸው መካከል አንዱ የሆነውን “በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ከርሃብ እና ድህነት ለመውጣት ሃሳብ ከሚያመነጩት አንዷ መሆን ነበር” ይላሉ።

ዶ/ር ዕሌኒ በስፋት የሚታወቁበት ምርት ገበያ በኢትዮጵያ ያለው ግብይትን ሥርዓት ለማስያዝ፣ ግልጽነት ለመፍጠር፣ በአምራቾች፣ ንግድ ላይ በተሰማሩ እና በላኪዎች መካከል በቴክኖሎጂ የተደገፈ ግብይት እንዲኖር ማገዙን ተናግረዋል።

“በነበረው የባንክ ሁኔታ፣ በነበረው የቴሌኮም ሁኔታ...ብዙ ሰው ‘እንዲህ አይነት ሥርዓት ሊዘረጋ አይችልም። የኢትዮጵያ ሁኔታ አይፈቅድም’ ብለው በጭራሽ ያላመኑ ብዙ ሰዎች ነበሩ” ካሉ በኋላ “ይህንን ማድረግ መቻላችን እና ለዓለም ማስመስከራችን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው እገምታለሁ” ሲሉ አክለዋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ለወጣቶች የሥራ ፈጠራ ሃሳብ ድጋፍ ለማድረግ እና ሃሳቡን ለማስተዋወቅ ቀዳሚ ሆነው መትጋታቸውን አንስተዋል።

በዚህም መነሻ ከ7 ዓመት በፊት የተመሠረተው ብሉሙን የተሰኘው የወጣቶች ሥራ ፈጠራ እና ሃሳብ ማፍለቂያ ተቋም መሠረት እንደጣለ እገምታለሁ ብለዋል።

አሁን የጀማሪ ሥራ ፈጠሪዎችን ለመደገፍ በመንግሥት ደረጃ ያለውን ፖሊሲ ለማዘጋጀት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ እንዲሁም ግለሰቦች በተመሳሳይ ሥራ ላይ መሰማራታቸው ጠቅሰዋል።

“ስለዚህ ብሉሙንም ልክ እንደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሠረት የጣለ ሥራ ነው ብዬ ነው የማምነው፤ ብዙዎችም ይህንን ይመሰክራሉ ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።

ይህም ሽልማት ለዚህ ተግባራቸው እውቅና ሰጥቷል።

“በጣም ነው ክብር የተሰማኝ። ኢትዮጵያም በጥሩ ሁኔታ እንደምትጠራ እና ለኢትዮጵያ ክብር የሚያስገኝ አድርጌ ነው የቆጠርኩት” ብለዋል።

ዶ/ር ዕሌኒ ገብረ መድኅን ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በተባባሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ስር የተቋቋመውን እና እሳቸው የሚመሩት ቲምቡክቱ የተሰኘውን መርሃ ግብር ሀሳብ በማበልጸግ ቆይተዋል።

ይህ መርሃ ግብር በመጪው መስከረም በመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሚመረቅ ሲሆን መቀመጫው ከኒው ዮርክ ወደ ሩዋንዳ ኪጋሊ ተዘዋውሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ውስጥ ሥራውን ያከናውናል።