ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ መዲና ናይሮቢ በተከሰተ ከባድ የጋዝ ፍንዳታ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆሰሉ
በኬንያ መዲና ናይሮቢ የጋዝ ሲሊንደር በጫነ መኪና ላይ በተከሰተ ፍንዳታ ቢያንስ ሦስት ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ ወደ 300 የሚጠቀጉ ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ።
ፍንዳታውን ተከትሎ በተነሳው እሳት ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል ከ20 የሚልቁ ሰዎች በአሳሳቢ ሁኔታ በመጎዳታቸው በከተማዋ ሆስፒታሎች ውስጥ ህክምና እያገኙ መሆኑ ተዘግቧል።
ከባድ ፍንዳታን ያደረሰው አደጋው ትላንት ሐሙስ ዕኩለ ሌሊት አካባቢ መሆኑን የኬንያ መንግሥት ቃል አቀባይ ገልጸው፣ በአካባቢው በነበሩ ተሽከርካሪዎች እና መኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።
አደጋውን ተከትሎ በማኅበራዊ ገጾች የተለቀቁ ቪዲዮዎች ፍንዳታው ባጋጠመበት አካባቢ ያሉ መኖሪያ ቤቶች፣ ሕንጻዎች እና ተሽከርካሪዎች በእሳት ተያይዘው አሳይተዋል።
ከአደጋው በኋላ 271 ሰዎች ባጋጠማቸው ጉዳት ከተማ ውስጥ ወደ ሚገኙ የተለያዩ ሆስፒታሎች መወሰዳቸው እና ተጨማሪ 27 ሰዎች ደግሞ እየተፈለጉ እንደሆነ የኬንያ ቀይ መስቀል ማኅበር ገልጿል።
የአደጋው መንስኤ እስካሁን እየተጣራ ነው።
የመንግሥት ቃል አቀባዩ አይዛክ ማውራ አደጋው ኬንቴኔሪ በተባለ ድርጅት ውስጥ መከሰቱን ተናግረዋል።
አይዛክ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጹሁፍ ደርጅቱ ጋዝ እየሞላ ሳለ አደጋው ማጋጠሙን አንስተው በርካታ ሰዎች ወደ ሆስፒታል መዋሰዳቸውን ጠቁመዋል።
“ድርጅቱ የነበረበት ህንጻ ክፉኛ ተጎድቷል። የእሳት አደጋው መንስኤ እስካሁን አልታወቀም። የነፍስ አደን ሥራው በመቀጠሉ ነዋሪዎች ወደ አካባቢው ከመጓዝ መቆጠብ አለባቸው” ሲሉ መክረዋል።
የተከሰተው እሳት ወደ ሌሎች የመኖሪያ ህንጻዎች ተዘምቶ ስለነበረ የሟች እና የተጎጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተሰግቷል።
ስፍራው ላይ የነበሩ የዐይን እማኞች ፍንዳታው ሲያገጥም መሬት ሲንቀጠቀጥ ተሰምቶናል ብለዋል።
ከተጎዱት መካከል ቦንፌስ ሲፉና የተባለ ነዋሪ “ከሲለንደሩ ፍንዳታ ለማምለጥ ስሞክር ቃጠሎ አጋጥሞኛል” ሲል ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጿል።
“ሲሊንደሩ የፈንዳው ከፊት ለፊቴ ነው። በነበልባሉ ተሸፍኜ ወድቄ ነበር። ዕድለኛ ነኝ ከአደጋው ለማምለጥ አቅም አግኝቻለሁ” ሲል አክሏል።
ሌላ ስሙ ያልተጠቀሰ የዐይን እማኝ ደግሞ ለኔሸን ጋዜጣ በሰጠው አስተያየት “ከፍተኛ ፍንዳታ ነበር። እሳቱም ከፍተኛ ነበር። ሰዎች እየጮኹ ወደ ሁሉም አቅጣጫ ይሮጡ ነበር” ብሏል።
ስፍራው ላይ ይኖር የነበረ የኔሽን ጋዜጠኛ በአካቢው ላይ የነበሩ ሁሉም ሰዎች ከፍንዳታው በኋላ ቤታቸውን ጥለው መሄዳቸውን ተናግሯል።
የኬንያ ቀይ መስቀል ማኅበር አደጋውን ለመቆጣጠር “ያለድካም እየታገለ እንደሆነ” በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አሳውቋል።