ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“ቭላድሚር ፑቲን ካልተመረጡ ማን ሊመረጥ ነው?”
የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መቀመጫ ከሆነው ክሬምሊን ፊት ለፊት የተንጣለለ አዳራሽ ይገኛል። ፕሬዝዳንቱ በዚህ አዳራሽ ተገኝተዋል።
አዳራሹን የሞላው ሕዝብ ከመቀመጫው ተነስቶ ፕሬዝዳንት ፑቲንን ሞቅ ባለ ጭብጨባ ወደ መድረክ መራቸው።
በአባት አገር ሩሲያ ይህ የሚያስደንቅ አይደለም። ጥሪ የተደረገላቸው የአገሪቱ ስመ ጥር ሰዎች ናቸው። ሁሉም ደግሞ የፑቲንን ለፕሬዝዳንትነት ዕጩ ሆነው መቅረብን በይፋ የሚደግፉ ናቸው።
ፑቲን ለአምስተኛ የሥልጣን ዘመን ይወዳደራሉ። ታዳሚዎች በዚህ ውሳኔያቸው ደስተኞች ናቸው።
የፊልም አዘጋጁ አንድሬ ኮንቻሎቭስኪ “[ፑቲን] የተለየ መሪ ነው። በጣም ደፋር እና ጥበበኛም ሰው ነው” ብሏል።
ዘፋኟ ናዴዝዳ ባብኪና በበኩሏ “የሩሲያ ሕዝብ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ፕሬዝዳንቱን ይደግፋል። ይህንን ለመከላከል የሚሞክር ሁሉ ይወድቃል” ብላለች።
ታዋቂ ሰዎችን ካሰባሰበው ዝግጅት ጀርባ ያለው ሐሳብ ዕጩ ሆነው የቀረቡት ፑቲን ከሁሉ በተለየ ሊግ ውስጥ መሆናቸውን ለማሳየት ይመስላል። የፑቲን ፕሪሚየር ሊግ እንበለው?
አንድ ነገር ግን መረሳት የለበትም። ይህንን ሊግ የፈጠሩትም ሆነ የሚቆጣጠሩት ራሳቸው ፑቲን ናቸው።
የሩሲያ የፖለቲካ ሥርዓት የፑቲን የፖለቲካ ሥርዓት ነው። የጨዋታ ሕጉ ደግሞ መመረጥ ነው። የፑቲን ዋነኛ ተቺዎች ከሊጉ ከወረዱ ቆይተዋል። በስደት ወይም በእስር ላይ ናቸው።
ይህ ሁሉ ተደማምሮ ምርጫውን በቀላሉ ተገማች አድርጎታል።
በፊት በፊት ሩሲያ እንደዚህ አልነበረችም።
ከሰላሳ ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የፓርላማ ምርጫ ተካሂዶ ነበር። በምርጫው ማን እንደሚያሸንፍ ማንም ፍንጭ አልነበረም።
ኮከብ ቆጣሪዎች ሁሉ የፖለቲካ ትንበያ ለመስጠት ይሞክሩ ነበር። ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ሩሲያውያን ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለ ነፃነት እና ስለ አገራቸው የወደፊት ዕጣ ፈንታ ተስፋ ነበራቸው።
የዛሬው የሩሲያ ምርጫ ኮከብ ቆጣሪዎችን ወይም ተንታኞችን አይፈልግም። የ2024 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዴት እንደሚጠናቀቅ በቀላሉ ማወቅ ይችላሉ። ቭላድሚር ፑቲን በሰፊ ልዩነት ያሸንፋሉ።
ምን ይሆን በዚህ ደረጃ በመተማመን ያሸንፋሉ ያስባለው?
ፑቲን ዋነኛ ተቀናቃኝ ይሆናሉ የተባሉት አሌክሲ ናቫልኒ ስማቸው ከዕጩዎች ተርታ የለም። ይህ የመጀመሪያው ምክንያት ነው። ፑቲን ከናቫልኒ? እንደዚህ ያሉ ፉክክሮች በፑቲን ፕሪሚየር ሊግ እንዲደረጉ አይፈቀድላቸውም።
የክሬምሊንን አስተዳደር የሚተቹት ቦሪስ ናዴዝዲን በምርጫው ውስጥ አለሁ እያሉ ነው። ናዴዝዲን ግን እንደ ናቫልኒ አይደሉም። ፑቲን ላይ ትችት የሚሰነዝሩት በጥንቃቄ ነው። ከፕሬዚዳንቱ አስተዳደር ጋርም ግንኙነት እንዳላቸውም ይታማሉ።
ተሳክቶላቸው ከተወዳደሩም በክሬምሊን ይሁንታ ነው የሚሆነው - ፑቲን ተፎካካሪ አላቸው የሚል ገጽታ ለመፍጠር።
ሩሲያ ውስጥ ክሬምሊን ነው መገናኛ ብዙሃንን የሚቆጣጠረው። ፑቲን በጣም የሚወደሱበት እና ብዙም የማይተቹበት እጅግ በርካታ የአየር ሰዓት ያገኛሉ። ይህ ደግሞ ለዳግም ምርጫ ወሳኝ ነው።
ፑቲን አሸናፊ የሚሆኑበት ሌላም ምክንያት አለ።
ፑቲን የፈረንጆቹ ዓመት ሲጠናቀቅ በሰጡት መግለጫ የሩሲያ ቲቪ ወጣት ጋዜጠኛ የሆነው አሌክሳንደር “በምርጫው መወዳደርዎን ሁላችንም እንደግፋለን። ምክንያቱም ሌላ ሰው ወንበሩን ተቆጣጥሮ አይቼ አላውቅምና” ብሏል።
እንደ አሌክሳንደር ያሉ ብዙ ሩሲያውያን በክሬምሊን የመሪነት መንበር ላይ ሌላ ሰው ተቀምጦ ማሰብን እንደማይችሉ ይናገራሉ። ፑቲንን እንደብቸኛ አማራጭ ስለሚመለከቱ አይደለም። ምንም አማራጭ ስለማይታያቸው ነው።
ብዙ ጊዜ “እሺ ፑቲንስ አይሁን፣ ታዲያ ማን ይሆናል?” ሲሉ ይደመጣሉ።
ክሬምሊን ይህ አስተሳሰብ እንዲሰርጽ አድርጓል። ሩብ ምዕተ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ሩሲያን በፕሬዚዳንትነት እና በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩትን ሰው ሊቃወሙ የሚችሉትን ከፖለቲካ ምኅዳሩ አጽድተዋል። ይህን በማድረግ “ታዲያ ማን ይሁን?” የሚል ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል። መልስም አልሰጠበትም።
ከሞስኮ 225 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ርዜቭ ከተማ የሚኖሩ አብዛኞቹ ለውጥ ይፈልጋሉ። መሪው እንዲቀየሩ ግን አይፈልጉም። መሪ ሳይቀየር ለውጥ ፍለጋ መሆኑ ነው።
ኢሊያ የሚባል ወጣት “ሁሉም ባለበት በመሆኑ ነገሮች ወደ በተሻለ ሁኔታ እንደሚቀየሩ ተስፋ አደርጋለሁ። አዲስ ሰው ከተመረጠ የመንግሥትን ሸክም ላይወጣው ይችላል። ልምድ ያለው እንደ ፑቲን ያለ ሰው አሁን ባለንበት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንኳን አገሪቷን ማሳደግ ይችላል።”
ከጡረታ በሚያገኙት ገንዘብ የሚተዳደሩት ሊዲያ ደግሞ “በምርጫው ትልቅ ተስፋ አለኝ። ጦርነቱ ያበቃል፤ ኢኮኖሚውም ይሻሻላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ፑቲንን ግን አከብራለሁ” ይላሉ።
“እሱን መተካት የሚችል ሌላ ማንም የለም?” የሚል ጥያቄ ይነሳል።
“ለጊዜው የለም። ምናልባት ፑቲን የሚተካውን ሰው ያገኝ ይሆናል። ለረዠውም ጊዜ በሥልጣን ላይ የሚቆይ ግን ይመስለኛል” ሲሉ ሊዲያ ይመልሳሉ።
የዩክሬን ጦርነት እና ጉልህ የሆነው የሩሲያ ጦር ኪሳራ እንኳን በሩሲያው ፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ላይ ብዙዎችን ተስፋ ያስቆረጠ አይመስልም።
ወረራው እንዲጀመር የወሰኑት ፑቲን ናቸው። ዓላማው እና ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በጦርነት ወቅት መሪያቸውን መደገፍ እንዳለባቸው አንዳንድ ሩሲያውን ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ ጦርነቱን የጀመረችው ሩሲያ ሳትሆን ምዕራባውያን ናቸው የሚለውን የአገሪቱን ትርክት ይቀበላሉ።
በክሬምሊን ለውጥ ማየት የምትፈልግ አንዲት ሴት የርዤቭ ነዋሪ ናት። የቀድሞዋ የቲቪ ጋዜጠኛ እና የግዛት ሕግ አውጪ የሆነችው የካትሪና ዱንትሶቫ በፕሬዚዳንትነት ለመወዳደርም ሞክራለች። በዩክሬን ሠላም እንዲሰፍን፣ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እና “ሰብአዊ” የሆነች ሩሲያ እንድትፈጠር ጥሪ አቅርባለች።
የሩሲያ ምርጫ ኮሚሽን በማስረጃዎቿ ላይ ስህተቶች መገኘታቸውን በማንሳት ዕጩነቷን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም።
“እዚህ ያለው የፖለቲካ ሥርዓት እኔን ባዕድ አድርጎ ይመለከተኛል። ምን ማድረግ እንዳለበትም አያውቅም። ምክንያቱም በድንገት ስለመጣሁ ማን እንደሆንኩ አያውቅም። ስለዚህ እኔን ለማራቅ ተወስኗል” ስትል ዱንትሶቫ ትናግራለች።
አሁን አዲስ ፓርቲ እያቋቋመች ነው። ሥርዓቱ እንዳይጎዳት ስጋት አያድርባትም?
“እኛ ሕገወጥ ነገር እየሠራን አይደለም፤ በሕጉ መሠረት እንሠራለን። ፍርሃት ማሸነፍ የለበትም። እየሠራሁት ባለው ነገር አምናለሁ። ይህ ውሳኔዬ ፍርሃትን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ያደርገዋል” ብላለች።
ወደ ፑቲን የምርጫ ዘመቻ ዝግጅት እንመለስ። የአርቲ ቴሌቪዥን ዋና አዘጋጅ የሆነችውን ማርጋሪታ ሲሞንያን ስለፑቲን ትከራከራለች።
“ለሩብ ምዕተ-ዓመት እና ከዚያም በላይ በሥልጣን ላይ ያለ መሪ ... ለዚያውም ግልጽነት እና ቁጥጥር የሌለበት፤ ይህ አደገኛ አይሆንም?” ስንል ጠየቅናት።
“ይህ ለዓመታት ደጋግማችሁ ስትሰራጩት የነበረ ሃሳብ ነው። አንድ ሰው ለረዥም ጊዜ በሥልጣን ላይ ከቆየ በየአራት ዓመቱ መሪ ከተቀየሩት አንጻር የከፋ ይሆናል ማለት አይደለም። የካምቦዲያው ፖል ፖት በሦስት ዓመታት ውስጥ ነው አንድ ሦስተኛውን የአገሩን ሕዝብ ያጠፋው” ስትል መልሳለች።