ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ እና የክሬን፡ የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ታማኝ ሰዎች እነማን ናቸው?
የሩሲያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ እንደመሆናቸው በዩክሬን ላይ ለተፈጸመው ወረራ ዋነኛው ውሳኔ የሚተላለፈው በፕሬዝዳንት ፑቲን ነው።
ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ ለሚሰጡት ውሳኔያቸው ከአስርት ዓመታት በፊት አንስቶ አብረዋቸው የሰሩ የቅርብ ታማኝ ሰዎቻቸው በሚሰጧቸው ምክር ላይም ይተማመናሉ። እየተካሄደ ካለው ጦርነት አንጻር የፑቲን የቅርብ ታማኝ ሰዎች እነማን ናቸው?
ሰርጌይ ሹይጉ
የፑቲን የረጅም ጊዜ ታማኝ የቅርብ ሰው የሆኑት የመከላከያ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ሹይጉ ዩክሬንን በተመለከተ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ተመሳሳይ አቋምን ያንጸባርቃሉ። በዚህም ዩክሬንን ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ በማድረግ ሩሲያን ከምዕራባውያን ወታደራዊ ስጋት መጠበቅ የሚል አቋም አላቸው።
ከቅርበታቸው የተነሳ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል የፑቲን ተተኪ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰብ ነበር። ነገር ግን አሁንም ድረስ በሩሲያ መንግሥት ውስጥ ከፍ ያለ ተደማጭነት ያላቸው የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ሰው ናቸው።
ሰርጌይ ሹይጉ ከስምንት ዓመት በፊት ሩሲያ ከዩክሬን የተጠቀቻትን ክሪሚያን ስትይዝ ወታደራዊ ዘመቻውን በመምራት ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም የፑቲን ተቃዋሚዎችን ከሩሲያ ውጪ እያደነ በመርዝ ያጠፋል የሚባለውን የወታደራዊ መረጃ ቡድንን የሚመሩት እኚሁ ግለሰብ ናቸው።
የሩሲያ የደኅንት ተንታኝና ፀሐፊ የሆኑት አንድሬ ሶልዳቶቭ እንደሚሉት ሰርጌይ ሹይጉ፣ የጦር ሚኒስትር ብቻ ሳይሆኑ በአብዛኛው በታሪክ ላይ የተመሰረተው የሩሲያ መንግሥት ርዕዮተ ዓለምንም በከፊል የሚቃኙት ናቸው።
ቫሌሪ ጌራሲሞቭ
የአገሪቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የሆኑት ቫሌሪ ጌራሲሞቭ የዩክሬን ወረራ እና ወታደራዊ እርምጃውን በፍጥነት ማጣናቀቅ ኃላፊነታቸው የነበረ ቢሆንም፣ የተፈለገውን ያህል የተሳካላቸው አይመስሉም።
ፑቲን ከ20 ዓመት በፊት በቼቺኒያ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ቫሌሪ ጌራሲሞቭ ሠራዊቱን ሲመሩ የቆዩ ሲሆን፣ በክሪሚያ ወረራ፣ ከዩክሬን ወረራ በፊት ቤላሩስ ውስጥ የተደረገውን ወታደራዊ ልምምድን እንዲሁም ወረራውን በመማራት ከፊት ተሰልፈዋል።
በተደነቃቀፈው የዩክሬን ወረራ ጅማሬ እና በሩሲያ ወታደሮች ዘንድ አለ በሚባል ዝቅተኛ ሞራል ምክንያት ወደ ጎን ተገፍተዋል የሚሉ አንዳንድ ሪፖርቶች እየወጡ ናቸው።
ነገር ግን አንድሬ ሶልዳቶ እንደሚያምኑት ይህ ከእውነት የራቀ ምኞት ነው። ምክንያቱም ፑቲን በጦር ሜዳ የሚካሄዱ ነገሮችን በራሳቸው ሊከውኑና ሊቆጣጠሩ አይችሉም። ስለዚህም የቫሌሪ ጌራሲሞቭ ሚና እንዲሁ በቀላሉ የሚተካ እንዳልሆነ ያመለክታሉ።
ኒኮላይ ፓትሩሼቭ
ፓትሩሼቭ ምዕራባውያን ለሩሲያ መልካም አመለካከት የላቸውም ብለው በጽኑ የሚያምኑ ሲሆን ከአስርታት በፊት አንስቶ ከፑቲን ጋር የጠበቀ ቅርበት አላቸው።
ከፓትሩሼቭ በተጨማሪ የአገር ውስጥና የውጭ ደኅንት ኃላፊዎቹ ቦርትኒኮቭ እና ናሪይሽኪን ሌሊን ግራድ ውስጥ ከ1970ዎቹ ጀምሮ ከፑቲን ጋር አብረው የሰሩ ሲሆን፤ አሁን ድረስ የፕሬዝዳንቱ ቁልፍ ሰው ሆነው እንዳሉ ናቸው።
ነገር ግን የፓትሩሼቭን ያህል በፑቲን ዘንድ ተደማጭነት ያላቸው ሰዎች በታም ጥቂት እንደሆኑ ይነገራል። ሁለቱ በሶቪየት ዘመን ኬጂቢ ውስጥ የሰሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ ሁለቱም የሩሲያን የስለላ ድርጅት አንዳቸው ከአንዳቸው በመረከብ መርተዋል።
ከዩክሬን ወረራ ሦስት ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የደኅንት ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አሜሪካ ዋነኛ ግብ አድርጋ የያዘችው ሩሲያን እንድተርበታተን መድረግ ነው ሲሉ ጠንካራ ክስ አቅርበዋል።
አሌክሳንደር ቦርትኒኮቭ
የክሬምሊንን እርምጃ በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች እንደሚሉት ቦርትኒኮቭ ከሚመሯቸው የደኅንነት ተቋማት የሚቀርቡ መረጃዎችን ቭላድሚር ፑቲን ከየትኛውም ምንጭ በላይ ያምናሉ። በዚህም ቦርትኒኮቭ የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ታማኝ ከሆኑት መካከል ይጠቀሳል።
የሩሲያ የፌደራል ደኅንት መሥሪያ ቤትን (ኤፍኤስቢ) የመሪነት ቦታ የያዙት ቦርትኒኮቭ፣ ቦታውን ከሌላኛው የፑቲን የቅርብ ሰው ኒኮላይ ፓትሩሼቭ ነበር የተረከቡት።
ይህ የሩሲያ የደኅንት መሥሪያ ቤት በአገሪቱ ውስጥ ባሉ ሌሎች የደኅንት ተቋማት ላይ ከፍ ያለ ተጽዕኖ ማሳረፍ የሚችል ሲሆን የራሱ ልዩ ኃይልም አለው።
አንድሬ ሶልዳቶቭ እንደሚያምኑት ቦርትኒኮቭ በሩሲያ የሥልጣን ማዕከል ውስጥ እጅጉን አስፋለጊ ሰው ቢሆኑም፣ ሌሎች እንደሚያደርጉት የመሪውን ሐሳብ የሚገዳደሩና ምክር የሚሰጡ ሰው አይደሉም ይላሉ።
ሰርጌይ ናሪይሽኪን
ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ለረጅም ጊዜ አብረው በቅርበት በመስራት ከሚጠቀሱት ባለሥልጣንት መካከል ሰርጌይ ናሪይሽኪን አንዱ ናቸው።
ነገር ግን ከዩክሬን ወረራ በፊት በተካሄደውና በቴሌቪዥን በቀረበው የአገሪቱ የደኅንት ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት ፑቲን ለናሪይሽኪን ያሳዩት ምላሽ፣ በብዙዎች ዘንድ በሁለቱ መካከል የነበረው ቅርበት መላላቱን የሚያመላክት ነው ይላሉ።
ስለ ክስተቱ አስደንጋጭነት ቤን ኖብል ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፣ የፑቲን በሚገርም ሁኔታ መረጋጋት በበርካቶች ዘንድ ጥያቄን አጭሯል። አጠቃላይ የስብሰባው ድባብም ግራ አጋቢና መልካማ ያልሆነ ምስል የተንጸባረቀበት ነበር።
ሰርጌይ ናሪይሽኪን በ1990ዎቹ ሴንት ፒተርስበርግ ውስጥ፣ በ2004 ፕሬዝዳንትንት ከሆኑ በኋላ፣ ቀጥሎም የአገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሆነው ከፑቲን ጋር አብረው ሰርተዋል።
በተጨማሪም የሩሲያ ታሪክ ማኅበር መሪ ሆነው ሰርተዋል። ሶልዳቶቭ እንደሚሉት ይህ የናሪይሽኪን የታሪክ ዕውቀት ፕሬዝዳንቱ ለሚወስዷቸው እርምጃዎች ርዕዮተ ዓለማዊ መሰረቶችን በመስጠት ያላቸውን ተፈላጊነት አጉልቶታል።
ሰርጌይ ላቭሮቭ
ምንም እንኳን በሩሲያ ውስጥ በሚሰጡ ቁልፍ ውሳኔዎች ላይ ጉልህ ሚና የላቸውም ተብሎ ቢታሰብም ሰርጌይ ላቭሮቭ ለ18 ዓመታት ቁንጮ ዲፕሎማት በመሆን የአገራቸውን ጉዳይ ለዓለም ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
የ71 ዓመቱ ላቭሮቭ የረጅም ዘመን አገልግሎት ፕሬዝዳንት ፑቲን አመራራቸው በዋናነት ለዘመናት የካበተ ልምድ ባላቸው ሩሲያውያን ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑን ያሳያል።
ነገር ግን ለረጅም ጊዜ ዩክሬንን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ተገልለው እንደቆዩ የሚነገርላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ምንም እንኳን ግልፍተኛና ኃይለኛ ናቸው ቢባሉም ዩክሬንን በተመለከተ የፑቲን ጆሮ ባያገኙም ዲፕሎማሲያዊ ንግግርን በመፍትሔነት ሲያቀርቡ ቆይተዋል።
ቫለንቲና ማትቪዬንኮ
በፑቲን የቅርብ ክበብ ውስጥ ብቸኛዋ ሴት የሆኑት ቫለንቲና ማትቪዬንኮ፣ የአገሪቱ የላይኛው ምክር ቤት የሩሲያ ኃይሎች ወደ ሌላ አገር ገብተው እንዲሰማሩ ያደረገውን ውሳኔ ሲያጸድቅ የበላይ ሆነው የመሩ ናቸው። ይህም ለዩክሬኑ ወረራ መንገድ ጠርጓል።
ቫለንቲና ማትቪዬንኮ ፑቲን ሴንት ፒተርስበርግ ውስጥ ሥልጣን ላይ እያሉ ጀምሮ አብረዋቸው ከመጡ ታማኝ ሰዎች መካከል አንዷ ሲሆኑ፣ ሩሲያ ክሪሚያን ወራ ስትይዝ በውሳኔው ውስጥ ተሳትፎ ነበራቸው። ቢሆንም ግን በቀዳሚ የውሳኔ ሰጪዎች ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱ ግለሰብ አይደሉም።
እንደሁሉም የሩሲያ የደኅንነት ምክር ቤት አባል የቫለንቲና ማትቪዬንኮ ሚና ፕሬዝዳንት ፑቲን አብላልተውና ከውሳኔ ላይ ደርሰው የሚያመጧቸው ሐሳቦች የጋራ ውይይት ተደርጎባቸው የተሰጡ የሚመስል ገጽታ እንዲይዙ ማድረግ ነው።
ቪክቶር ዞሎቶቭ
የቀድሞው የፕሬዝዳንቱ የግል ጠባቂ ቪክቶር ዞሎቶቭ፣ ከስድስት ዓመት በፊት እንደ ኦእሬዝዳንቱ የግል ሠራዊት በራሳቸው በፑቲን የተቋቋመውን 'ሮስግቫርዲያ' የተባለውን የሩሲያን ብሔራዊ ዘብ ይመራሉ።
ፑቲን የግል ጠባቂያቸው ብሔራዊ ዘቡን እንዲመሩ ማድረጋቸው የበለጠ ታማኝነትን ለማረጋገጥ የታለመ ነው። ቪክቶር ዞሎቶቭም ይሚመሩትን ዘብ ቁጥር አሁን 400,000 እንዳደረሱት ይነገራል።
የዩክሬን ወረራ ሲታቀድ የአገሪቱ ሠራዊት በቀናት ውስጥ እንዲያጠናቅቀው ታቅዶ ነበር፤ ነገር ግን የታሰበው ሳይሆን ሲቀር የሩሲያ ብሔራዊ ዘብ የመሪነቱን ሚና ተረክቦ ጦርነቱን እያካሄደ ነው።
የብሔራዊ ዘቡ ችግር የሚባለው መሪው ቪክቶር ዞሎቶቭ ወታደራዊ ስልጣናና ልምድ የሌላቸው መሆኑና ሠራዊታቸውም ታንክ የታጠቀ አለመሆኑ ለጥቃት ተጋላጭ እንዳደረገው ይነገራል።