ትራምፕ 'የሚቃወሟቸው' የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃድ ሊሰረዝ እንደሚችል ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፈቃዳቸው "ሊነጠቅ" እንደሚችል ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃንን የሚቆጣጠረው አካል የኤቢሲ ፕሮግራም አቅራቢ የነበረው ጂሚ ኪሚል ላይ የወሰደውን እርምጃ ደግፈው አስተያየት በሰጡት ወቅት ነው።

በዲዝኒ ባለቤትነት የተያዘው ጣቢያ ረቡዕ ዕለት ጂሚ ኪሚል በወግ አጥባቂው ቻርሊ ከርክ ግድያ ላይ የሰጠውን አስተያየት ተከትሎ በተፈጠረ ውዝግብ የኮሜዲያኑን ቶክ ሾው "ላልተወሰነ" ጊዜ ከሥርጭት ማገዱን አሳውቋል።

ሰኞ ዕለት ኪሚል ተጠርጣሪው የትራምፕ አቋምን የሚያራምድ (ማጋ) ሪፐብሊካን አካል ነው በማለት የተናገረ ሲሆን፣ የዩታ ባለሥልጣናት ግን ግለሰቡ "በግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም የተጠመቀ" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ኤቢሲ የፌደራል ኮሙኑኬሽንስ ኮሚሽን ኮሜዲያኑ የሰጠውን አስተየየት ተከትሎ እርምጃ አንደሚወስድ ካስጠነቀቀ በኋላ 'ጂሚ ኪሚል ላይቭ' የተባለ ፕሮግራሙን አስቁሟል።

ትራምፕ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ይፋዊ ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ወደ አሜሪካ ለመመለስ ኤር ፎርስ ዋን ውስጥ ሳሉ በሰጡት አስተያየት "የሆነ ቦታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች 97 በመቶ ከእኔ በተቃራኒ የቆሙ መሆናቸውን አንብቤያለሁ፤ እንደገና 97 በመቶ አሉታዊ ሆነው እኔ ዳግም መመረጥ ችያለሁ። ሁሉንም ሰባት ልዩነት የሚፈጥሩ ግዛቶች [ባለፈው ዓመት በተደረገ ምርጫ] ማሸነፍ ችያለሁ" ብለዋል።

ጂሚ ኪሚል ሰኞ ዕለት የፕሮግራሙ መግቢያ ላይ በነበረው መነባነብ ላይ "የማጋ ቡድን" የነበረው "ቻርሊ ከርክን የገደለው ወጣት ከእነርሱ የተለየ አድርገው ለማቅረብ እየሞከሩ ነው" እንዲሁም እየሞከሩ ያሉት "ከዚያ የሚገኝ የፖለቲካ ነጥብን ማስቆጠር ነው" ብሎ ነበር።

ቻርሊ ከርክ በተተኮሰበት ጥይት ከተገደለ በኋላ ጂሚ ኪሚል በኢንስታግራም ገፁ ላይ ገድያውን አውግዞ ለቤተሰቦቹ "መጽናናትን" ተመኝቷል።

ሐሙስ ዕለት ለፎክስ ኒውስ ቃለመጠይቅ የሰጡት የብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ኃላፊ ብሬንዳን ካር የኪምል መታገድ "የመጨረሻው እርምጃ አይደለም" ብለዋል።

"እነዚህም መገናኛ ብዙኃን ለሕዝብ ፍላጎት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረጋችንን እንቀጥላለን" ካሉ በኋላ "ብሮድካስተሮቹ ይህንን ቀላል መፍትሄ የማይቀበሉ ከሆነ ፈቃዳቸውን ለተቆጣጣሪ ተቋሙ መመለስ ይችላሉ" ሲሉ አክለዋል።

ባለሥልጣኑ እንደ ኤቢሲ ባሉ ግዙፍ ኔትወርኮች እና አጋሮቻቸውን የመቆጣጣር ሥልጣን አለው።

ኤጀንሲው እንደ ፎክስ ወይም ኤምኤስኤንቢሲ (MSNBC) ያሉ የኬብል ቻናሎች ላይ ያለው ሥልጣን የተገደበ ሲሆን፣ በፖድካስቶች ወይም ይዘቶቻቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚያሠራጩ ላይ ምንም ዓይነት ሥልጣን አልተሰጠውም።

የሕግ ባለሙያዎች የአሜሪካ ሕገመንግሥትን በመጥቀስ ኤጀንሲው በፖለቲካ አለመግባባት የተነሳ ፈቃድን በሕግ የመሰረዝ መብት የለውም ሲሉ ይከራከራሉ።

የጂሚ ኪምል ቶክሾው መታገዱ የተገለፀው ረቡዕ ዕለት ሲሆን፣ የቴሌቪዥን ጣቢያው ባለቤቶች ከሆኑት መካከል ግዙፉ ኔክስታር ኮሜዲያኑ "ላልተወሰነ ጊዜ" ወደ አየር አይመለስም ሲል መታገዱን ይፋ አድርጓል።

ኔክስታር ኪምል ቻርሊ ከርክን በሚመለከት የሰጠው አስተያየት "በአገር አቀፍ ደረጃ ፖለቲካዊ ውይይት በጦዘበት በዚህ ጊዜ የተሰጠ ተገቢ ያልሆነ እና ኃላፊነት የጎደለው አስተያየት" ብሎታል።