ቻርሊ ከርክ ማን ነው? አሜሪካውያንን ያስደነገጠው የትራምፕ የቅርብ ሰው ግድያ

የዶናልድ ትራምፕ ሁነኛ ሰው፣ ወግ አጥባቂ ተሟጋች እንዲሁም የሚዲያ ሰው የሆነው አሜሪካዊው ቻርሊ ከርክ ረቡዕ ዕለት በተተኮሰበት ጥይት ተገድሏል።

የ31 ዓመቱ ወጣት በአሜሪካ ኮሌጅ ውስጥ ባዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ ዒላማ ተደርጎ በተተኮሰበት ጥይት መገደሉን ፖሊስ ገልጿል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም በወጣቱ አክቲቪስት የተሰማቸውን ድንጋጤ ገልፀዋል።

በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ "ታላቁ እናም ተዓምረኛው፣ ቻርሊ ከርክ ሞቷል። በአሜሪካ ከቻርሊ በስተቀር የወጣቶችን ልብ በተሻለ የሚረዳ የለም" ብለዋል።

የሊብራል መንፈስ ባረበበባቸው የአሜሪካ ኮሌጆች የኮንሰርቫቲቭ ሃሳቦችን ለማስፋፋት በማሰብ ተርኒንግ ፖይንት (Turning Point) የተሰኘውን ተቋም የጀመረው በ18 ዓመቱ ነው።

ረቡዕ ዕለት በዩታ ቫሊ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅቶት በነበረው መርሃ ግብር ላይ በጥይት ተመትቶ ሲገደል በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተመሳሳይ ዝግጀቶችን አዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን፣ ተማሪዎች በመረሃ ግብሩ ላይ በመገኘት በተመሳሳይ ሀሳቦች ከእርሱ ጋር አንዲወያዩ እና እንዲከራከሩ የተመቻቸ ነበር።

የእሱ ማኅበራዊ ሚዲያ እና ታዋቂው ዕለታዊ ፖድካስት እንደ የልውጥ ፆታ ማንነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ እምነት እና የቤተሰብ ዕሴቶች ባሉ ጉዳዮች ላይ ከተማሪዎች ጋር ሲከራከሩ የሚያሳይ ቪዲዮዎች ተቆርጠው ይጋሩበታል።

የትራምፕ ቪዲዮም በከርክ ፖድካስት መጀመሪያ ላይ ይታያል።

"ቻርሊን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ እሱ ምርጥ ሰው ነው፣ መንፈሱ፣ ለአገሩ ያለው ፍቅር፣ እስካሁን ከተመሠረቱት የወጣቶች ድርጅቶች ሁሉ እጅግ በጣም ከፍተኛ አቅም ያለው የእርሱ ተቋም አስደናቂ ሥራ ሠርቷል።"

ከርክ መንግሥታዊ ያልሆነውን ድርጅት የመሠረተው ባራክ ኦባማ በአውሮፓውያኑ 2012 ዳግም ከተመረጡ በኋላ ነው።

የተቋሙ ተልዕኮ ወጣቶች ላይ ሲሆን፣ ተማሪዎችን በማደራጀት "ኃላፊነት የተሞላበት ወጪን፣ የነጻ ገበያ እና አነስተኛ መንግሥትን" ያስተዋውቃል።

አሁን በ850 ኮሌጆች ውስጥ ይንቀሳቀሳል።

ባለፈው ዓመት ዶናልድ ትራምፕ እና ሌሎች ሪፐብሊካኖች ሲመረጡ ወጣቶች ወጥተው ድምጻቸውን እንዲሰጡ በመቀስቀስ ከፍተኛ እገዛ አድርጓል።

ወጣቱ ቻርሊ ከርክ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ አዲስ መራጭ ወጣቶች ወጥተው እንዲመዘገቡ በማድረግ እና በአሪዞና ግዛት ትራምፕ አሸናፊነትን እንዲያገኙ ከፍተኛ ወሳኝ ሥራዎችን በመሥራቱ ስሙ በበጎ ይናሳል።

የከርክ እና የዶናልድ ትራምፕ ወዳጅነት እየጠነከረ የመጣው አሸንፈው ዋይት ሐውስ ከገቡ በኋላ ነው። ከርክ የትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ የተገኘ ሲሆን፣ የዋይት ሐውስም ቤተኛ ሆኗል።

በጥር ወር ላይ ከዶናልድ ትራምፕ ልጅ ትራምፕ ጁኒየር ጋር በመሆን ትራምፕ በአርክቲክ አካባቢ የምትገኘው እና የአሜሪካ ግዛት መሆን አለባት ሲሉ ወደ ተናገሯት ግሪንላንድ ተጉዟል።

ከቱጃር ቤተሰቦች የተገኘው ከርክ የተማረው በቺካጎ አቅራቢያ በሚገኝ የማኅበረሰብ ኮሌጅ ውስጥ ነው።

ቢሆንም ትምህርቱን የፖለቲካ አክቲቪዝም ላይ ለማሳለፍ በመፈለጉ አቋርጦ ወጥቷል።

በጣም ታዋቂ ለሆነው ዌስት ፖይንት ለተባለው የአሜሪካ ወታደራዊ አካዳሚ አመልክቶ የነበረው ከርክ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።

ከተማሪዎች ጋር እንደ ድኅረ ዘመናዊነት (ፖስት ሞደርኒዝም) ያሉ ሃሳቦችን አንስቶ በሚከራከርበትም ወቅት ኮሌጅ ገብቶ አለመመረቁን በማንሳት ይቀልዳል።

በመላው አሜሪካ በመዟዟር ሪፐብሊካኖች በሚያዘጋጇቸው መድረኮች ላይ ንግግር የሚያደርገው ከርክ ከበርካታ ታዋቂ ሪፐብሊካን ጋር በሚያዘጋጇቸው ግብዣዎች ላይ ይጋበዛል።

ወግ አጥባቂ የሆነው የሬዲዮ ፕሮግራሙም በማኅበራዊ መድረክ ላይ ሚሊዮኖች ይከተሉታል።

ከርክ በ2020 እና በዚህ ባለንበት 2025 የኦክስፎርድ ኅብረት ላይ ተገኝቶ ንግግር ያደረገ ሲሆን፣ ዘ ማጋ ዶክትሪን (The Maga Doctrine) የተሰኘ በሚሊዮን ቅጂዎች የተሸጠ መጽሐፍ ደራሲም ነው።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው ከርክ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ከፊት በመሆን ይታወቃል።

በፖድካስቶቹ ላይ ከሚያነሳቸው ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ባሻገር ስለ ጦር መሣሪያ ቁጥጥር ይወያያል።

ከጥቂት ወራት በፊት ከርክ "እንዳለመታደል ሆኖ ሕገ መንግሥቱ የሰጠንን መብት ለመጠበቅ በየዓመቱ የተወሰኑ ሰዎችን በጦር መሳሪያ ግድያ መገበራችን ነው" ብሎ ነበር።

ከርክ ፆታ ልውጥ ለሆኑ ሰዎች ባለው የመረረ ተቃውሞ በኮቪድ ወረርሽኝ በመከሰቱ ላይ በነበረው ጥርጣሬ፣ እንዲሁም በ2020 ትራምፕ በምርጫ ተጭበርብረዋል በሚሉት አቋሞቹ ይታወቃል።

በተተኮሰበት ጥይት ከተገደለ በኋላ ግን ከርክ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በነጻነት መወያየትን ያስቀድም ነበር የሚሉ ድምጾች ተሰምተዋል።

ዊሊያም ዎልፍ የባብቲስት ሊደርሺፕ ማዕከል ዳይሬክተር "አጠቃላይ ሥራው የተመሠረተው በተከፋፈሉ ቡድኖች መካከል ያሉ ጉዳዮችን ለመፍታት ንግግርን በመስበክ ነው። ጠብን አይደግፍም ነበር" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።