በቻርሊ ከርክ ግድያ የተጠረጠረው ግለሰብ ወንጀሉን መፈጸሙን ለጓደኛው መናገሩን ዐቃቤ ሕግ ገለፀ

አሜሪካዊውን ቀኝ ዘመም አክቲቪስት ቻርሊ ከርክን በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ በቁጥጥር የዋለው ግለሰብ አብሮት ለሚኖረው ጓደኛው በላከው መልዕክት ላይ መግደሉን ማመኑን ዐቃቤ ሕግ ገለፀ።

ዐቃቤ ሕግ አክሎም በተጠርያሪው ላይ ሰባት ክሶች እንደተመሰረተበት አስታውቋል።

የ22 ዓመቱ ወጣት ታይለር ሮቢንሰን አብሮት ለሚኖረው እና ለፍቅር ጓደኛው ከኮምፒውተር ኪቦርድ ስር ማስታወሻ ማስቀመጡን የዩታ ካውንቲ ዐቃቤ ሕግ ኬፍሪ ግሬይ ተናግረዋል።

አክለውም አንድ ክፍል ውስጥ አብሮት የሚኖረው ግለሰብ የፍቅር ጓደኛው ነው ብለዋል።

እንደ ግሬይ ከሆነ ማስታወሻው "ቻርሊ ከርክን የመግደል አጋጣሚውን አግኝቻለሁ እናም ላደርገው ነው" ይላል።

በሁለቱ ጓደኛሞች መካከል የነበረውን የጽሑፍ መልዕክት ልውውጥ ያጋሩት ዐቃቤ ሕጉ ተከሳሽ በአንድ መልዕክቱ ላይ "ጥላቻው ከዚህ በላይ በቃኝ" ስለዚህ ገደልኩት ይላል።

ተጠርጣሪው በዩታ ካውንቲ እስር ቤት ውስጥ ያለ ዋስትና በእስር ላይ ይገኛል።

ማክሰኞ ዕለት ለመጀመርያ ጊዜ እስር ቤት የቀረበው ታይለር ሮቢንሰን አቃቤ ሕግ የተመሰረተበትን ሰባት ክሶች አንብቦለታል።

ክሶቹ ነፍስ ማጥፋት፣ያለፈቃድ የጦር መሣሪያ መተኮስ፣ ሁለት የሕግ ማደናቀፍ፣ ሁለት ምስክር ማባበል እና ሕጻናት በሚገኙበት አሰቃቂ ወንጀል መፈጸም ይገኙበታል።

አክሎም ከርክን ተኩሶ በመግደሉ የሞት ቅጣት እንዲፈረድበት አንደሚጠይቅ ተናግሯል።

ቻርሊ ከርክ በዩታ ቫሊ ዩኒቨርስቲ የዛሬ ሳምንት ረቡዕ ንግግር እያደረገ በነበረበት ወቅት ከጣሪያ ላይ በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ መሞቱ ይታወሳል።

ከ33 ሰዓታት ፍለጋ በኋላ በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ እስካሁን ድረስ ጥፋተኛ አለመሆኑን ወይንም ወንጀሉን መፈጸሙን ለፖሊስ አልተናገረም።

ተጠርጣሪው ወንጀሉን መፈጸሙ እስኪረጋገጥ ድረስ እንደ ነጻ ሰው የመቆጠር መብት እንዳለው ዐቃቤ ሕጉ ተናግረው ጉዳዩ ዳኞች ከተሰየሙ በኋላ መታየት ይጀምራል ብለዋል።

ማክሰኞ ዕለት አቃቤ ሕግ አሰባስቧቸዋል ያሉትን ማስረጃዎች የዘረዘሩት ዐቃቤ ሕግ፣ ተከሳሹ ግድያውን መፈጸሙን የገለፀበት ማስታወሻ፣ ለግድያው ጥቅም ላይ ውሏል በተባለው መሳሪያው ቃታ ላይ የተገኘ ዲኤንኤ መኖሩን ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግ ግሬይ ማክሰኞ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መግደሉን አምኖበታል ስላሉት ለጓደኛው የተላከ የጽሑፍ መልዕክት ሲናገሩ "የምትሰራውን ትተህ ኪቦርዱ ስር ያስቀመጥኩልህን ተመልክት" እንደሚል ገልፀዋል።

ከመርማሪዎች ጋር ትብብር እያደረገ ነው የተባለ እና ስሙ ያልተጠቀሰው ጓደኛው የተባለውን ማስታወሻ ካነበበ በኋላ "ምን????????? እየቀለድክ ነው አይደል????????" ሲል መልሶለታል።

ግሬይ ሁለቱ ጓደኛሞች የተለዋወጧቸውን ረዥም የጽሑፍ መልዕክቶች ካነበቡ በኋላ የፍቅር ጓደኛሞች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ባለሥልጣናት የተጠርጣሪው ጓደኛ ጾታ ልውጥ(ትራንስጄንደር) መሆኑን እና ከወንድ ወደ ሴት ሽግግር እያደረገ ያለ እንደሆነ ገልፀዋል።

በአንድ የመልዕክት ልውውጣቸው ላይ ለምን ከርክን ገደልከው ሲል ተጠርጣሪን ጠይቋል።

"ጥላቻውን ከዚህ በላይ መሸከም አልችልም" ሲል መመለሱን ግሬይ ጠቅሰው "አንዳንድ ጥላቻዎች በድርድር የምታስወግዳቸው አይደሉም" ብሏል።

ተከሳሽ "እውነቱን ለመናገር ይህንን ሚስጥር እስከ ሕይወቴ ፍጻሜ ድረስ ይዤው መኖር ፈልጌ ነበር። በዚህ ውስጥ ስለከተትኩህ አዝናለሁ" ሲል መጻፉ ተነግሯል።

አብሮ አደሩ በምላሹ "የገደልከው አንተ አይደለህም አይደል????" ሲል ሲጠይቀው ተከሳሹ "እኔ ነኝ፤ አዝናለሁ" ሲል መልሷል።

ዐቃቤ ሕግ ግሬይ ቤተሰቡ ልጃቸው በቻርሊ ከርክ ግድያ ላይ ተሳትፏል ብለው እንዴት ሊጠራጠሩ እንደቻሉም አስረድተዋል።

ግድያው ከተፈጸመ አንድ ቀን በኋላ የተጠርጣሪው ቪዲዮ ይፋ ሲሆን የተመለከቱት እናቱ ልጃቸውን እንደሚመስል ለባለቤታቸው መናገራቸውን ጠቅሰዋል።

ለልጃቸው ደውለው ወንጀሉን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረው ሰው እርሱን አንደሚመስል ሲጠይቁት የዛን ዕለት ቤት መሆን ፈልጎ አለመውጣቱን ተናግሯል።

በኋላ ላይ አባቱ ጉዳዩን መልሰው አንስተው ሲጠይቁት የራሱን ሕይወት ሊያጠፋ እንደሚችል በማመልከት ምላሽ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪው ወደ ወላጆቹ ቤት እንዲመጣ ካሳመኑት እና ከመጣ በኋላ ገዳዩ ሊሆን እንደሚቸል ፍንጭ ሰጥቷቸዋል።

ከዚያም ከመታሰር ይልቅ "ራሱን ማጥፋት" ፈልጎ እንደነበር መናገሩን ግሬይ ጠቅሰዋል።

የቤተሰቡ ጓደኛ በሆነ እና ጡረታ በወጣ የፖሊስ ባልደረባ እርዳታ ቤተሰቡ እጁን እንዲሰጥ አሳምነውት ከ33 ሰዓታት ፍለጋ በኋላ ባለፈው ሳምነት ሐሙስ በቁጥጥር ስር ውሏል።

ተጠርጣሪው ለቤተሰቦቹ ከርክን በሚያመለክተው ንግግሩ ላይ "እጅግ ብዙ ክፉ ነገር አለ እንዲሁም ሰውየው በጣም ብዙ ጥላቻን ያስፋፋል" ማለቱን ተናግረዋል።

እናቱ ለመርማሪዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልጃቸው የበለጠ ፖለቲከኛ እየሆነ መጥቷል ማለታቸውን ግሬይ ጠቅሰው የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት እና የጾታ ልውጥ ሰዎች መብት ደጋፊ እየሆነ መምጣቱን እንዲሁም ከጾታ ልውጥ ሰው ጋር ግንኙነት መጀመሩን ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግ ከርክ የተገደለው በጾታ ልውጥ ሰዎች ላይ ባለው አመለካከት መሆን አለመሆኑን ተጠይቀው "ያ የዳኞች ውሳኔ ነው የሚሆነው" በማለት ከመመለስ ተቆጥበዋል።

ግሬይ አክለውም ከርክ በጾታ ልውጥ ሰዎች ስለሚፈጸም የጅምላ ግድያ ተጠይቆ ምላሽ እየሰጠ ባለበት ወቅት በጥይት መመታቱን ተናግረዋል።

የተተኮሰችዋ ጥይት ሕጻናትን እንዲሁም ከርክን ጥያቄ የጠየቀውን ግለሰብ አልፎ እንደመታው ዐቃቤ ሕጉ አብራርተዋል።

ግሬይ አክለውም የተጠርጣሪው ዲኤንኤ ግድያው በተፈጸመበት መሳሪያ ቃታ ላይ መገኘቱን ተናግረዋል።

የተጠርጣሪው አባት መሣሪያው ከአባታቸው መሣሪያ ጋር እንደሚመሳሰል መናገራቸውን አብራርተው፣ ግድያው ከተፈጸመ በኋላ ልጃቸውን ባናገሩበት ወቅት መሣሪያውን ፎቶ አንስቶ እንዲልክላቸው ቢጠይቁትም ምላሽ አለመስጠቱን አስረድተዋል።

ተከሳሹ ለአብሮ አደሩ በላከው የጽሑፍ መልዕክት ላይ ከግድያው በኋላ ስለነበረው እንቅስቃሴ ዝርዝር መረጃ ልኳል።

ተከሳሹ ምስክሮችን በማባባል ወንጀል መከሰሱን የገለፁት ዐቃቤ ሕጉ ጓደኛው መልዕክቶቹን በሙሉ እንዲያጠፋ እና ጥያቄ ከቀረበለት ምንም እንዳይናገር መጠየቁን ተናግረዋል።