የዚህን ዓመት የሰላም ሽልማት ማን ያሸንፋል? ስድስቱ አወዛጋቢ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዎች

የዚህ ዓመት የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ መስከረም 30 2018 ዓ.ም. ይፋ ይደረጋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለረዥም ጊዜ ይህንን ሽልማት በርካታ ጦርነቶችን በማስቆማቸው የተነሳ እንደሚገባቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የእስራኤሉ ጠቅይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለኖቤል የሰላም ሽልማት ዕጩ ማድረጋቸውን ይፋ አድርገዋል።

ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሸልማት ማግኘት የረጅም ጊዜ ህልማቸው እንደሆነ በተለያዩ ጊዜ ያደረጓቸው ንግግሮች ጠቁመዋል።

"አሁን ይህንን በምናቀርብበት ወቅት ለሰላም በር እየከፈቱ ነው። በቀጣናው ከአንድ አገር ወደ ሌላ ይህንኑ ተግባራዊ እያደረጉ ነው" ሲሉ ኔታንያሁ ለኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴ የላኩትን ደብዳቤ ለትራምፕ ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል።

ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት ይገባቸዋል ሃሳብ የመጣው ከኔታንያሁ ብቻ ሳይሆን ፓኪስታን በበኩሏ በሕንድ እና በፓኪስታን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ አስተዋጽኦ አድርገዋል በሚል ትራምፕን በዕጩነት ለማቅረብ ማቀዷን ከጥቂት ሳምንታት በፊት አስታውቃ ነበር።

በማግስቱ አሜሪካ የኢራን የኒውክሌር ይዞታዎችን በቦምብ መደብደቧን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከፍተኛ ትችት ቀርቦበታል።

በዓለም ላይ ካሉ ስመ ጥር ሽልማቶች መካከል አንዱ የኖቤል ሽልማት ነው። የኖቤል የሰላም ሽልማት በስዊድናዊው ሳይንቲስት፣ ነጋዴ እና በጎ አድራጊ አልፍሬድ ኖቤል ከተፈጠሩ ስድስት ሽልማቶች አንዱ ነው።

የኖቤል ኮሚቴ ስድስት ሽልማቶችን ይሰጣል። እነዚህም የፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ሥነ-ልቦና ወይም ሕክምና፣ ሥነ-ጽሑፍ፣ ኢኮኖሚክስ እና ሰላም ናቸው።አሸናፊዎቹ የሚመረጡት በኖርዌይ ፓርላማ በተመረጡ የአምስት ሰዎች ኮሚቴ ነው።

ትራምፕ ቢያሸንፉ አወዛጋቢ መሆናቸው አያጠራጥርም፤ ሆኖም የኖቤል የሰላም ሽልማቶች አብዛኛውን ጊዜ ፖለቲካዊ ይዘት ስለሚኖራቸው ከሌሎች የኖቤል ሽልማቶች አንጻር ሲታይ በተገቢነታቸው ዙሪያ አወዛጋቢ ሆነው ቆይተዋል።

የኖቤል የሰላም ሽልማት ከተቀበሉ እና ብዙ ካወዛገቡ አሸናፊዎች መካከል ስድስቱ የሚከተሉት ናቸው።

ባራክ ኦባማ

የቀድሞ አሜሪካ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ በአውሮፓውያኑ 2009 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ይፋ ሲደረግ፤ ኦባማን ሳይቀር ያስደነቀ እና ያስገረመ ነበር።

ኦባማ ከአምስት ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 2020 ላይ በጻፉት ግለ ታሪካቸው ላይ የሰላም ኖቤል አሸናፊ መሆናቸውን ሲሰሙ፤ የመጀመሪያ ምላሻቸው "ምን ስላደረኩ?" የሚል እንደነበረ ገልጸዋል።

ኦባማ የሰላም ኖቤል ማሸነፋቸው የተገለጸው ሥልጣን ከያዙ ገና በዘጠነኛው ወራቸው ነበር። በተጨማሪም የሰላም ተሸላሚ ዕጩ ማቅረቢያ ቀነ ገደብ ያለፈው የአባማ ሲመት ከተፈጸመ ከ12 ቀናት በኋላ ነበር

ተቃዋሚዎች ውሳኔው የፈጠነ እና ጊዜውን ያልጠበቀ ነው ሲሉ ሽልማቱ ለኦባማ መሰጠቱን አጥብቀው ተችተው ነበር።

ኦባማ አሜሪካንን ለሁለት የሥልጣን ዘመን በፕሬዝደንትነት ባስተዳደሩበት ዓመታት ጦራቸው በአፍጋኒስታን፣ ኢራቅ እና ሶሪያ ተዋግቷል።

የኖቤል ተቋም ዳይሬክተር የነበሩት ጌይር ሉንደስታድ ጊየር ለኦባማ ሽልማት እንዲሰጥ የወሰነው ኮሚቴ በውሳኔው መጸጸቱን ከዓመታት በፊት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ዐቢይ አሕመድ

ከስድስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ሽልማት ያገኙት በአትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በድንበር ግጭት ለ20 ዓመታት የዘለቀውን ጠላትነት ለማስቆም በመቻላቸውን እንደሆነ ተጠቅሷል።

ዐቢይ ሽልማቱን ከተቀበሉ ከአንድ ዓመት በኋላ ግን የኮሚቴው ውሳኔ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄዎች መነሳት ጀመሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ትግራይ ጦራቸውን ማዝመታቸው በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትችትን አስከትሏል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል፣ የኤርትራ ሠራዊት እና ሌሎች የክልል አጋሮች በጋራ ሆነው ከትግራይ ኃይሎች ጋር ያደረጉት ጦርነት በደም አፋሳሽነቱ ይጠቀሳል።

በጦርነቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አልቀዋል፤ እንዲሁም በሚሊዮን የሚቆጠር ነዋሪ ተፈናቅሏል።

ረሃብ፣ መደፈርን ጨምሮ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ውለውበታል በሚባለው በዚህ ጦርነት የጦር ወንጀሎች፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እና የዘር ማጽዳት እንደተፈጸሙ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶችን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ያወጧቸው ሪፖርቶች ያሳያሉ።

የትግራዩ ጦርነት በፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም ስምምነት ቢቋጭም፤ ከዚያ በኋላ የአማራ ክልል ግጭት ተከስቶ እንደተፋፈመ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል እና የፋኖ ታጣቂዎች በሚፋለሙበት በዚህ ግጭት ሰላማዊ ሰዎች በድሮኖች መገደላቸውን የተለያዩ ሪፖርቶች አሳይተዋል።

ከአማራ ግጭት በተጨማሪ በኦሮሚያም እንዲሁ መከላከያ ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር በሚያደርገው ውጊያ ሰላማዊ ሰዎች በተለያዩ ስፍራዎች መገደላቸውን ሪፖርቶች ገልጸዋል።

ሄንሪ ኪሲንጀር

በአውሮፓውያኑ 1973 የወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሄንሪ ኪሲንጀር የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆኑ።

ኪሲንጀር ብዙ ተቃውሞ እና ትችት ያስተናገደውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን አስፈጽመዋል። በካምቦዲያ የቦምብ ጥቃት እንዲፈጸም አድርገዋል። በደቡብ አሜሪካ ለአምባገነን መንግሥታት የጦር መሪዎች ድጋፍ መስጠታቸውም ሌላው የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩን ካስተቻቸው ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።

ኪሲንጀር የኖቤል የሰላም ሽልማትን ያገኙት ከሰሜን ቬትናም መሪ ሌ ደክ ቶ ጋር በመሆን የቬትናም ጦርነት ቆሞ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ጥረት በማድረጋቸው ነው።

ለኪሲንጀር የኖቤል የሰላም ሽልማት መሰጠት የለበትም በሚል ሁለት የኖቤል ኮሚቴ አባላት ሥራቸውን ለቅቀው ነበር።

የኪሲንጀር አሸናፊነት ይፋ ሲደረግም፤ ኒው ዮር ታይምስ ሽልማቱን "ኖቤል ዋር ፕራይዝ" (የኖቤል የጦርነት ሽልማት) ሲል ጠርቶት ነበር

አን ሳን ሱ ቺ

አን ሳን ሱ ቺ በምያንማር የነበረውን ወታደራዊ አገዛዝ ሰላማዊ በሆነ መልኩ በመታገላቸው በከፍተኛ ድጋፍ በአውሮፓውያኑ 1991 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆኑ።

ሽልማቱን ከተቀበሉ ከ20 ዓመታት በኋላ ግን አን ሳን ሱ ቺ የምያንማር መሪ ሳሉ የአገሪቱ ጦር በንጹሃን ሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ የተፈጸመውን የግፍ ጭፍጨፋ ማስቆም አልቻሉም።

በተባበሩት መንግሥታት 'የዘር ማጥፋት' ስለተባለው የጅምላ ግድያ ጥቃት ፖለቲከኛዋ ምንም ሳይሉ አልፈዋል።

ይህም በኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዋ ላይ ከፍተኛ ትችትን አስከትሏል።

በርካቶችም አን ሳን ሱ ቺ ያገኙትን የሰላም ሽልማት እንዲነጠቁ የሚጠይቁ ድምጾች በስፋት ተሰምተዋል። የኖቤል ሽልማቶች ለአሸናፊው ከተሰጡ በኋላ ሽልማቱን ሊነጠቅ አይችልም።

ያሲር አራፋት

በሕይወት የሌሉት የፍልስጤም መሪ የነበሩት ያሲር አራፋት በኦስሎ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ለነበራቸው አስተዋጽኦ፣ ከወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ይትዛህክ ራቢን እና ከእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሺሞን ፔሬዝ ጋር በጋራ በአውሮፓውያኑ 1994 ላይ የኖቤል ሽልማትን ተቀብለዋል።

በአውሮፓውያኑ1990 ላይ በኦስሎ የተደረሰው የሰላም ስምምነት በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል ሰላም ያመጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።

በትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ለነበራቸው ያሲር አራፋት የኖቤል የሰላም ሽልማት መስጠትን በእስራኤል እና በሌሎችም ትችትን አስከትሏል።

በእርግጥ የአራፋት ለኖቤል የሰላም ሽልማት በዕጩነት መቅረብ በኖቤል ኮሚቴ አባላት መካከል አለመግባባትን ፈጥሮ ነበር።

የኖቤል ኮሚቴ አባል የነበሩት የኖርዌይ ዜጋ የሆኑት ፖለቲከኛው ኬር ክሪስቲያንሰን የአራፋት መመረጥን በመቃወም ከኮሚቴ አባልነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው ለቀው ነበር።

ዋንጋሪ ማታይ

በሕይወት የሌሉት ኬንያዊቷ የማኅብረሰብ አንቂ ዋንጋሪ ማታይ የኖቤል የሰላም ሽልማትን በአውሮፓውያኑ 2004 በማሸነፍ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሴት ሆኑ።

ዋንጋሪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ለፈጠሩት የአረንጓዴ እንቅስቃሴ ነበር የኖቤል ሽልማትን ያገኙት።

ይሁን እንጂ የማኅብረሰብ አንቂዋ ሽልማት ጥይቄ ይነሳበት የጀመረው ስለ ኤችአይቪ ኤድስ የሚሰጡት አስተያየት መሰማት ከጀመረ በኋላ ነበር።

ዋንጋሪ ማታይ ኤችአይቪ ቫይረስ ጥቁሮችን ለማጥፋት ሆነ ተብሎ በላብራቶሪ የተሠራ ቫይረስ፣ 'ባዮሎጂያዊ መሳሪያ' ነው የሚል አስተሳሰብን ያራምዱ ነበር።

የዋንጋሪ ማታይን ሃሳብን ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ግን የለም።

የኖቤል ሽልማት ትልቁ ክፍተት- የማህተመ ጋንዲ አለመሸለም

የኖቤል ሽልማት ለሚገባው ግለሰብ ሳይሰጥ ቀርቷል በሚልም ሽልማቱን በሚሰጠው ኮሚቴ ላይ ቅሬታ ሲነሳ ቆይቷል።

በሰላም ዘርፍ፤ የኖቤል ሽልማት የሚገባቸው ግን ሽልማቱን አላገኙም ተብሎ ስማቸው በተደጋጋሚ ከሚነሱት መካከል ማህተመ ጋንዲ ዋነኛ ናቸው።

ሕንዳዊው ሰላማዊ ታጋይ፤ እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን የሰላም ትግል መለያ የሆኑት ጋንዲ በተደጋጋሚ ለሽልማቱ ቢታጩም አሸናፊ ሆነው ግን አያውቅም።

በአውሮፓውያኑ 2006 የታሪክ ምሁሩ እና የወቅቱ የኖቤል የሰላም ኮሚቴ ፕሬዝደንት ጊኤር ሉንደስታድ፤ ለጋንዲ አበርክቶዎች እውቅና ሳይሰጥ መቅረቱ በኖቤል የሰላም ታሪክ ውስጥ ትልቁ ክፍተት ነው ብለው ነበር።