ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የድማሚት ፈንጂ አምራቹ እና ከኖቤል ሽልማቶች ጀርባ ያለው አልፍሬድ ኖቤል
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቂያ ላይ አሜሪካ በጃፓኖቹ ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ከተሞች ላይ ከፈጸመችው የአውቶሚክ ቦምብ ጥቃት በተረፉት ሰዎች የተቋቋመው ኒሆን ሂዳንኪዮ የተባለው ቡድን የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።
በአውሮፓውያነ 1945 ከተፈጸመው አሰቃቂው ጥቃት 10 ዓመታት በኋላ የተመሠረተው ይህ ቡድን የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ከዓለም እንዲወገዱ በሚያደርገው ጥረት ነው በኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆነው።
በዓለም እጅግ የተከበረው የኖቤል ሽልማት በተለያዩ መስኮች በየዓመቱ በሥራቸው ለተመረጡ ግለሰቦች እና ቡድኖች የሚሰጥ ሲሆን፣ የኖቤል የሰላም ሽልማትም የዚህ አካል ነው።
ለዚህ ሽልማት መጀመር ምክንያት የሆነው ስዊድናዊው የንግድ ባለቤት ኢንጂነር አልፍሬድ ኖቤል ነው። ግለሰቡ ሐብቱን ለዚሁ ሽልማት እንዲሆን አበርክቷል።
ግለሰቡ ዝነ እና ሐብት ያገኘው ድማሚት የሚባለውን ከባድ ፈንጂ በመፍጠር ነው። በዚህም ኖቤል የግዙፍ ጦር መሳሪያ ማምረቻ ድርጅት ባለቤት ቢሆንም፣ በመጨረሻም ገንዘቡ ለዓለም ሰላም አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሰዎች በሽልማት እንዲሰጥ ወስኗል።
አልፍሬድ ኖቤል እንዴት ወደ ሐብት ማማ ወጣ?
እአአ በ1833 በስዊዲን መዲና ስቶክሆልም ውስጥ የተወለደው አልፍሬድ ኖቤል፣ የኢንጂነር ኢማኑኤል ኖቤል እና የአንድሪቴ አህልሴል ልጅ ነው።
አባቱ ኢማኑኤል የፈጠራ ባለቤትነት መብት ያገኘባቸው በርካታ ፈጠራዎችን አሉት። አንደኛው ፈጠራው የወታደሮች ቦርሳ ነው። ቦርሳው ውሃ ውስጥ እንደመንሳፈፊያ እና በድካም ጊዜ ደግሞ እንደትራስ ሆኖ ያገለግላል።
ነገር ግን ሥራው ሳይሰምርለት ቀርቶ በ1833 ለኪሳራ በመዳረጉ ከአራት ዓመታት በኋላ አበዳሪዎቹን ሽሽት ከስዊድን ወደ ሩሲያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ኮበለለ።
ከባላበት ወገን የሆነችው እናቱ አንድሪቴ ቤተሰቡን ለመደገፍ በሚል አምስት ዓመታትን ስቶክሆልም በሚገኝ ግሮሰሪ ውስጥ ለመሥራት ተገደደች።
አማኑኤል ኖቤል ሩሲያ ውስጥ መሥራት ጀመረ። ለሩሲያ ጦር መሳሪያ ለማቅረብ በሴንት ፒተርስበርግ ሱቅ ከፈተ። የሩሲያ ባሕር ኃይልም የሚያዘጋጀውን የባሕር ውስጥ ቦምቦቹን እንዲጠቀም አሳምኗል። ቦምቦቹ እአአ ከ1853 እስከ 1856 በተደረገው የክሬሚያ ጦርነት ሴንት ፒተርስበርግን ከብሪታንያ የጦር መርከቦች ለመከላከል ጥቅም ላይ ውለው ነበር።
በዚህ ጊዜ ንግዱ ትርፋማ ሆነለት። እአአ በ1842 ደግሞ የተቀረውን ቤተሰቡን ወደ ሩሲያ ወሰደ። አልፍሬድ እና ወንድሞቹ ሳይንስ እና የቋንቋ ትምህርቶችን በግል አስተማሪዎች ተከታትለዋል።
አልፍሬድ የኬሚስትሪ ትምህርቱን እንዲቀጥል በ1850 ወደ ፓሪስ ተላከ። ፓሪስ እያለም ናይትሮግሊሰሪንን የፈጠረውን ጣሊያናዊ ሳይንቲስት አስካኒዮ ሶብሬሮን ተዋወቀ።
ሶብሬሮ ያዘጋጀው ንጥረ ነገር በጣም የሚፈነዳ ፈሳሽ ነበር። ከባሩድ ብዙ እጥፍ የሚበልጥ ነበር። ለሙቀት ወይም ለግፊት ለውጦች ከተጋለጠ ይፈነዳል። ደኅንነቱን መጠበቅ ከተቻለ በጣም ትርፋማ ሊሆን እንደሚችል አልፍሬድ ኖቤል አሰበ።
ከክሬሚያ ጦርነት ማብቃት በኋላ በሩሲያ የነበረው ንግድ ሥራው የተቀዛቀዘበት ኢማኑኤል ኖቤል እአአ በ1863 በድጋሚ ከሰረ። ከዚያም ወደ ስቶክሆልም ተመልሶ ከልጁ ከአልፍሬድ ጋር በመሆን ናይትሮግሊሰሪን ላይ ሙከራዎችን ማድረግ ጀመሩ።
እአአ በ1864 ኬሚካሉን የተከመቸበት ክፍል ፈንድቶ የአልፍሬድ ወንድም የሆነውን ኤሚልን ጨምሮ ብዙ ሰዎችን ገደለ።
የስቶክሆልም ባለሥልጣናት በከተማው ወሰን ውስጥ የሚደረገውን የንጥረ ነገሩን ሙከራዎች ከለከሉ። አባት እና ልጅ ወርክሾፓቸውን ከስቶክሆልም ውጪ ወደምትገኘው ቪንተርቪከን አዛወሩ።
እአአ በ1866 አልፍሬድ ኖቤል ናይትሮግሊሰሪንን ከአሸዋ ጋር በማዋሃድ በቀላሉ እንዳይፈነዳ ማድረግ ቻለ። ይህም ሊጥ ስለሚመሰል በተለያየ መያዣ ውስጥ ለማስገባት የሚመች ሆነ። በተቦረቦሩ ድንጋይዎች ውስጥ ሲገቡ ደግሞ በመፈንዳት ድንጋዩን ይበታትኑት ጀመር።
አዲሱን ፈንጂ “ዳይናማይት” ብሎ ሰየመው። እአአ በ1867 ደግሞ የፈጠራ ባለቤትነት መብት አገኘበት። ዳይናማይት (ድማሚት) የማዕድን ቁፋሮ፣ የድንጋይ ማውጣት፣ የመንገድ እና የባቡር ሃዲድ ግንባታ ሥራ ላይ ተፈላጊ ሆነ።
እአአ በ1898 በተካሄደው በስፔን-አሜሪካ ጦርነት ወቅት ደግሞ “ዳይናማይት” የተባለ ሽጉጥ ጥቅም ላይ ዋለ።
በሕይወት ዘመኑ ወደ 355 የፈጠራ ባለቤትነት ያገኘው አልፍሬድ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ትምህርት የመቀበል ችግር ካለባቸው ተማሪዎች መካከል መማሩን በኢንግሪድ ካርልበርግ የተጻፈው የኖቤል የሕይወት ታሪክ ያስረዳል።
የኖቤል ሽልማቶች እንዴት ተጀመሩ?
አልፍሬድ ኖቤል እአአ በ1896 ሕይወቱ ሲያልፍ ወደ ጦር መሳሪያ ማምረቻ ድርጅትነት የተቀየረውን ቦፎርስ የተባለውን የስዊድን ብረታ ብረት ኩባንያን ጨምሮ 90 ፋብሪካዎች ከ20 በሚበልጡ የዓለም አገራት ነበሩት። ወንድሞቹ ሩሲያ ውስጥ በነበራቸው የነዳጅ ንግድ ላይ ኢንቨስት በማድረግም በሐብት ላይ ሐብት አፍርቷል።
ኖቤል በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ፣ በሕክምና ወይም በፊዚዮሎጂ፣ በሥነ ጽሑፍ እና በሰላም ዘርፎች የሰውን ልጅ ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ላደረጉ ሰዎች ዓመታዊ ሽልማቶችን ለመስጠት ሐብቱን (3 ሚሊዮን ዶላር) አበርክቷል።
አሸናፊውን የመምረጥ ኃላፊነት የተሰጠው ደግሞ የሮያል ስዊድን የሳይንስ አካዳሚ ነው። አካዳሚው እአአ በ1884 ኖቤልን በአባልነት ተቀብሎታል።
ቤተሰቦቹ በውሳኔው ደስተኛ አልነበሩም። ተቋሙን ለመመሥረት እየሞከረ ከነበረው የኖቤል ረዳት ራግናር ሶህልማን ጋርም ለአራት ዓመታት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ሲሟገቱ ከርመዋል።
የስዊድን መንግሥት ጉዳዩ ካርልስኮጋ በምትባል እና ኖቤል ይኖርባት በነበረባት አነስተኛ ከተማ ውስጥ እንዲወሰን ትዕዛዝ አስተላለፈ።
የመጀመሪያዎቹ የኖቤል ሽልማቶች እአአ በ1901 ተሰጡ። አሸናፊዎቹ እንደ ዛሬዎቹ አሸናፊዎች ሁሉ 9 ሚሊዮን ክሮነር አግኝተዋል።
የሰላም ሽልማት ለምን ይሰጣል?
ከኖቤል ታሪክ ጋር በተያያዘ አንድ የሚነገር ያልተረጋገጠ ታሪክ አለ። እሱም ኖቤል ገንዘቡን ለሽልማቱ እንዲሰጥ ያደረገው አንድ የፈረንሳይ ጋዜጣ ያተመው ዜና ነው።
በዚህም የፈረንሳይ ጋዜጦች በ1888 ኖቤል በሕይወት እያለ በስህተት ስለመሞቱ ተቀባብለው ሲዘግቡ፣ አንደኛው ጋዜጣ ደግሞ የሕይወት ታሪኩን የሚገልጽ ጽሁፍ “የሞት ነጋዴው” በሚል ርዕስ አተመ። በዚህም ኖቤል ህሊናውን ለማሳረፍ ሲል የሰላም ሽልማትን ለማቋቋም መወሰኑ ይነገራል።
የበለጠ ሊሆን የሚችለው ታሪክ ግን በርታ ኪንስኪ ቮን ቺኒክ አን ቴታው (በኋላም ካውንተስ በርታ ቮን ሳትነር ተብላለች) ከተባለች ሴት ጋር ኖቤል የነበረው ጓደኝነት ነው።
እሷ ታዋቂ ኦስትሪያዊት የሰላም አቀንቃኝ እና በብዙ ቁጥር የተቸበቸበ ‘ሌይ ዳውን ዩር አርም’ የተሰኘ ልብ ወለድ ደራሲ ነበረች። ፀሐፊው ሆናም ለተወሰነ ጊዜ አገልግላለች። ሥራዋን ትታ ትዳር ስትመሠርትም ግንኙነታቸው አልተቋረጠም ነበር። ለሰላም እንቅስቃሴ ገንዘብ ከመስጠት ይልቅ የሰላም ሽልማት እንዲያዘጋጅ ተጽዕኖ አድርጋበታለች ተብሎ ይታሰባል።
“የጦርነትን አስፈሪነት ለመቃወም በነበራት ድፍረት” ምክንያት እአአ በ1905 የሰላም ሽልማትን ያገኘች የመጀመሪያዋ ሴት ሆናለች።