ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በባለሥልጣናት ላይ “ጥቃት ለመፈጸም አሲረዋል” የተባሉ ግለሰቦች መያዛቸው ተነገረ
በመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ጥቃት በመፈጸም ሁከት እና ብጥብጥ ለመቀስቀስ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት የደኅንነት ጥምር ቡድን አስታወቀ።
ይህ የፀጥታ እና የደኅንነት የጋራ ግብር ኃይል የተባለው አካል በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጠሪዎች ጥቃቱን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ለመፈጸም ሲንቀሰቀሱ ነበር ብሏል።
ግብረ ኃይሉ ደረስኩባቸው ያላቸው ቡድኖች “በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በአዳማ እና በድሬ ዳዋ ከተሞች ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች በመፈጸም አገራዊ ሁከት እና ብጥብጥ ለማስነሳት ሲንቀሳቀሱ ነበር” ብሏል ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ባሰራጨው መግለጫ።
ጨምሮም የተባለውን ጥቃት ለመፈጸም በአማራ ክልል፣ በአዲስ አበባ እና በሌሎች ክልሎች መቀመጫቸውን ያደረጉ ምሁራን፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለቤቶችን እና የማኅበረሰብ አንቂዎችን የያዘ ህቡዕ መዋቅር በምስጢር ሲንቀሳቀስ ነበር ብሏል።
የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብር ኃይል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በመግደል ሁከት እና ብጥብጥ ለመፈጠር ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር አውያቸዋለሁ ያላቸውን ተጠርጣሪዎች የስም ዝርዝር እና ፎቶግራፎችን ጨምር ይፋ አድርጓል።
ግብረ ኃይሉ በዚህ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ይፋ ካደረጋቸው ግለሰቦች መካከል በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ፖለቲካዊ አስተያየቶችን ሲሰጡ የሚታወቁት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው ይገኙበታል።
በተጠቀሰው ህቡዕ እንቅስቃሴ ምክንያት በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች “ወታደራዊ ክንፍ በማደራጀት በጦር መሣሪያ የታገዘ የከተማ ውስጥ ጥቃት የመፈፀም ዕቅድ ነበራቸው” ያለ ሲሆን፤ በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ጥቃት በመፈፀም ሕዝቡን የማሸበር ተልዕኮ ነበራቸው ብሏል።
“. . . በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ጭቆና ውስጥ ይገኛል የሚል ቅስቀሳ በማድረግ በሃይማኖት፣ በብሔር እንዲሁም ከእኛ ውጪ አገሪቷን ሌላ ማስተዳደር የለበትም በሚል የፖለቲካ ፅንፈኝነት ዓላማ ዙሪያ ደጋፊዎችን ለማሰባሰብ ሞክረዋል” ብሏል ግብረ ኃይሉ።
“ሕዝቡን ነጻ እናወጣለን የሚል የአመጽ እንቅስቃሴ ለማካሄድ ሲደራጁ” ነበሩ የተባሉ ግለሰቦች በአማራ ክልል እና በአዲስ አበባ እንዲሁም በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎችን የማደራጀት ሥራዎች ሲሰሩ ነበር ብሏል።
ቡድኑ በአዲስ አበባ ለዘረጋው መዋቅሩ ጦር መሣሪያዎች፣ ፈንጂዎች እና ቦምቦችን አስገብቷል ያለ ሲሆን፣ ሌሎች የህቡዕ አደረጃጀቱ ቡድን አባላትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብሏል።
ተደራጅተው ጥቃቶችን ለመፈጸም አሲረዋል የተባሉት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያሳወቀው የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብር ኃይል የዋነኞቹ የአገሪቱ ደኅንነት ተቋማት ጥምረት ነው።
በዚህም ውስጥ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት እና የመረጃ መረብ ደኅንነት ተቋም ይገኙበታል።