የተወካዮች ምክር ቤት የዶ/ር ጫላ ዋታን ያለመከሰስ መብት አነሳ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፓርላማ አባል የሆኑትን ዶ/ር ጫላ ዋታ ያለመከሰስ መብት አነሳ።

ፓርላማው የቀድሞ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት የነበሩትን ዶ/ር ጫላ ዋታ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የቀረበውን ጥያቄ ዛሬ መጋቢት 25/2015 ዓ.ም ባደረገው 13ኛው መደበኛ ጉባኤ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ወስኗል።

የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ዶ/ር ጫላ ዋታ የቡሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት የመንግሥት ግዢ ሥርዓትን ሳይከተሉ የተለያዩ ግዢዎችን በመፈጸማቸው ነው የሕግ ከለላ መብታቸው እንዲነሳ ውሳኔ የተላለፈው።

የፍትሕ ሚኒስቴር የዶ/ር ጫላ ዋታ የሕግ ከለላ እንዲነሳ ለምክር ቤቱ የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎም ቋሚ ኮሚቴው ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔውን አሳልፏል።

የውሳኔ ሀሳቡን የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ በዝርዝር አቅርበዋል።

ዶ/ር ጫላ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በነበሩበት ጊዜ ከመንግሥት የግዢ አሰራር ውጪ የተጋነነ ግዢ እንዲፈፀም በማድረግ፣ በስማቸው በተመዘገበ የባንክ አካውንት በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በመግባቱ፣ በባለቤታቸው ስም የመኖሪያ ህንጻ ተመዝግቦ መገኘቱ በዋነኛነት ተጠርጣሪ የሆኑባቸው ነጥቦች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ዶ/ር ጫላ ዋታ የመንግሥት ግዢ ሕግ ከሚፈቅደው አሰራር ውጪ የውስጥ ገቢ ማስገኛ በሚል ቢኤችዩ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚል አማካሪ ድርጅት በማቋቋም እና በስማቸው የንግድ ፈቃድ ማውጣታቸው ተጠቅሷል።

በዚህም ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ የግንባታ ሥራዎች የማማከር አገልግሎት ለመስጠት በቀጥታ ግዢ በመፈጸም መዋዋል እንዲሁም ለአማካሪ ድርጅቱ እና ላጸደቃቸው ተቋራጮች ክፍያዎች በመፈጸም በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል የሚል ጥቆማም ቀርቧል።

ይህንን ተከትሎ ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው የወንጀል ማጣራት 196 ሚሊዮን ብር አካባባቢ የሚያወጡ የተለያዩ የግንባታ ተዋፅኦዎች ለዘጠኝ ተቋራጮች ከመንግሥት የግዢ አዋጅ እና አፈጻጸም መመሪያ ውጭ በቀጥታ እንዲፈጸም ማድረጋቸው ተጠቅሷል።

ዩኒቨርስቲው ለመሠረተ ልማት ግንባታ የተፈቀደለትን የካቲታል ገንዘብ ያለ አግባብ በመጠቀም የግዢ ደንብ እና ሕግ ባልተከተለ መልኩ ዋጋቸው 116 ሚሊዮን ብር የሆኑ አስራ አራት ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎች በግል ተቋራጭ ድርጅት ስም ግዢ ፈጽመዋል ተብሏል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ ተሽከርካሪ እና ማሽነሪዎቹ በዩኒቨርስቲው ገንዘብ የተገዙ ቢሆንም በግል ተቋራጮች ድርጅቶች ስም እንዲሆኑ አድርገዋል ተብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ተሽከርካሪ እና ማሽነሪዎቹ የተገዙበት ዋጋ እጅግ የተጋነነ እንደሆነም ተጠቅሷል።

ለምሳሌም ያህል የተጠቀሰው አንድ ደብል ጋቢና ፒክ አፕ የተሽከርካሪ ተቋራጭ ድርጅቱ ከአስመጭ 3 ሚሊዮን 300 ሺህ ብር ግዢ ቢፈጽምም 6 ሚሊዮን 174 ሺህ በሚገመት ብር እንደተገዛ ተቆጥሮ ከዩኒቨርስቲው ክፍያ ተፈጽሟል።

ሌላ ተሽከርካሪ እንዲሁ የተገዛው 1.6 ሚሊዮን ብር ቢሆንም 6.5 ሚሊዮን ብር ገደማ ተገዝቷል በሚል ከዩኒቨርስቲው ወጪ እንዲሆን መደረጉ ተጠቅሷል።

በተጨማሪም የ14ቱ ተሽከርካሪዎች እና ማሽነሪዎች ባለቤቶች የዩኒርስቲው ሳይሆን የሥራ ተቋራጭ ድርጅቶቹ እንዲሆኑ ማድረጋቸውም ተገልጿል።

“የተሰጣቸውን የመንግሥት ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ለራሳቸው የማይገባ ጥቅም በማግኘት እንዲሁም አማካሪ ድርጅት በሌለበት ከ11 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ ለተቋራጭ ድርጅቶች በመክፈል የመንግሥት እና የሕዝብ ገንዘብ እንዲባክን አድርገዋል” ተብሏል።

በዶ/ር ጫላ ዋታ እና በቢኤችዩ ላይ በተደረገው ማጣራትም የሚያንቀሳቅሱትም ሆነ ዳይሬክተሩ ራሳቸው መሆናቸው ተገልጾ፣ በተለያየ ጊዜም ከዩኒቨርስቲው ተቀንሶ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ወደ ድርጅቱ አካውንት እንደገባም ነው የተጠቆመው።

ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው እንደራሴ ከእሳቸው በተጨማሪ በባለቤታቸው እና በልጃቸው ስምም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እና ንብረት መገኘቱ ተገልጿል።

በምክር ቤት አባላት በኩል ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ከመቅረቡ በፊት ዶ/ር ጫላን ማነጋገራቸውን እና ተገቢው የማጣራት ሥራ መሰራቱ ተገልጿል።

ዶክተር ጫላ ዋታ በበኩላቸው የቀረበውን ያለመከሰስ መብት በዛሬው የፓርላማ ውሎ ተቃውመው ሃሳባቸውን አቅርበው በውሳኔው ላይ ድምጸ ተአቅቦ አስመዝግበዋል።

በቀጣይ በዶ/ር ጫላ ላይ በፖሊስ ምርመራ እንደሚደረግ እንዲሁም ክስ ይመሰረትባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።