ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቱርክ እና ሶሪያን በመታው የመሬት መንቀጥቀጥ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 2000 ተጠጋ
ቱርክ እና ሶሪያ በሚወሰኑበት የድንበር አካባቢ ባጋጠመው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ ሁለት ሺህ መጠጋቱን ባለሥልጣናት አሳወቁ።
ዛሬ ሰኞ ጠዋት በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በቱርክ አስካሁን ከአንድ ሺህ በላይ እንዲሁም በሶሪያ በኩል ደግሞ ወደ 800 የሚደርሱ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።
ቱርክ ከሶሪያ ጋር በምትዋሰንባት በደቡብ ምሥራቋ ጋዚያንቴፕ ግዛት ውስጥ ባጋጠመው በዚህ አደጋ በአጠቃላይ በሁለቱ አገራት ወደ ሁለት ሺህ እየተጠጉ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።
የነፍስ አድን ሠራተኞች በፍርስራሾች ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን ፈልጎ የማውጣት ሥራ እያከናወኑ ሲሆን፣ በዚህም የአደጋው ሰለባዎች ቁጥር እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል ተሰግቷል።
በርዕደ መሬቱ ከሞቱት በተጨማሪ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን፣ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ውድመት ማጋጠሙም ተዘግቧል።
የቱክር ፕሬዝዳንት ረሲፕ ኤርዶዋን ይፋ እንዳደረጉት በአገራቸው ግዛት ውስጥ ብቻ ቢያንስ 912 ሰዎች በአደጋው ሲሞቱ፣ 5ሺህ 383 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ኤርዶዋን ጨምረውም በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥርን ለመገመት አስቸጋሪ መሆኑን በመጥቀስ፣ የፍላጋ ሥራው ተጠናክሮ ሲቀጥል የሰለባዎች ቁጥር ይጨምራል ብለዋል።
በአጎራባች ሶሪያ ውስጥ በርዕደ መሬቱ ሳቢያ የሞቱት ሰዎች አሃዝ 783 መድረሱን የፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) ዘግቧል።
የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ጥናት እንዳለው ጋዚያንቴፕ ከተማ ያጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 7.8 ሆኖ ተመዝግቧል።
ርዕደ ሬቱ በመታቸው አካባቢዎች ያሉ ሕንጻዎች የፈራረሱ ሲሆን፣ በርካታ ሰዎችም በተደረመሱት ሕንጻዎች ውስጥ ተቀብረው መውጣት እንዳልችሉ ተገልጿል።
ይህም በሰዎች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን በትክክል ማወቅ እንዳይቻል አድርጓል ተብሏል።
የመሬት መንቀጥቀጡ ንዝረት በሌሎች የቱርክ ከተሞች እና በአካባቢው ባሉ አገራት ጭምር ተሰምቷል።
ከባድ ጉዳት ካደረሰው የመጀመሪያው የመሬት ነውጥ ከተከሰተ ከሰዓታት በኋላ በርዕደ መሬት መለኪያ 7.5 የሆነ ሌላ አደጋ በደቡብ ምሥራቅ ቱርክ ውስጥ አጋጥሟል።
የዚህኛው ነውጥ ማዕከል የሆነችው ደግሞ ካህራማናማራስ የተባለቸው ከተማ መሆኗን ሪፖርቶች አመለክተዋል።
የቱርክ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሌይሞን ሶይሉ ዛሬ በተከሰተው የመጀመሪያው የመሬት መንቀጥቀጥ 10 ከተሞች ጉዳት አጋጥሟቸዋል ብለዋል።
በሰሜን ምሥራቅ ጋዚያንቴብ ዲያርባኪር በተባለች ከተማ አንድ የገበያ ማዕከል መደርመሱን በስፍራው ያለው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ዘግቧል።
የመሬት መንቀጥቀጡ በሶሪያ፣ በሊባኖስ እና በቆጵሮስ ውስጥ የተሰማ ሲሆን ጉዳትም ማድረሱ እየተዘገበ ነው።
ቱርክ የመሬት መንቀጥቀጥ የመከሰት ዕድሉ ከፍተኛ በሆነ አካባቢ ትገኛለች።
እአአ 1999 ላይ በአገሪቱ ሰሜን ምዕራብ ባጋጠመ የመሬት መንቀጥቀጥ ከ17ሺህ ሰዎች በላይ ሕይወታቸውን አጥተው ነበር።