ለ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ማሽቆልቆል ምክንያቱ እና መፍትሔው ምንድን ነው?

በአማራ ክልል ደራ ወረዳ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱ ያጠናቀቀው ተማሪ ሔኖክ [ስሙ የተቀየረ]፤ ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ድረስ ተጉዞ ነው ለፈተና የተቀመጠው።

ቀደም ባሉት ዓመታት በአገር አቀፉ ፈተና ላይ በተደጋጋሚ ሲያጋጥሙ ነበር የተባሉትን መኮራረጅ እና የፈተና ስርቆት ለመከላከል ያለፈው ዓመት ተፈታኞች በተለየ ሁኔታ ነበር ለፈተና የተቀመጡት።

ተማሪዎች ጥሩ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ዝግጅት አላደረጉም ብሎ የሚያምነው ሔኖክ በተለይ በመጀመሪያው ዙር ያጋጠመው ጉዳይ ተማሪዎች ተረጋግተው እንዳይፈተኑ አድርጓል ይላል።

የትምህርት ሚኒስቴር በቀየሰው አዲስ መንገድ መሠረት ተፈታኞች በአገሪቱ ውስጥ ወዳሉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ገብተው በጥብቅ ቁጥጥር ስር እንዲፈተኑ ተደርገዋል።

“መልካም የሚባል ዝግጅት አልነበረንም። ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመፈተን የመጀመሪያዎቹ በመሆናችን . . . ጫና ነበረው።”

በ2014 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛው ቁጥር ያላቸው ዝቅተኛ ውጤት ማምጣታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

“አስደንጋጭ” የተባለው ውጤት እንደሚያሳየው ለፈተና ከተቀመጡት ከ980 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል 30 ሺህ ገደማ ብቻ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ማግኘት የቻሉት።

ሔኖክ፤ አምና ለፈተና ተቀምጠው ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚያስችል ውጤት ባያመጣም ፈተናውም ሆነ ፈተና የተሰጠበት መንገድ ችግር አለበት ብሎ አያምንም።

እሱ እንደሚለው የትምህርት ጥራት መዳከሙን በመጥቀስ ለውጤቱ ቀውስ አስተዋፅዖ አድርጓል ይላል።

“የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱ የሞተ ነው። በተግባር የተደገፈ አይደለም። ፅንሰ-ሐሳብ ነው የምንማረው። ክፍል ውስጥ ትምህርቱን የተረዳ ውጤት ያመጣል። ይህ ዓይነት የትምህርት ፖሊሲ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም።”

ከ50 በመቶ በታች ያመጡ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ መቀላቀል እንደማይችሉ የትምህርት ሚኒስቴር ቢገልጽም፣ የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም ከግምት በማስገባት በውጤታቸው መሠረት ተጨማሪ ተማሪዎች ሊገቡ እንደሚችሉ አሳውቋል።

የ2014 የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ ዝቅተኛ ውጤት ያመጡበት ምክንያት ምን ይሆን?

የአገሪቱ የትምህርት ሁኔታ

የዓለም ባንክ ባለፈው ሰኔ ባወጣው አንድ መረጃ መሠረት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት 70 በመቶ የሚሆኑ ከ10 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ቀለል ያለ ፅሑፍ የመረዳት አቅማቸው አናሳ ነው።

የዓለም ባንክ እና በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት በትብብር ያስጠኑት ይህ ጥናት እንደሚጠቁመው ይህ ቁጥር ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት 57 በመቶ ነበር።

ዘ ኢኮኖሚስት የተሰኘው መጽሔት ዓለም ባንክን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ኢትዮጵያ ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ ዕድሜያቸው 10 የደረሰ ሕፃናት ቀለል ጽሑፍ አንብበው መረዳት አይችሉም።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናት እና ምርምር ተቋም ያደረገው ጥናትም የሚጠቁመው ይህንኑ ነው።

የተቋሙ ዳይሬክተር በላይ ሃጎስ (ዶ/ር) ለቢቢሲ እንደሚናገሩት በፈረንጆቹ 2021 በተደረገ ጥናት 68 በመቶ የሚሆኑ የሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ‘ዜሮ ሪደርስ’ ናቸው።

ይህም ማለት ሕፃናት የተሰጣቸውን ቀላል የሚባል ጽሑፍ አንብቦ የመረዳት አቅማቸው አልጎለበተም፤ አሊያም ማንበብ አይችሉም።

51 በመቶ የሚሆኑ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ አንብበው መረዳት አይችሉም።

ዳይሬክተሩ እንደሚሉት “የዘንድሮው የፈተና ውጤት የማይጠበቅ አልነበረም”፤ ምክንያቱም ተቋማቸው ባለፉት ዓመታት ያደረጋቸው ጥናቶች ይህ ሊመጣ እንደሚችል አመላካች ነበሩ ይላሉ።

ምሑሩ፤ ተማሪዎች ከክፍል ወደ ክፍል የሚዘዋወሩት ብቃታቸው ተፈትሾ ነው ለማለት ያስቸግራል።

በርካታ ኢትዮጵያውዊያን ምሑራን የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ዘንድሮው ለመጣው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ውጤት ተጠያቂ ነው ብለው ያምናሉ።

የጥናት እና ምርምር ተቋሙ ኃላፊም በዚህ ይስማማሉ። ይህ ውጤት “የትምህርት ሥርዓቱ የወለደው” ነው ይላሉ።

“የትምህርት ሥርዓቱ ልጆች ብቃት እንደሌላቸው እየታወቀ ከክፍል ወደ ክፍል እንዲዛወሩ ይፈቅዳል።”

ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ተማሪዎች ከክፍል ወደ ክፍል ብቃት ሳይኖራቸው እንዲያልፉ ከመደረጋቸውም በላይ ከ4ኛ ክፍል በኋላ ተማሪዎች ክፍል የመድገም ምጣኔያቸው ከ10 በመቶ በታች ነው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ ትምርህርት ሊያጠናቀቁ የተቃረቡ ሕፃናት ማንበብ እንደማይችሉ ዓለም ባንክ ይገልጻል።

ተማሪዎች ብቃት ሳይኖራቸው ከክፍል ወደ ክፍል መሸጋገራቸው “ትክክል አለመሆኑን ደጋግመን በሠራናቸው ጥናቶች ለማሳየት ሞክረናል” የሚሉት ዳይሬክተሩ የትምህርት ሥርዓቱ ለብቃት “ቦታ የለውም” የሚል እምነት አላቸው።

እንደ አንድ ምሳሌ የሚጠቅሱት በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ከ8ኛ እና 10ኛ ክፍል በቀር ሁሉም ተማሪዎች ወደሚቀጥለው ክፍል እንዲሸጋገሩ መደረጉን ነው።

“ተማሪ ወደሚቀጥለው ክፍል የሚዛወረው ብቁ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው። የትምህርት ሥርዓቱ እያነጠረ በብቃት የሚያዘዋውር ሳይሆን በቁጥር ብዛት ሪፖርት እያደረገ የሚጓዝ ነው።”

ምሑሩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት በስፋት መሰጡትን ትክክል ነው ቢሉም “ብቃት ሳይኖረው ወደፊት መጓዝን ግን በፍፁም አልደግፈውም” ይላሉ።

የትምህርት ሥርዓቱ ተማሪዎች ለማብቃት እየሻተ በሌላ በኩል ብቁ ባይሆንም ከክፍል ወደ ክፍል እንዲዘዋወሩ መፍቀዱ የሥርዓቱን መጣረስ [ሲስተም ኢንኮሂረንስ] የሚያሳይ ነው ባይ ናቸው።

“የትምህርት ሥርዓቱ ካልተስተካከለ በቀር ለውጥ ሊመጣ አይችልም። መምህራን አይደሉም መጠየቅ ያለባቸው። መምህራንን እዚህ ውስጥ የከተታቸው የትምህርት ሥርዓቱ ነው።”

ራይዝ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2021 ያሳተመው ጥናት እንደሚጠቁመው ምንም እንኳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ቢደረገም፣ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በፈረንጆቹ ከ2000-2017 ባለው ጊዜ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር ከ7.1 ሚሊዮን ወደ 21 ሚሊዮን ማደጉን ይህ ጥናት ያሳያል።

ጣሰው ወደልሃና (ዶ/ር)፣ ፕሮፌሰር ሪካርዶ ሳባቴስ እና ዳዊት ጥበቡ (ዶ/ር) በትብብር ያሳተሙት ጥናት ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት ደረጃዋን ከፍ ለማድረግ መሥራት አለባት የሚል ምክረ-ሐሳብ አስፍሯል።

ይህ ጥናት አክሎም አዳጊ በሚባሉ ክልሎች እና ገጠራማ ሥፍራዎች ያሉ ሕፃናት ጥራት ያለው ትምህርት እያገኙ እንዳልሆነ እና ይህም በውጤታቸው ላይ እየተንፀባረቀ እንደሆነ ይጠቁማል።

የትምህርት ጥራት ይጎድልባቸዋል በሚባሉ አካባቢዎች ያሉት ዐበይት ችግሮች የመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት እና የተሟላ ትምህርት ቤት አለመኖር መሆናቸውን አክሎ ይገልጻል።

‘የማንቂያ ደወል’

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 96 በመቶ ገደማው አልተሳካላቸውም።

ይህ አሳስቦኛል ያለው የትምህርት ሚኒስቴር ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸውን ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች ደካማ ያስመዘገቡባቸውን የትምህርት ዓይነቶች ለአንድ ዓመት በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንዲማሩ ፈቅዷል።

ከአንድ ዓመት በኋላ የሚሰጣቸውን የመመዘኛ ፈተና የሚያልፉ ከሆነ የአንደኛ ዓመት የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ይጀምራሉ ሲሉ ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ ይህን መግለጫ በሰጡበት ወቅት የተማሪዎች የውጤት ማሽቆልቆል “ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ የበርካታ ችግሮች መገለጫ እና ተሸፍኖ የቆየውን እውነተኛ የትምህርት ሥርዓት ያለበትን ደረጃ ያመለከተ ነው” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የትምህርት ሁኔታ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር በርካታ ጥናቶች ያካሄዱት በላይ ሃጎስ (ዶ/ር) ውጤቱን “አንደ ማንቂያ ደወል” ነው የምናየው ይላሉ።

ምሑሩ፤ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች ተስፋ እንዳይቆርጡ መክረው፣ ነገር ግን የትምህርት ሥርዓቱን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለው ያምናሉ።

“የትምህርት ሥርዓቱ ሲስተካከል ለብዙ ነገሮች መፍትሔ ይዞ ይመጣል። የሥርዓቱ ተልዕኮ በብቃት ዜጋን መገንባት ነው። ይሄ ነበር ወይ ሲሆን የነበረው? የሚለውን ቆም ብሎ ማየት ያስፈልጋል።”

እንደ መፍትሔ ከሚያስቀምጧቸው ነጥቦች አንዱ የመምህራንን የተሻለ ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪዎች ወደ ትምህርት ሥርዓቱ ሊሳቡ ይገባል ሲሉ ያሰምራሉ።

“አንድ ግለሰብ ‘ውጤቴ ዝቅ ብሏል’ ሲል ‘መምህርነት አመልክት’ የሚባልበት ዘመን ላይ ነው ያለነው” ሲሉ የሚወቅሱት በላይ፤ መምህርነት ክብር ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራሉ።

ስለመምህራን ሲነሳ ማበረታቻ እና ተመጣጣኝ ክፍያ ከግምት እንዲገባ የሚመክሩት ተመራማሪው ለመምህራን የሚሰጣቸው ዝቅተኛ ክፍያ አንዱ ለትምህራት ጥራት ተጠያቂ ምክንያት እንደሆነ ያውሳሉ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ምርምር እና ጥናት ተቋም የትምህርት ፍኖተ-ካርታ ባጠናበት ወቅት ካነሳቸው ምክረ-ሐሳቦች መካከል አንደኛው የትምህርት ግብር (Education Tax) እንደሆነ ምሑሩ ይገልጻሉ።

እሳቸው እንደሚያምኑት ማንኛውም ሸቀጥ ላይ የትምህርት ግብር ሊጣል ይገባል፤ ይህ ገቢ የመምህራንን ክፍያ የመሸፈን አቅምም አለው።

“በጥናታችን ወቅት ይህ ግብር ቢተገበር ‘ሕዝቡ አያማርርም ወይ?’ ብለን ጠይቀን ነበር። የመለሱልን መልስ ቤተሰብ የሚያማርረው በሌሎች የግብር ዓይነቶች ነው እንጂ በትምህርት ግብር አያማርርም የሚል ነው።”

ተቋሙ ይህን ጥናት ባስጠናበት ወቅት ስለትምህርት ግብር ከኮሪያ ልምድ እንደቀሰመ የሚጠቅሱት ተመራማሪው ይህ ግብር ቢተገበር ስኬታማ እንደሚሆን እምነት አላቸው።

‘ኢዱኬሽን ታክስ አክት’ በመባል የሚታወቀው የደቡብ ኮሪያ የትምህርት ግብር በፈረንጆቹ ከ1990ዎቹ ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ ሲሆን የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ የሚያስችል ወጪ መሸፈኛ እንዲሆን የታወጀ ነው።

ምሑሩ፤ በአጠቃላይ ትምህርት ላይ የሚፈሰው መዋዕለ-ንዋይ ጥራት ያለው ባለሙያ እንዲመረት የሚያደርግ ስለሆነ ሁሉም ሊረባረብበት ይገባል ይላሉ።

“የችግሩም የመፍትሔውም ወሳኝ አካል መንግሥት ነው። መንግሥት ንቅናቄውን ከላይ ቢያስጀምረው በተዋረድ እስከ ቤተሰብ ድረስ ተከታይ ነው። ሁሉም ሊሳተፍበት ይገባል። ካልሆነ ግን የአንድ ሰሞን ወሬ ብቻ እንዳይሆን ስጋት አለኝ።”