ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“ራሴን ማየት የምፈልገው ናሳ ገብቼ ነው” ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው ሚክያስ አዳነ
ሚክያስ አዳነ በ2014 ዓ.ም. የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በ666 ነጥብ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል።
ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል የተማረው ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው ወገል ጤና ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተከታትሏል።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በደረጃ ተማሪነት ያጠናቀቀው ሚክያስ፣ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ውጤቱን ለመስማት በጉጉት ሲጠባበቅ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።
“ውጤቱን የሰማሁት ቤት ሆኜ፣ ሌሊት ላይ ነው። በጣም ስጠብቅ ነበር። ከቤተሰቦቼ ጋር አብረን እየጠበቅን ነበር። መጀመሪያ እኔ አየሁና ከዚያ ነገርኳቸው። ደስ ብሎኛል።”
ከፍተኛ ውጤት እንደሚያመጣ ቢጠብቅም በአገሪቱ በጠቅላላ ከተፈተኑ ተማሪዎች አንደኛ እሆናለሁ ብሎ ግን አላሰበም ነበር።
መምህር የሆኑት አባቱ አቶ አዳነ እውነቱም በዚህ ከፍተኛ ውጤት የደስታው ተቋዳሽ ናቸው።
ከጦርነቱ እንዲሁም ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የአምናው ብሔራዊ ፈተና መሰናክል የሞላው ነበር። ፈተናው ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርስቲዎች ከመሰጠቱ ጋር በተያያዘና ሌሎችም የአካሄድ ጥያቄዎች ሲነሱም ተደምጧል።
በዚህ ሁሉ ውስብስብ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ፈተና መቀመጥ ለሚክያስ ቀላል አልነበረም።
“ትምህርት የጀመርነው በታኅሣሥ ነበር። የሁለት ሴሚስትር ትምሀርት በአንድ ሴሚስተር ነው የጨረስነው” ሲል ያስታውሳል። ክረምት ላይ ባገኙት ጊዜ ጥናት ማጠናቀቅም ነበረባቸው።
ጦርነቱ ብዙ መስተጓጎል እንደፈጠረ የሚገልጹት አባቱ አቶ አዳነ “ጦርነቱ ባይኖር ከዚህም በላይ ውጤት ይጠበቅ ነበር” ይላሉ።
በሚማርበት የአዳሪ ትምህርት ቤት ሁሉም ተማሪዎች በጋራ ተጋግዘው ያጠኑ እንደነበር የሚናገረው ሚኪያስ “ሁላችንም ጥሩ ውጤት ማምጣት ነበር የምንፈልገው። እዚያው ስለምንኖር ጠዋትም፣ ከሰዓትም፣ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናትም እናጠና ነበር።”
የደሴ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲከፈት የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ [ሚኒስትሪ] ከ85 በመቶ በላይ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎችን ሲወስድ ሚክያስ አንዱ ተማሪ ነበር። 92 ነጥብ አምጥቶ ነበር ትምህርት ቤቱን የተቀላቀለው።
“አዳሪ ትምህርት ቤት የሚገኙት ተማሪዎች እና መምህራን የተሻሉ ስለሆኑ እነሱ ላይ ለመድረስ መፍጠን የግድ ነው” የሚለው ሚክያስ ይህም የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደረዳው ይገልጻል።
ሚክያስ ከሦስት ልጆች መካከል ለቤተሰቡ የበኩር ነው። መዋዕለ ሕጻናት የገባው በሦስት ዓመቱ የነበረ ሲሆን፣ ከሌሎች ተማሪዎች እኩል አንዲራመድ አንዲት መምህርቱ ያደረገችለትን እርዳታ እንደማይረሳው ይናገራል።
አባቱም “መዋዕለ ሕጻናት ጥሩ መምህርት ነበረችው። ስምንተኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ አዳሪ ትምህርት ቤት ገባ። የሚፈልገውን መጽሐፍ አቀርብለት ነበር። በተፈጥሮውም ተረጋግቶ፣ ሳይጨናነቅ ያነበበውን ይይዛል” ይላሉ።
መሠረተ ልማት እምብዛም ባልተሟላለት ደቡብ ወሎ ውስጥ በሚገኝ መንደር ውስጥ ማደጉና መማሩ መሰናክል ሳይሆንበት እንዴት ሰቃይ ተማሪ እንደሆነ ሲጠየቅ “አባቴም መምህር ስለሆነ ከታች ክፍል ጀምሬ ለትምህርት ጥሩ አመለካከት ነበረኝ። ጥሩ እሠራ ነበር። ቤተሰቤም ይደግፈኛል።”
በአካባቢው ለብዙ ጊዜ መብራት እንዳልነበረ፣ እንደ ከተማ ኢንተርኔትም እንደማይገኝ የሚናገሩት አቶ አዳነ፣ ነገሮች አልጋ በአልጋ እንዳልሆኑ ሳይጠቅሱ አያልፉም። ለዚህ ነው በአካባቢያቸው መጽሐፍ የማከፋፈል ኃላፊነትን የወሰዱት።
አብዛኛውን ጊዜ የበይነ መረብ ትምህርቶችን እንደሚከታተል ሚክያስ ይናገራል። በዚህም ቤተሰቡ ያደረገለትን ድጋፍ ይጠቅሳል።
አባቱ እንደሚሉት፣ ሚክያስ ከስድስተኛ ክፍል እስከ ስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ጥሩ ውጤት ላላቸው ተማሪዎች “አስተማሪ በመመደብ ካስተማሩ በኋላ ትልልቅ ሰዎች በመጥራት እንዲመረቁ” ያደርጉ ነበር።
እነዚህ የደገፏቸው 11 ተማሪዎች ጥሩ ውጤት እንዳመጡ መምህሩ ይናገራሉ።
ሚክያስም ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ ለአስትሮኖሚ እና ፊዚክስ ልዩ ፍላጎት እንዳዳበረ ይናገራል። በብሔራዊ ፈተና ውጤቱ ፊዚክስ 100 ነው ያመጣው።
የውጭ አገር የትምህርት ዕድል ካገኘ አስትሮፊዚክስ ማጥናት እንደሚፈልግ ሚክያስ ይናገራል። ከወዲሁም የትምህርት ዕድሎች እያፈላለገ ነው።
“ራሴን ማየት የምፈልገው ስፔስ ኤክስ ወይም ናሳ ገብቼ ነው” ሲል የወደፊት ሕልሙን ለቢቢሲ አጋርቷል።
አባቱ በበኩላቸው፣ ልጃቸው ሚክያስን “ቢሆንልኝ. . .ማየት የምፈልገው ሳይንቲስት ቅጣው እጅጉን ሆኖ ነው። ሕጻን እያለ ‘ዘ ሲክሬት’ የተባለውን ፊልም አሳየው ነበር። እነ ቅጣውንም እያየ ታላላቅ ሰዎችን መሆን ይፈልጋል። የእኔም ፍላጎት ይኸው ነው” ይላሉ።
የ2014 ዓ. ም. የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ከወሰዱት ከ900 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል ከሃምሳ በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ከ30 ሺህ በታች የሚሆኑት ናቸው።
ሚኪያስ ደግሞ ከ700 ከተያዘው አጠቃላይ የፈተናው ውጤት 666 በማምጣት ከዓመቱ ተፈታኞች ከፍተኛውን ውጤት ካስመዘገቡት መካከል አንዱ ለመሆን ችሏል።