ከ800 በላይ የአል ሻባብ ታጣቂዎች መገደላቸውን የሶማሌ ክልል ገለጸ

የአልሸባብ ተዋጊዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በሚዋሰኑባቸው የድንበር አካባቢዎች በኩል ወደ ሶማሌ ክልል ዘልቀው የገቡ ከ800 በላይ የአል ሻባብ ታጣቂዎች መገደላቸውን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቃት በመፈጸም ታሪክ የሌለው አል ሻባብ በቅርቡ የኢትዮጵያን ድእነበር ዘልቆ ከገባ በኋላ ከሶማሌ ልዩ ኃይል ጋር ውጊያ አድርጓል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ሙስጠፌ ኡመር ዛሬው አርብ ሐምሌ 29/2014 ዓ.ም. እንደተናገሩት ከተገደሉት በተጨማሪ ወደ መቶ የሚጠጉ የቡድኑ አባላትም ተይዘዋል ብለዋል።

የታጣቂዎቹ መገደልንም ሆነ መያዝንም በተመለከተ ቢቢሲ ከገለልተኛ አካል አላረጋገጠም።

ጥቃቱ በተከፈተበት ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም. በደረሰው የመጀመሪያ ጥቃት ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አል ሻባብ በርካታ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላትን መግደሉን ተናግሯል።

ሐምሌ 13/2014 ዓ.ም. በተከፈተው በዚህ ጥቃት አል ሻባብ ሁለት ቡድኖችን ያሳተፈ ሲሆን ከሶማሊያ የሚያሻግር አንድ ቡድን እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ የሚገባ ሌላ ቡድኖች እንደነበሩት ታውቋል። 

በመቀጠልም ሁለተኛው ዙር ጥቃት ሰኞ ሐምሌ 18/2014 ዓ.ም. በሶማሊያ ፊር ሸበሌ ክልል በኩል የተከፈተ ሲሆን፣ ይህንን አካባቢ ተከትላ ፌር ፌር የተሰኘችው የኢትዮጵያ የድንበር ከተማ ትገኛለች። ከፌር ፌር አካባቢ ላስቁሩን የተሰኘች ከተማ ላይ ውጊያ ተካሂዷል።

ከፍተኛ ውጊያን ያስተናገደው እና የኢትዮጵያ መንግሥት ከ80 በላይ የአል ሻባብ ታጣቂዎች መገደላቸውን የገለጸው በዚሁ በፌር ፌር በኩል ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአካባቢው በልዩ ኃይል ኃይሎች እና በእስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ አባላት መካከል የተካሄዱ ውጊያዎችን የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንኑ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አምስተኛዋ እና አነስተኛ ውጊያን ያስተናገደችው በሪስማን የተሰኘች ሌላኛዋ ፌርፌር አካባቢ ያለች ቦታ ነች። 

የክልሉ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ጋር በመሆን የጥምር ዘመቻ መጀመሩን አስታውቀው ነበር።

ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ ከገባው ከአል ሻባብ ታጣቂዎች ጋር በተደረገው ውጊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች መገደላቸውን፣ ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን እንዲሁም በርካታ የጦር መሳሪያዎች መማረካቸው ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የአሜሪካ መንግሥት መገኛውን ለጠቆመ 5 ሚሊዮን ዶላር ወሮታ እከፍላለሁ በማለት ሲያፈላልገው የነበረው የአል ሻባብ የቅስቀሳ እና ፕሮፓጋንዳ ኃላፊ ፉአድ መሐመድ ካህላፍን ጨምሮ ሦስት የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች መግደሉን አስታውቋል።

ከፉአድ መሐመድ ካህላፍ በተጨማሪ የቡድኑ ቃል አቀባይ ነው የተባለው አብዱላዚዝ አቡ ሙሳ እና የባኩል ዞን እና የኢትዮጵያ ድንበሮች አዋሳኝ የእስላማዊ ቡድኑ ኃላፊ ኡቤዳ ኑር ኢሴ በአየር ጥቃት በታገዘ ወታደራዊ ዘመቻ መገደላቸው ተገልጿል።

አል ሻባብ በበኩሉ እነዚህ አመራሮች አልተገደሉም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ሙስጠፋ ቀደም ሲል ለክልሉ ምክር ቤት እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በሶማሊያ ውስጥ ክልሉን ከተመሳሳይ ጥቃቶች ለመከላከል የመከላከያ ቀጠና የመገንባት እቅድ እንዳላት አስረድተዋል።

በዛሬው ዕለት ባደረጉት ንግግር ቡድኑ "ወደ ድንበር ለመቅረብ ፈጽሞ እንዳደፍር" ለማረጋገጥ ጥረቶች እየተደረጉ ናቸው ብለዋል ። 

ከጥቃቱ በኋላ ዝርዝሩ ባይገለጽም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች በሶማሊያ ውስጥ ጉብኝት በማድረግ ከባለሥልጣናት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቧል።