በአሜሪካ ድብብቆሽ ስትጫወት የነበረች ታዳጊ ጭንቅላቷን በጥይት ተመታች

ዴቪድ ዶይል

የፎቶው ባለመብት, POLICE

የምስሉ መግለጫ, ዴቪድ ዶይል

አሜሪካ ውስጥ ከቤቱ አቅራቢያ ድብብቆሽ ስትጫወት የነበረችን ታዳጊ በጥይት ተኩሶ የመታው አንድ ግለሰብ ክስ እንደተመሰረተበት ፖሊስ አስታወቀ።

በሉዊያኒያ ግዛት ውስጥ በሚገኝ የገጠር አካባቢ ነዋሪ የሆነችው የ14 ዓመቷ ታዳጊ፣ በግለሰቡ በተተኮሰባት ጥይት ጭንቅላቷን ከኋላ ተመትታ ሆስፒታል የገባች ሲሆን፣ ጉዳቷ ለሕይወት አስጊ እንዳልሆነ ፖሊስ ገልጿል።

ታዳጊዋን በጥይት መትቶ ያቆሰለው የ58 ዓመቱ ዴቪድ ዶይል የተባለው ግለሰብ፣ ከቤቱ ውጪ “የሚንቀሳቀስ የሰው ጥላ በመመልከቱ” ጥይት መተኮሱን ለፖሊስ ተናግሯል።

ታዳጊዋ ላይ በፈጸመው ጥቃትም ከባድ ጉዳት በማድረስ እና አካላዊ ጥቃት በመፈጸም ክስ ተመስርቶበታል።

ይህም አሜሪካ ውስጥ ከሚፈጸሙ የጅምላ የጦር መሳሪያ ጥቃቶች በተጨማሪ፣ በቀላል ምክንያት እና በጥርጣሬ የተፈጸመ ወንጀል እንደሆነ ተነግሯል።

ከሉዊዚያና ግዛት ዋና ከተማ ኒው ኦርሊንስ በስተ ምዕራብ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ስታርከርስ በተባለቸው ከተማ ውስጥ ይህ ጥቃት የተፈጸመው ባለፈው እሁድ ነው።

ጠዋት ላይ የ14 ዓመቷ ታዳጊ ተተኩሶባት ጉዳት እንደደረሰባት ለፖሊስ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ነበር የአካባቢው ፖሊሶች ወደ ቦታው የደረሱት።

ከክስተቱ በኋላ የአካባቢው ፖሊስ ባወጣው መግለጫ፣ የፖሊስ መኮንኖች ከስፍራው ደርሰው እንደተረዱት “በርካታ ታዳጊዎች በአካባቢው ድብብቆሽ ሲጫወቱ እንደነበር እና በጥቃት ፈጻሚው ግለሰብ ይዞታ ውስጥም ተደብቀውም ነበር” ብሏል።

የቤቱ ባለቤት እና ታዳጊዋን ተኩሶ በመምታት የተከሰሰው ግለሰብ፣ ዴቪድ ዶይል “ከቤቱ ውጪ የሰው ጥላ በመመልከቱ፣ ወደ ውስጥ በመግባት ጠመንጃ ይዞ እንደወጣ ተናግሯል” ሲል የፖሊስ መግለጫ ጠቅሷል።

“ከዚያም ወደ ውጪ ሲወጣ ከጊቢው ውስጥ እየተሯሯጡ የሚወጡ ሰዎችን ተመልክቶ መተኮስ መጀመሩን እና ሳያውቀው ታዳጊዋን እንደመታትም ገልጿል።”

ታዳጊዋን በጥይት የመታው ግለሰብ በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ያለ ሲሆን ክስም ተመስርቶበታል።

ባለፈው ሚያዝያ ወር የጦር መሳሪያ በመጠቀም በርካታ ወጣቶች ላይ ጉዳት ያደረሱ ጥቃቶች በአሜሪካ ውስጥ የተፈጸሙ ሲሆን እነሱም፡

  • ኦስቲን አቅራቢያ ቴክሳስ ውስጥ በመኪና ማቆሚ ቦታ ፔተን ዋሽንግተን የተባለች የ18 ዓመት ወጣት በስህተት ወደ አንድ መኪና ለመግባት ስትሞከር ተተኩሶባት በጽኑ ቆስላለች።
  • ኒው ዮርክ ውስጥ የ20 ዓመቷ ካይሊን ጊልስ ጓደኛዋ በተሳሳተ መንገድ ላይ ሲያሽከረክር በተተኮሰባቸው ጥይት ተመትታ ሞታለች።
  • ሚሱሪ ውስጥ የ16 ዓመቱ ራልፍ ያርል በስህተት የአንድ ግለሰብ ቤትን የመጥሪያ ደወል ከደወለ በኋላ ጭንቅላቱን እና ክንዱ ላይ በጥይት ተመትቷል።
  • ሰሜን ካሮሊና ውስጥ ደግሞ የስድስት ዓመት ህጻን ትጫወትበት የነበረው የቅርጫት ኳስ ወደ አንድ ግለሰብ ጊቢ ውስጥ በመግባቱ ህጻኗ እና አባቷ በጥይት ተመትተዋል።