በአሜሪካ ቴክሳስ አንድ ታጣቂ ገበያ አዳራሽ ውስጥ በከፈተው ተኩስ 8 ሰዎችን ገደለ

ፖሊሶች በጥቃቱ ወቅት በገበያ አዳራሹ ውስጥ የነበረ ሰዎችን በሰልፍ ሲያስወጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፖሊሶች በጥቃቱ ወቅት በገበያ አዳራሹ ውስጥ የነበረ ሰዎችን በሰልፍ ሲያስወጡ

በአሜሪካዋ የቴክሳስ ግዛት ውስጥ በምትገኘው አለን ከተማ አንድ ታጣቂ በገበያ አዳራሽ ውስጥ በፈጸመው ጥቃት ስምንት ሰዎችን በጥይት ገደለ።

ታጣቂው በጅምላ ባገኘው ሰው ላይ በከፈተው ተኩስ ግድያውን የፈጸመ ሲሆን፣ በገበያ አዳራሹ ውስጥ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ድጋፍ እንዲወጡ መደረጉን የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

ታጣቂው እዚያው ጥቃቱን በፈጸመበት ስፍራ በፖሊሶች ተተኩሶበት የተገደለ ሲሆን፣ ጥቃቱን የፈጸመው ብቻውን እንደሆነ ታምኗል።

በታጣቂው ከተገደሉት ውስጥ ሕጻናት ይገኙበታል። ከሞቱት በተጨማሪ ሰባት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል ህክምና እየደረገላቸው ሲሆን፣ ከመካከላቸው ሦስቱ በጽኑ የተጎዱ ናቸው።

የአለን ከተማ የእሳት አደጋ መከላከያ ኃላፊ ጆናታን ቦይድ እንደተናገሩት፣ ጥቃት ፈጻሚውን ጨምሮ ሰባት ሰዎች በጥቃቱ ስፍራ መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፣ አንደኛው ሆስፒታል ውስጥ ቆይቶ ነው ሕይወቱ ያለፈው።

የቴክሳስ ግዛት ገዢ ግሬግ አቦት ጥቃቱን “ለመግለጽ የሚከብድ ሰቆቃ” በማለት ያሉት ሲሆን፣ የግዛቱ አስተዳደር የአለን ከተማ ባለሥልጣናትን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

አንዳንድ የዐይን እማኞች ጥቃት ፈጻሚው ታጣቂ ሙሉ ለሙሉ ጥቁር የለበሰ እና ለውጊያ የሚውሉ ቁሶችን የታጠቀ መሆኑን ተናግረዋል።

የአለን ከተማ ከንቲባ ኬን ፎክ ከጥቃቱ በኋላ “ዕለቱ ለከተማችን አሰቃቂ ቀን ነው። በሰላማዊዋ አለን ከተማ የተፈጸመው ይህ ድርጊት በእጅጉ አስደንጋጭ ነው” በማለት በከተማዋ ድረ ገጽ ላይ ጽፈዋል።

“የከተማችን ፖሊሶች እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ለወሰዱት ፈጣን እርምጃ አድናቆቴን መግለጽ እወዳለሁ። የወሰዱት ጠንካራ ሥልጠና በዛሬው ዕለት የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ለማትረፍ እርምጃ ከመውሰድ እንዳያመነቱ አድርጓቸዋል” ብለዋል ከንቲባው።

የአለን ከተማ ከሌላኛዋ የቴክሳስ ከተማ ዳላስ በስተሰሜን 32 ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኝ ሲሆን፣ 105,000 የሚሆኑ ሰዎች የሚኖሩባት ናት።

ከቀናት በፊት እዚያው ቴክሳስ ውስጥ አንድ የዘጠኝ ዓመት ታዳጊን ጨምሮ አምስት ሰዎችን ተኩሶ በመግደል የተከሰሰን ግለሰብ ፖሊስ መያዙ ይታወሳል።

ፍራንሲስኮ ኦሮፔሳ የተባለው ተጠርጣሪ ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ ለአራት ቀናት ተሰውሮ በፖሊስ በጥብቅ ሲፈለግ የቆየ ቢሆንም በመጨረሻ ቁምሳጥን ውስጥ ተደብቆ ተገኝቷል።

በቴክሳስ ግዛት ከዚህ በፊት በጥፋተኝነት አስካልተፈረደባቸው ድረስ ከ21 ዓመት በላይ የሆናቸው አዋቂዎች ምንም አይነት ፈቃድ ሳያስፈልጋቸው ሽጉጥ የመታጠቅ መብት አላቸው። ጠመንጃ ለመታጠቅም ከተወሰኑ ክልከላዎች ውጪ የሚከለክላቸው ነገር የለም።

ባለፉት አራት ወራት ውስጥ በአሜሪካ አራት ወይም ከዚያ በላይ ሰዎች የተገደሉባቸው ወይም የቆሰሉባቸው ቢያንስ 198 የጅምላ የጦር መሳሪያ ጥቃቶች መፈጸማቸውን በጦር መሳሪያ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የሚመዘግበው ተቋም አመልክቷል።

ይህም ከአውሮፓውያኑ 2016 ወዲህ የተከሰተ ከባድ ጉዳት ነው ተብሏል።