በአሜሪካ ቴክሳስ ታጣቂው የ8 ዓመት ሕጻንን ጨምሮ 5 ጎረቤቶቹን ተኩሶ ገደለ

ቴክሳስ ሒውስተን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችና አዳጊዎች በጦር መሣሪያ ይገደላሉ።

በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ውስጥ ከሒውስተን ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ ሰፈር አንድ ታጣቂ አምስት ጎረቤቶቹን ተኩሶ ገድሏል።

ከሟቾቹ መካከልም አንድ የስምንት ዓመት አዳጊ ይገኝበታል።

ነገሩ የተከሰተው ዐርብ እኩለ ሌሊት ላይ ሲሆን፣ ይህ ተጠርጣሪ መሣሪያ አቀባብሎ የተኩስ ልምምድ በማድረግ ሰፈሩን ያውከዋል።

አንድ ጎረቤቱ ወደርሱ ቤት በመሄድ “እባክህን ልጅ እያስተኛን ነው፣ የተኩስ ድምጽ ረበሸን” ይለዋል።

ግለሰቡም ተቆጥቶ “ማንም ሊናገረኝ አይችልም፤ ይህ የእኔ ጊቢ እስከሆነ ድረስ ያሻኝን አደርጋለሁ” ብሎ ይመልሳል።

ጎረቤት አገር ሰላም ብሎ ወደ ቤቱ ከተመለሰ በኋላ ግን ታጣቂው የተኩስ ልምምዱን አልቀጠለም። ይባስ ብሎ ወደ ገረቤቶቹ በማቅናት የተኩስ እሩምታ ከፍቶ አምስት ሰዎችን ገድሏል።

ከሟቾቹ መካከልም ሁለት ሴቶች የሞቱበት ሁኔታ በይበልጥ ልብ የሚሰብር ነው ተብሏል።

ሁለቱ ሴቶች ሁለት ሕጻናትን ከሞት ለመታደግ ሕጻናቱን ደብቀው ላያቸው ላይ በመሆን ልጆቹ አንዳይገደሉ ከገዳዩ ሲከላከሉላቸው ነበር የተገለደሉት።

ይህን ታላቅ ጀብዱ የፈጸሙት ሁለቱ ሴቶች በታጣቂው የተገደሉ ሲሆን፣ ከለላ የሰጧቸው ሕጻናት ግን ተርፈዋል።

ጥቃት ፈጻሚው ግለሰብ በማምለጡ በፖሊስ እየተፈለገ ነው።

የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ ክሬግ ኬፐርስ ግለሰቡን ያለበትን የሚያውቅ ለፖሊስ እንዲያሳውቅ አደራ ብለዋል።

ተጠርጣሪው ፈራንሲስኮ ኦሮፔዝ የሚባል ሲሆን የ38 ዓመት ሜክሲኳዊ ነው።

ሟቾቹ ደግሞ ሁሉም የሆንዱራስ ዜጎች ናቸው።

ተጠርጣሪው ለጊዜው ወደ አካባቢው ጫካ እንደሸሸ ተጠርጥሯል።

ፖሊስ በሰለጠኑ ውሻዎች እና በሰው አልባ አነስተኛ አውሮፕላን (ድሮን) ጭምር በመታገዝ ግለሰቡ የገባበት ገብቶ ለመያዝ ከፍተኛ ዘመቻ ላይ ይገኛል።

“ልጅ እያስተኛን ነው እባክህን ድምጽ ቀንስ” የተባለው ተጠርጣሪ ኦሮፔዝ በውድቅ ሌሊት ተኩስ በሚለማመድበት ወቅት መጠጥ እየጠጣ እንደነበረም የአካባቢው ፖሊስ አዛዥ ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

አምስቱ ጎረቤቶቹ በብዛት ጭንቅላታቸው አካባቢ ተተኩሶባቸው ወዲያውኑ ነው የሞቱት።

የስምንት ዓመቱ ታዳጊ ግን ሆስፒታል ደርሶ ነው ሕይወቱ ያለው።

ተጠርጣሪው ጎረቤቶቹን ለመጨረስ የተጠቀመው ኤአር-15 መለስተኛ አውቶማቲክ ጠመንጃ ነው።

የተጠርጣሪው ጎረቤት ቬሮኒካ ፒኔዳ ስለ ክስተቱ ለጋዜጠኞች ስትናገር፣ ተኩስ መስማቷን ገልጻ ነገር ግን በዚያ ሰፈር ተኩስ መስማት ምንም ብርቅ ነገር አይደለም፤ እንደሁልጊዜው መስሎኝ ነው ቤት የተቀመጥኩት ብላለች።

“በእኛ ሰፈር ሁልጊዜም ተኩስ አለ፤ ሁልጊዜም ፖሊስ ይደወልለታል፤ ሁልጊዜም መራበሽ ነው” ብላለች።

ይህ አሳዛኝ ዜና ከአሜሪካ የተሰማው በዚያው ግዛት ቴክሳስ ከጥቂት ቀናት በፊት በአንድ የልጅ ልደት ድግስ ላይ ዘጠኝ ሰዎች ተተኩሶባቸው መቁሰላቸውን ተከትሎ ነው።

ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ በዚያው በደቡባዊ አሜሪካ፣ አላባማ ግዛት በልደት ቀን አራት ሰዎች ተተኩሶባቸው መሞታቸው ተዘግቦ ነበር።

በአሜሪካ የጦር መሣሪያ መታጠቅ እና አጠቃቀም ዙርያ ሰፊ የፖለቲካ ልዩነቶች ይስተጋባሉ። ዲሞክራቶች የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ይደረግ ሲሉ ሪፐብሊካኖች ይህ በፍጹም ለድርድር የማይቀርብ የሁሉም አሜሪካዊ መብት ነው ይላሉ።

በአሜሪካ በዓመት በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች እና ታዳጊዎች በጦር መሣሪያ ይገደላሉ።