የፕሬዝዳንት ኬኔዲን ግድያ የተመለከተ የምርመራ ዶሴ ከ60 ዓመት በኋላ ይፋ ሆነ

ዋይት ሐውስ ጆን ኤፍ ኬኔዲን የተመለከተው ዶሴ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ወሰነ።

ይህ ዶሴ ለሕዝብ ይፋ እየሆነ ያለው ከ60 ዓመታት ጥብቅ ምሥጢርነት በኋላ ነው።

ብዛቱ ከ10ሺህ በላይ ይሆናል የተባለው ይህ ሰነድ ይፋ እንዲሆን የወሰኑት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ናቸው።

ይሁንና አንዳንድ ሰነዶች አሁንም በምሥጢር የሚቆዩ ይኖራሉ። ይህም ለአንዳንድ ሰዎች ደኀንነት ሲባል ነው ተብሏል።

ምንም እንኳ የጆን ኤፍ ኬኔዲ ግድያ ለዐሥርታት እያወዛገበ ቢቆይም በዚህ ሰነድ የሚገለጥ አንዳች ታላቅ ምሥጢር ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም።

ዶሴው በፕሬዝዳንቱ ግድያ ዙርያ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ግን ልዩ ዕድል ነው ተብሏል። 

የቀድሞው ዝነኛና ተወዳጁ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በቴክሳስ ግዛት፣ ዳላስ ከተማ፣ በክፍት መኪና ከባለቤታቸው ጋር በጉብኝት ሳሉ ነበር እአአ በኅዳር 22፣ 1963 በተተኮሰባቸው ጥይት የተገደሉት።

ከዚያች ቅጽበት ጀምሮ ሰውየውን ማን ገደላቸው? ለምን ተገደሉ? በሚለው ዙርያ ሺህ ምርመራዎች ተደርገዋል።

እነዚህ የምርመራ ሂደቱን የያዙ ዶሴዎችም በምሥጢር ሲከማቹ ነው የኖሩት።

የ1992 የአሜሪካ ሕግ ዶሴዎቹ በጥቅምት 2017 ለሕዝብ ይፋ እንዲደረጉ አስገዳጅ አድርጎ ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ለይስሙላ ያህል የተወሰኑ ሰነዶችን ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን አዘውም ነበር።

ትናንት ሐሙስ ግን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልዩ ትዕዛዝ በመስጠት 97 ከመቶ የሚሆኑትን ሰነዶች ይፋ እንዲሆን አዘዋል።

ጨምረውም አንዳንድ ጉዳቶችን ለመቀነስ ስንል አንዳንድ የሰነዱ ክፍሎች በሰኔ 2023 ይፋ እንዲሆኑ ብለናል ብለዋል።

የአሜሪካ ብሔራዊ ቤተ መዛግብት ለሕዝብ ይፋ የማይደረጉት ሰነዶች ብዛት 515 ነው ብሏል።

ከጠቅላላው ሰነድ 2ሺህ 545 ሰነዶች ደግሞ ይፋ የሚሆኑት በከፊል እንደሆነ አስታውቋል።

የ1964 የእውነት አፈላላጊው ‘ዋረን ኮሚሽን’ ፕሬዝዳንት ኬኔዲ የተገደሉት ሊ ሐርቬይ ኦስዋልድ በተባለ ግለሰብ ነው ብሎ ነበር።

ሊ ሐርቬይ ቀደም ሲል በሶቭየት ኅብረት ለአጭር ጊዜ የኖረ አሜሪካዊ ሲሆን ድርጊቱን የፈጸመውም በግሉ ነው ተብሎ ነበር።

በቁጥጥር ሥር በዋለ በሁለተኛው ቀን ግን ብዙም ግልጽ ባልሆነ መንገድ በዳላስ ፖሊስ ምድር ቤት ውስጥ ተገድሏል።

ይሁንና የኬኔዲ አገዳደል፣ ገዳያቸው ነበር የተባለው ሰው በፖሊስ ምድር ቤት መገደል ምሥጢርና ተያያዥ ጉዳዮች ለዐሥርታት ለብዙ መላምቶች ክፍት ሆኖ ቆይቷል። 

የሴራ ፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ ግድያውንና ግድያውን ተከትሎ የሆነውን ነገር ሁሉ የትየለሌ ትርጉም ሲሰጡት ኖረዋል።

አንዳንዶች ወጣቱን ፕሬዝዳንት ኬኔዲን የገደላቸው ሴአይኤ ራሱ ነው፤ ለዚያም ነው ገዳያቸው ነው የተባለውን ሰው ፈጥነው የገደሉት ብለው ያምናሉ።

ሲአይኤ ግን የኔ እጅ የለበትም ይላል። 

ገዳያቸው ነው የተባለው ኦስዋልድ በሜክሲኮ አገር ከኬጂቢ ሰላይ ጋር ተገናኝቶ እንደነበር ወደ በኋላ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። 

የመጀመርያው የሮማን ካቶሊክ እምነት ተከታይ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ በጊዜያቸው ገናና የነበሩ 35ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸውም ባሻገር በንግግር አዋቂነታቸው ይደነቃሉ። 

ከንግግራቸው አንዳንዶቹ ዛሬም ድረስ እንደ ጥቅስ ይወሳሉ፤ ከነዚህም መሀል ‘አገሬ ለኔ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ለአገሬ ምን አደረኩላት ብለን እንጠይቅ’ የሚለው የበዓለ ሲመት ንግግራቸው በይበልጥ ይታወሳል።