ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ባይደን በመሪዎች ስብሰባ ላይ አሜሪካ ለአፍሪካ የቢሊዮን ዶላሮችን ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቁ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዩኤስ-አፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ለአህጉሪቱ በድጋፍ እና በኢንቨስትመንት መልክ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አገራቸው ፈሰስ እንደምታደርግ አስታውቁ።
ባይደን አሜሪካ ለአፍሪካ የወደፊት ተስፋ ሙሉ ትኩረቷን እንደምትሰጥ በመሪዎች ውይይት ላይ ለመሳተፍ ዋሽንግተን ለተገኙ የ49 አገራት መሪዎች ተናግረዋል።
አሜሪካ መሰል የመሪዎች ውይይትን ስታካሂድ ይህ በስምንት ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው ነው።
አሜሪካ ይህን ስብሰባ የጠራችው በአፍሪካ እያደገ ለመጣው የቻይና ተጽእኖ መልስ ለመስጠት ያለመ ተደርጎ ተወስዷል።
ከዚህ በተጨማሪ ዶናልድ ትራምፕ በአራት ዓመታት የሥልጣን ዘመናቸው አፍሪካውያን መሪዎችን ገሸሽ ከማድረግ አልፈው፣ አፍሪካውያን አገራትን በማንቋሸሽ በመጥራት የአሜሪካ እና አፍሪካ ግንኙነት አሻክረዋል።
ጆ ባይደን ግን ከዚህ በተለየ መልኩ አገራቸው ከአፍሪካ አህጉር ጋር የበለጠ ቅርብ እንድትሆን ፍላጎታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ለተሰበሰቡት የአፍሪካ መሪዎች “አፍሪካ ስኬታማ ስትሆን፤ ዩናይትድ ስቴትስም ስኬታማ ትሆናለች። እውነት ለመናገር፤ መላው ዓለም ጭምር ስኬታማ ይሆናል” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ዓለም በአሁኑ ወቅት ከገባችበት ቀውስ ለመውጣት የአፍሪካ መሪዎች የመሪነት ጥበብ እና ሃሳብን ትፈልጋለች ብለዋል።
የፕሬዝዳንቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጃክ ሰሊቫን አሜሪካ በቀጣይ ሦስት ዓመታት በድጋፍ እና በኢንቨስትመንት 55 ቢሊዮን ዶላር በአፍሪካ ፈሰስ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ረቡዕ ዕለት ሲናገሩ በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ቤኒን የትራንስፖርት ወጪን ለመቀነስ 500 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ታደርጋለች ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በአህጉሪቱ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማሳደግ 350 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።
አሜሪካ ከአፍሪካ አገራት ጋር በዓለም ትልቅ የሆነውን የአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጠና ለመፍጠር የመግባቢያ ሰነድ እንደምትፈራረም ጨምረው ተናግራል።
ከዚህ ስብሰባ ጎን ለጎን ባይደን በእአአ 2023 ምርጫ ከሚያካሂዱ ስድስት የአፍሪካ አገራት መሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከመሪዎቹ ጋር ውይይት ያደረጉት የሚካሄዱት ምርጫዎች ነጻ እና ፍትሐዊ እንዲሆኑ ጫና ለመፍጠር ነው ተብሏል።
ባይደን በእአአ 2023 ላይ ወደ አፍሪካ ለሥራ ጉብኝት ሊጓዙ እንደሚችሉ ይፋ ሊያደርጉ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ የአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ ለሦስተ ቀናት ተካሂዶ ዛሬ ሐሙስ ታኅሣሥ 06/2015 ዓ.ም. ይጠናቀቃል።