ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ከተከሰተው ሁከት ጋር በተያያዘ የባልደራስ አባላት፣ መምህራንና ተማሪዎች መታሰራቸው ተነገረ
ከሰሞኑ በአዲስአበባ ትምህርት ቤቶች ከተከሰተው ሁከት ጋር በተያያዘ የተወሰኑ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አባላት፣ አንዳንድ ተማሪዎች እና መምህራን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ከኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ አላማ እና መዝሙር ጋር በተያያዘ ተቀሰቀሰ ባለው ሁከት “በጥፋት ድርጊቱ ቀጥተኛ ተሳትፎ” እንደነበራቸው በማስረጃ ማረጋገጡን የአዲስ አበባ ፖሊስ ታኅሣሥ 04/2015 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ቀደም ሲልም በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁከት ለመፍጠር ሞክረዋል ያላቸውን 72 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ማስታወቁ ተዘግቧል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት አብዛኛዎቹ ከትምህርት ቤት ማኅበረሰብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው መሆናቸውንም የቢሮው ኃላፊ ሊዲያ ግርማ ታኅሣሥ 03/2015 ዓ.ም ለብሔራዊው ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) ተናግረዋል።
ግለሰቦቹ የተለየ አጀንዳ ያለቸው እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ ሁከት እንዲፈጠር ሲሰሩ በተጨባጭ መረጃ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ኃላፊዋ ተናግረዋል።
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የተከሰተው “እነዚህን ተቋማት የረብሻ እና የጥፋት ብሎም የውድመት መድረክ ለማድረግ የታቀደ ነው” ብሏል የአዲስ አበባ ፖሊስ።
በተጨማሪም ከትምህርት ቤት ውጪ ሆነው ችግሩን ሲያቀጣጥሉ የነበሩ ግለሰቦች ወደ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ሰብረው ገብተዋል ብሏል።
ስሙ ባልተጠቀሰው በዚህ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ውድመት መድረሱን እና የጥፋት አጀንዳ ተቀብለዋል ያላቸውን እነዚህ ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ገልጾ ጉዳያቸውም እየተጣራ እንደሆነም ገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ የተለያዩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በተደጋጋሚ ከኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እና መዝሙር ጋር ተያይዞ ሁከቶች ተነስተው የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ታኅሣሥ 04/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በዚህም በትምህርት ቤቶች ሰላም ማጣት፣ የአካል ጉዳትና ንብረት ውድመት እንዲሁም ሌሎችም ጉዳቶች ደርሷል ብሏል ኢሰመጉ።
ኢሰመጉ ታኅሣሥ 03/2015 ዓ.ም. በእንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት ዳግም በተነሳው ሁከት ተማሪዎች እና መምህራን ላይ ጉዳት መድረሱንና በጊዜያዊነት ፖሊሶችን ወደ ግቢው በማስገባት ችግሩን መቆጣጠራቸው ገልጿል።
በዚሁ ዕለት በወንድይራድ ትምህር ቤት በተነሳው ሁከት በተማሪዎች እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም በኮልፌ ቀራኒዮ በሚገኙት አየር ጤና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ሚሊኒየም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በተነሱ ሁከቶች በተማሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ኢሰመጉ ካሰባሰብኳቸው መረጃዎች ተደረድቻለሁ ብሏል።
በየካ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ከፍተኛ 12 ደረጃ ትምህርት ቤት ኅዳር 26 ከፍተኛ ሁከት ተነስቶ በአካባቢው የተኩስ ድምጽም ነበር ብሏል። በዚህም ሁከት ከአስር በላይ ተማሪዎች እና አንድ አስተማሪ ተጎድተው ሆስፒታል መግባታቸውን ማወቁን አስፍሯል፡፡
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስር በሚገኘው ጠመንጃ ያዥ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በኅዳር 29 እና 30 በተነሱ ዳግም ሁከቶች በርካታ ተማሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙን፣ የትምህርት ቤቱ ንብረቶች መውደማቸውን እንዲሁም በአንድ የፖሊስ አባል ላይ ድብደባ መፈጸሙን እና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቁጥራቸው ያልታወቁ ተማሪዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች መታሰራቸውንም ኢሰመጉ በዚሁ መግለጫው አስፍሯል።
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በለሚ ኩራ፣ በየካ፣ በቂርቆስ እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ የተወሰኑ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እና መዝሙር ጋር ተያይዘው የተነሱ አለመግባባቶች በዘንድሮውም ዓመት መቀጠላቸውን ገልጿል።
በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የቋንቋ ትምህርት ላይ አለመግባባት እንደሌለ ነገር ግን ዋነኛ አለመግባባቶች የተፈጠረው በሰንደቅ አላማ እና የመዝሙር ጉዳይ መሆኑም ተገልጿል።
“በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚነሱ ሁከቶች መንግሥት በቂ ትኩረት በመስጠት ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት አስቸኳይ ዘላቂ መፍትሔ ይስጥ” ሲልም አሳስቧል።
በትናንትናውም ዕለት ታኅሣሥ 04/2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላም መቀጠሉን ፖሊስ አስታውቋል።
“በሕጋዊ ሽፋን የሕብረተሰቡን ሰላምና ደኅንንት በሚያውኩ ልዩ ልዩ ሕገወጥ ተግባር ላይ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቡድኖችና ግለሰቦች ከአጥፊ ድርጊታቸው ይታቀቡ” ሲልም አሳሳስቧል።
ፖሊስ የከተማዋን ሰላም ለማደፍረስ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የጀመረውን እርምጃ አጠናከሮ እንደሚቀጥልም ገልጿል።
መንግሥታዊው የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በበኩሉ የትምህርት ተቋማት ከማንኛውም ዓይነት የሃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት እና ባህላዊ ተፅእኖዎች ነጻ እንደሆኑ በሕግ ተደንግጓል ብሏል።
በዚህም ሁኔታ “የአማራን/ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችን/ የሲዳማን ወይም የሌላ ክልልን ባንዲራ በትምህርት ቤት ማውለብለብ እና ክልላዊ መዝሙር እንዲዘመር ማስገደድ የሕግም ሆነ የሞራል መሠረት አለው ብሎ ተቋማችን አያምንም ብሏል።
አክሎም “የሌላ ክልል ሰንደቅ አላማ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ግቢ ይሰቀል የሚባልበት በቂ ምክንያት የሚኖር ከሆነም የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ፍቃድና ይሁንታ ማግኘት ይገባዋል” በማለት በመግለጫው አስፍሯል።
ይህንን ክስተት በተመለከተ የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫዎችን ያወጡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እንዲዘመር እና ባንዲራ እንዲውለበለብ የሚደረገው ተግባር ሕገወጥ ነው በማለት እንዲቆም በተከታታይ ባወጣቸው መግለጫዎች ጠይቋል።
ኢዜማ ይህ ተግባር በአፋጣኝ እንዲቆም የሚጠይቅ ደብዳቤ ለተለያዩ እና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ተቋማት ማስገባቱን አመልክቶ፣ ይህ ሁኔታ የማይገታ ከሆነ ጉዳዩን ወደ ሕግ እንደሚወስድ አሳውቋል።
በተመሳሳይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች እየታየ ያለው የኦሮሚያ ክልል ባንዲራን የመስቀልና የክልሉ መዝሙር እንዲዘመር እየተደረገ ያለው ሁኔታ እንዲቆም ጠይቋል።
አብን የፌደሬሽን ምክር ቤት እና የከተማዋ ምክር ቤት ለዚሁ ጉዳይ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ከተማዋን የግጭት እና የብጥብጥ ማዕከል ያደርጋታል ብሏል።
ፓርቲው ጨምሮም ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ለእስር የተዳረጉ ሰዎች እንዲለቀቁ ጠይቋል።