ከጀርመኑ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጀርባ ያለው ግለሰብ እና ቡድን ማነው?

ቱሪንጋ የሚባለው የምሥራቅ ጀርመን ቀጠና ውስጥ ነው የሚኖሩት።

እስከ ዛሬ እምብዛም ያልተወራለት ቡድን ነው። ባለፈው ሳምንት በጀርመን ከተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ጋር ተያይዞ ግን ስማቸው ይነሳ ጀምሯል።

የጀርመንን ምክር ቤት ተቆጣጥረው የዘመናዊ ጀርመን ሥርዓተ መንግሥትን በንጉሣውያን አስተዳደር ለመቀየር ነበር የወጠኑት።

የውጥኑ መሪ ቤተሰቦች አካባቢውን ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት መርተዋል።

መሪው አሁን ዘብጥያ ወርዷል። ሆኖም ግን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የጀርመን ፖሊሶችን አስደንብሯል።

ከጀርመን አልፈው በኦስትሪያ እና በጣልያን ጭምር ፍተሻ እያደረጉ ይገኛሉ።

ለፍተሻው 3 ሺህ ፖሊሶች ናቸው የተሰማሩት። 150 ቦታዎችን አስሰው እስካሁን 25 ሰዎችን አስረዋል። ምርመራው ስለሚቀጥል ተጨማሪ ሰዎች እንደሚታሰሩም የደኅንነት ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የጀርመን የፌደራል እና የክልል ምክር ቤቶች ጥበቃ ተጠናክሯል።

ቢቢሲ በቱሪንጋ የጎበኘው ሹሎስ ዋልድማንሺል የተባለ መዝናኛ ነው። መዝናኛውን የሚያዘወትሩ ሰዎች ከሕዝብ ዕይታ የራቁ እንደሆኑ የቱሪንጋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ሊመሠርቱ ላሰቡት አዲስ የጀርመን መንግሥት፣ ሚኒስትሮች እስከ መሾም እና ወታደራዊ ክንፍ እስከማዋቀር ደርሰዋል።

ቡድኑን የሚመራው ልዑል ቤተሰቦች የሚኖሩት ኦስትሪያ ነው።

“በሰማነው ነገር ደንግጠናል። ሐሳቡ የተጠነሰሰው ከዓመታት በፊት ነው። ፀረ ሴማዊ አካሄድ ያለው የሴራ ትንታኔ ገፍቶት ነው ይህን የፈጸመው። የእኛን ቤተሰብ አይወክልም” ሲል ቤተሰቡ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል።

ልዑሉ ሄንሪሽ 13ኛ ይባላል። ሬሲንግ ሄንሪሽ በሚል ቅጽል ስም ይጠራል። ሄንሪሽ በተባለው የቤተሰብ ስም የሚጠሩ 30 ሰዎች በሕይወት አሉ።

‘ሬሲንግ’ የሚለው ስም ለሄንሪሽ የተሰጠው ለፈጣን መኪኖች ባለው ፍቅር እንደሆነ ቤተሰቦቹ ይናገራሉ።

ቢቢሲ የጎበኘው መዝናኛ ለ100 ዓመታት የቤተሰቡ ንብረት ሆኖ ቆይቷል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ግን በምሥራቅ ጀርመን ኮምኒስት መንግሥት ተወርሷል።

ሄንሪሽ በዓመታት ውስጥ ቁጡ ሰው እየሆነ መምጣቱን ቤተሰቦቹ ይናገራሉ።

ልጁ በጠና ታማለች። የሪል ስቴት ንግዱም ስኬታማ አልሆነም። የቀድሞ ንብረቶችን ከጀርመን መንግሥት ለማስመለስ ያደረገው ጥረት በፍርድ ቤት አወንታዊ ብይን አልተሰጠውም።

በሕይወቱ ለደረሱበት ምስቅልቅሎች የጀርመን መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋል።

ፉርስት የተባለው ቤተሰቡ ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ በምሥራቅ ጀርመን የሚገኘውን መዝናኛ መልሶ ከገዛ በኋላ “ከአልባሌ ሰዎች ጋር መዋል አብዝቷል።”

ልዑሉ 71 ዓመቱ ነው። ወጣት ሩሲያዊት ሴት ጓደኛ አለችው። ሴት ጓደኛው ለመፈንቅለ መንግሥቱ ከክሬምሊን ድጋፍ ለማግኘት ሞክራ ነበር።

ስብስቡ ውስጥ የቀድሞ የጀርመን ልዩ ኃይል አባል፣ የቀድሞ የፖሊስ አመራር፣ የቀድሞ ዳኛ እና በቀኝ ዘመም ፓርቲ የቀድሞ የምክር ቤት አባል አሉበት።

ብሪጅት ማልሳክ-ዊንክማን የፍትሕ ሚኒስትር ይሆናሉ ተብሎ ነበር። የመፈንቅለ መንግሥቱ ቀን የተቆረጠው ሥነ ፈለክን ተከትሎ እንደሆነ የፖሊስ ምርመራ አጋልጧል።

ከገና በዓል በፊት በተወጠነው መፈንቅለ መንግሥት “ሊሞቱ የሚችሉ ሰዎች” እንዳሉ ቡድኑ መምከሩም ታውቋል።

ለጀርመን ደኅንነት አስደናቂ የሆነው ይህ ቡድን ያዋቀረው ወታደራዊ ክንፍ ነው።

ሩጀር ቮን ፒ በተባለ ግለሰብ ነው የሚመራው። ቡድኑ የአገሪቱን ምክር ቤቱን ጥሶ እንዲገባና ፖሊሶችን እንዲከላከል ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

የቀድሞ ሉተነንት ኮሎኔሉ ሩጀር በሥራ ላይ ሳለ መሣሪያ ያከማች እንደነበር ፖሊሶች ያምናሉ።

አንድሬስ ኤም የተባለ የልዩ ኃይል አመራር እና ማክሲሚላን ኤደር የተባለ ኮሎኔል በሥሩ ይገኛሉ። በሴራ ትንታኔ የሚታወቀው ማይክል ኤፍ እና አፍቃሪ-ናዚው ፒተር ደብሊውም አሉበት።

ፖሊስ ከፈተሻቸው ቤቶች በ50ው መሣሪያ አግኝቷል።

የቀኝ ዘመም ዘረኝነት ላይ ጥናት የሠሩት ኒኮላስ ፖተር ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ የዚህ ቡድን ጽንፈኛ ሐሳብ ምን ያህል ደጋፊዎች እንዳሉት በትክክል አለመታወቁ አስጊ ነው።

በጀርመን ልዩ ኃይል ውስጥ የሚገኝ ኬኤስኬ የተባለ ክፍል ቀኝ ዘመም አስተሳሰብ በማንጸባረቁ እንዲበተን መደረጉን ጠቅሰው “መሣሪያ እየተመዘበረ በቀኝ ዘመሞች እጅ ሲገባ እናያለን። ይህ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ትንሹ ስጋታችን ነው። ችግሩ ከዚህም እንደሚብስ እጠረጥራለሁ። በጣም አስጊ ነው” ይላሉ።

በመፈንቅለ መንግሥቱ ከተሳተፉ መካከል ሪችስቡርገር የተባለ ቡድን አባላት ይገኙበታል። እነዚህ ወደ 21 ሺህ ገደማ የሚሆኑት የቡድኑ አባላት ለጀርመን ፌደራል መንግሥት ዕውቅና አይሰጡም።

ግብር አይከፍሉም። በጀርመን ዳኞች የተላለፈ ውሳኔን አይቀበሉም። የጀርመን የተሽከርካሪ የሰሌዳ ቁጥርም አይጠቀሙም።

ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ ትክክለኛው የጀርመን አስተዳደር እንደፈረሰ ነው የሚያምኑት።

እአአ በ2016 ከዚህ ቡድን አባላት የአንዱ ቤት ሲፈተሽ የቤቱ ባለቤት ፖሊሶች ላይ ተኩሶ አንድ ፖሊስ ገድሏል።

ይህ ጽንፈኛ ቡድን አስጊነቱ እየጨመረ እንደመጣ የሚገልጸው የጀርመን ፖሊስ፣ ከመካከላቸው ወደ ነውጥ ሊገቡ የሚችሉ ግን በቁጥር ውስን እንደሆኑ ያስረዳል።

ልዑል ሄንሪሽ ከዚህ ቀደም በበተነው በራሪ ወረቀት የጀርመን ፌደራል መንግሥት መታወቂያ ያላቸው ሰዎች ‘ትክክለኛ ጀርመናዊ’ እንዳልሆኑ ተናግሮ ነበር።

በራሪ ወረቀቱን በበተነበት አካባቢ የሚኖሩ አዛውንት “ጤነኛ አይመስለኝም። በራሪ ወረቀቱ ላይ በቀድሞው የጀርመን አርማ ቀይ፣ ጥቁርና ነጭ የተሠራ መታወቂያ የምናገኝበት ድረ ገጽ ተጽፏል። አነስተኛ ግዛት ለመፍጠር ድምጽ እንድንሰጥም ይጠይቃል። በራሪ ወረቀቱን ቀዳድጄ ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ከተትኩት” ብለዋል።

ልዑሉን የሚነቅፉት ሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች አይደሉም። ሐሳቡን የሚደግፉም አሉ።

“ጀርመን አሁን ባለችበት ሁኔታ ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች ይደግፉታል። ያሳዝናል። ሌላ ዓይነት ጀርመን ማየት ነው የሚፈልጉት” ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

በአገሪቱ ሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ ጥናት የሚሠራው ጆሴፍ ሆልንበርገር እንደሚለው፣ 20 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች ለሴራ ትንታኔ ተጋላጭ ናቸው።

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ ከምጣኔ ሀብት መሽመድመድ እና ከኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ጋር በተያያዘ መንግሥታቸውን ይወቅሳሉ።

የደኅንነት ኃላፊው ስቴፈን ክሬመር “አክራሪዎች እንደ ኮሮናቫይረስ ባለ ወረርሽ ወቅት ይበረታታሉ። ከወረርሽኙ ጋር የተያያዙ የተቃውሞ ሰልፎች መበራከታቸው ቀኝ አክራሪዎችን አደፋፍሯል” ይላሉ።

እነዚህ ቡድኖች የጀርመን ፌደራል መንግሥት የመጣል ዒላማ አስተሳስሯቸዋል። ከመካከላቸው የፌደራል መንግሥቱን ዕውቅና የማይሰጡና፣ ዕውቅና ቢሰጡም ነቅለው መጣል የሚፈልጉ እንዳሉ የደኅንነት ኃላፊው ያስረዳሉ።

ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የተጣሉ ክልከላዎችን በመቃወም ከተካሄዱ ሰልፎች በአንዱ 40 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበት የበርሊን ተቃውሞ ይጠቀሳል። በወቅቱም ምክር ቤቱን ጥሰው ለመግባት ውስን እንቅስቃሴም አድርገው ነበር።

እነዚህ ግለሰቦች የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አድናቂ ናቸው።

ሁለቱም መሪዎችም ‘ወግ አጥባቂና ክርስቲያናዊ’ አስተዳደር ተምሳሌት አድርገው ነው የሚመለከቷቸው።

‘ኪውአኖን’ የተባለው የሴራ ትንታኔ ቡድን መነሻውን ያደረገው አሜሪካ ሲሆን፣ ለትራምፕ ጽኑ ፍቅር አለው። ከእንግሊዝኛ ተናጋሪ አገራት ውጭ ኪውአኖን ከፍተኛ ድጋፍ ያለው በጀርመን ነው።

ክትባት የሚያጣጥሉ፣ አፍቃሪ-ናዚ ተከታዮች አሉት።

የጀርመን አስተዳደር ባለበት እንዲቀጥል የሚፈልጉ አመራሮች የግድያ ዛቻ ሲደርስባቸው እንደሚስተዋል ቢቢሲ ተረድቷል።

የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች ተንታኙ ኒኮላስ ፖተር እና የፀረ ፋሺዝም አቀንቃኟ ማርቲና ሬነር በተደጋጋሚ ዛቻ ከሚሰነዘርባቸው መካከል ይጠቀሳሉ።

ቡድኑ ግድያን ጨምሮ አካላዊ ጥቃቶችም ያደርሳል። እንደ ማንኛውም ሰው ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ስለሚሳተፉ ቀኝ አክራሪዎችን በቀላሉ የደኅንነት አባላት መለየት እንደሚቸገሩ ይናገራሉ።

ቀኝ አክራሪዎች የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ‘የተናጠል’ እርምጃ እንደሆኑ እንደሚነገር የሚገልጸው ተንታኙ ኒኮላስ ፖተር፣ ስጋቱ ሥር እየሰደደ እንደመጣና የጀርመን አንዱ ገጽታ እንደሆነ እንዲታወቅ ያሳስባል።

የደኅንነት ኃላፊው ስቴፈን ክራመር “እጅግ የከፋ ነገር ይመጣል ብዬ ብሰጋም በጎ ነገር ይመጣል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ” ይላሉ።