ኦባማዎችን ዝንጀሮ አድርጎ የሚያሳየውን የትራምፕ ቪድዮ በተመለከተ ባራክ ኦባማ ምላሽ ሰጡ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ለጥፈውት የነበረውን ዘረኛ ቪድዮ በተመለከተ ቀጥተኛ ያልሆነ ምላሽ ሰጡ።

ኦባማ በፖድካስት ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ "የመንግሥት ባለሥልጣናት ቀድሞ የነበራቸው ክብር እና ሃፍረት አሁን ጠፍቷል" ብለዋል።

ትራምፕ፤ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ እና ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማን እንደ ዝንጀሮ አድርጎ የሚያሳይ ይዘት ያለውን ዘረኛ ቪድዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ከለጠፉ በኋላ ማጥፋታቸው ይታወሳል።

ኦባማ ከፖድካስት አቅራቢው ብራየን ታይለር ኮኸን ጋር ባደረጉት ቆይታ ከተወያዩባቸው ነጥቦች መካከል አሁን በአሜሪካ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ይጠቀሳል።

ትራምፕ በገጻቸው ለጥፈውት የነበረው ቪድዮም እንደ አንድ ማሳያ ተደርጎ ቀርቧል።

ኦባማ ስለ ወቅታዊው የአሜሪካ ፖለቲካ ሲናገሩ "ከዚህ ቀደም አይተነው በማናውቀው መጠን በክፋት የተሞላ ሆኗል" ብለዋል።

ቪድዮው ከተለጠፈ በኋላ ዋይት ሀውስ ተቺዎችን "ሐሰተኛ ቁጣ አታስተጋቡ" ብሎ ቢያጣጥልም፤ ውግዘቱ ሲበረታ ቪድዮው ከትራምፕ ትሩዝ ሶሻል ገጽ እንዲጠፋ አድርጓል።

በአንድ የዋይት ሀውስ ሠራተኛ የተፈጸመ "ስህተት" እንደሆነም ተገልጿል። ቪድዮውን ሪፐብሊካኖችም ዴሞክራቶችም አውግዘውታል።

አጠቃላይ ቪድዮው 62 ሰከንድ ርዝማኔ አለው። 'ዘ ላየን ስሊፕስ ቱ ናይት' በሚል ማጀቢያ ሙዚቃ በተሠራው ቪድዮ መጨረሻ ላይ ባራክ እና ሚሼል ኦባማን እንደ ዝንጀሮ አድርጎ የሚያሳይ ክፍል ይታያል።

ቪድዮው በአውሮፓውያኑ በ2020 የተካሄደው ምርጫ ተጭበርብሯል የሚል ይዘትም አለው።

ትራምፕ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ "ምንም ስህተት አልሠራሁም። የቪድዮውን የመጀመሪያ ክፍል ብቻ ካየሁት በኋላ የቢሮዬ ሠራተኞች ለጥፈውታል። ኦባማዎችን በዚያ መንገድ የሚያሳይ ክፍል እንዳለው አላወቅኩም" ብለዋል።

ጥቁር አሜሪካዊው ሪፐብሊካን የሕዝብ እንደራሴ ቲም ስኮት "እጅግ ዘረኛ ነው" ሲሉ ቪድዮውን ተችተዋል።

ኤክስ ላይ ይዘት የሚያጋራው ወግ አጥባቂ ዜርያስ የሠራው ቪድዮ፤ ጥቁር ሕዝብን ከዝንጀሮ ጋር የሚያመሳስል ዘረኛ ይዘት ነው።

የፖድካስት አቅራቢው ከቪድዮው በተጨማሪ በአሜሪካ የስደተኞች እና ጉምሩክ ባልደረቦች (አይስ) የሚወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ ከኦባማ ጋር ተወያይቷል።

በአይስ የተገደሉ ሰዎች "የአገር ውስጥ አሸባሪዎች" መባላቸውን ኮንኗል።

"ከቀናት በፊት ትራምፕ የእርስዎን ፊት የዝንጀሮ አካል ላይ የሚያሳይ ቪድዮ ለጥፈዋል" ሲልም ተናግሯል።

ኦባማም በምላሹ "አብዛኞቹ አሜሪካውያን ይሄ ድርጊት ረብሿቸዋል። ከዋነኛ ጉዳዮች ትኩረት የሚያስለውጥ ነው" ብለዋል።

ኦባማ በመላው አሜሪካ ሲዘዋወሩ የሚያገኟቸው ሰዎች "ጨዋ፣ ሰው አክባሪ እና ደግ" መሆናቸውን ጠቅሰው "በማኅበራዊ ሚዲያ እና በቴሌቭዥን የሚታየው ግን ሰርከስ ነው" ብለዋል።

"የመንግሥት ባለሥልጣናት ሊኖራቸው የሚገባው ሃፍረት፣ አክብሮት እና ቅድሚያ የሚሰጠውን የመለየት አካሄድ አሁን ላይ ደብዛው ጠፍቷል" ሲሉም ወቅታዊውን የአሜሪካ ሁኔታ ገልጸዋል።

ኦባማ በቃለ ምልልሳቸው በሰላማዊ መንገድ አይስን የሚቃወሙ ሰዎችን አሞግሰዋል።

ቤተ መጻሕፍታቸው በቀጣይ ዓመት ቺካጎ ውስጥ እንደሚከፈትም ጠቁመዋል።